በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ ሲደረጉ ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ሰበታ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 11ኛ በማሳደግ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል።
በ10ኛው ሳምንት ሰበታ ከተማ በሜዳው ሀዋሳ ከተማን ድል ያደረገ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል። ስለሆነም ሰበታ ከተማ ድሉን ለማስቀጠል ድሬዳዋ ከተማም ከሽንፈት ወደ ድል በመመለስ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ያደረጉት ጨዋታ በመሆኑ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በጉጉት ተጠብቆ ነበር።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ሰበታ ከተማን ተጭነው መጫወት ችለው ተስተውለዋል። ይህንንም ተከትሎ በተደጋጋሚ በኦዶንጎ ሪችሞንድ እና በያሬድ ታደሰ አማካኝነት የሰበታ ከተማን ተከላካዮች ሲያስጨንቁ ውለዋል። ሰበታ ከተማዎችም ወደ ኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ታይተዋል።
በጨዋታው 19ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ሙህዲን ሙሳ ያስቆጠራት ግብ ድሬዳዋን ከወራጅ ቀጠናው ለማውጣት በቂ ሆና ተገኝታለች። ውጤቱንም ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ በ13ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሽንፈት ያስተናገደው ሰበታ ከተማ በ14 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ሊጉን መቐለ 70 እንደርታ በ22 ነጥቦች ሲመሩ በሸገር ደርቢ ድል የቀናቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ2ነጥብ ዝቅ ብለው በ20ነጥቦች ሁለተኛ እንዲሁም ወደ ጅማ አቅንተው ያለግብ አቻ የተለያዩት ፋሲል ከተማዎች በ19ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ወላይታ ድቻ፣ ጅማ አባጅፋር እና ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የኮከብ ግብ አግቢነቱን የፋሲል ከተማው ሙጂብ ቃሲም በ10 ግቦች ሲመራ የባህር ዳር ከተማው ፍፁም አለሙ፣ የመቐለ 70 እንደርታው አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በነዠየነ በእኩል 6ግቦች ይከተሉታል።