የኢትዮጵያ ኘሪሚዬር 21ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሃ ግብር ዛሬ በብቸኝነት ደደቢት በአዲስአበባ ስታዲዬም መቐለ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ ሲጀምር እንግዳዎቹ መቆለዎች ባለሜዳውን ደደቢት 2-1 በመርታት ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡
ዛሬ በብቸኝነት በአዲስአበባ ስታዲዬም ደደቢት በሜዳው መቑለ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ ለባለሜዳዎቹ 21ኛ የሊግ ጨዋታ ሲሆን ለእንግዳዎቹ መቐለዎች 1ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታና 1ያልተጠናቀቀ ጨዋታ እየቀራቸው 19ኛ የሊግ ጨዋታቸው ነበር፡፡በጨዋታው እንግዳዎቹ መቐለ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት እዚሁ አዲስአበባ ስታዲዬም ከወልዲያ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች የ1 ተጨዋች ለውጥ ሲያደርጉ አንተነህን በዳንኤል ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ ፡ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት በፋሲል ከተማ ሽንፈት ካስተናገዱበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች የተጨዋቾች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በዕለቱ የከተማዋ ቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ ታጅቦ በተካሄደው የደደቢትና መቐለ ከተማ ጨዋታ የተጠበቀውን ያህል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ፡ለተመልካች እምብዛም ሳቢ ሳይሆን መጠነኛ ፉክክር ተስተናግዶበት ተጠናቋል፡፡በጨዋታው ባለሜዳዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ሁነው ባመሹበት ጨዋታ ፡የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንደመውሰዳቸው የግብ ዕድል በመፍጠር በኩል ደካማ ሁነው አምሽተዋል፡፡የዛሬው የደደቢት አማካኝ ክፍል፡ከአጥቂ ክፍሉ የሚገናኝበት መስመር ጤናማና ውጤታማ አልነበረም፡፡ከአማካኝ አልፎ በመስመር በኩል ወደ መሀል ለፊት አጥቂው ጌታነህ የሚጣሉ ኳሶች ጣጣቸውን የጨረሱ አልነበሩም፡፡እንደውም የአጥቂ ክፍሉን አላስፈላጊ ጉልበት ለማውጣት የሚጋብዙ ነበሩ፡፡
በእንግዳዎቹ መቐለዎች በኩል በጥብቅ መከላከል የመልሶ ማጥቃትን አጨዋወት መርጠው ሲጫዎቱ አምሽተዋል፡፡ይሄው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ዛሬ ውጤታማ አድርጓቸው አምሽቷል፡፡በሁለቱም በኩል ግልፅ የግብ ዕድል በመፍጠር በኩል በተዳከሙበት ምሽት መቐለ ከተማዎች በ25ኛው ደቂቃ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት የሰራውን ጥፋት በአግባቡ ተጠቅመው በሚካኤል ደስታ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ከግቧ መቆጠር በሇላ ባለሜዳዎቹ የአቻነት ግብ ለማግኘት በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ፈጥረው ቢጫዎቱም የመቆለዎችን መረብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ደደቢቶች በዚሁ እንቅስቃሴያቸው ቀጥለው በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ መገባደጃ ኤፍሬም አሻሞ ፍፁም ቅጣት ምት ተጠልፎ ቢወድቅም የዕለቱ የጨዋታው ኢንተርናሽናል ዳኛዳዊት አሳምነው በዝምታ ከማለፋቸው ባሻገር ለኤፍሬም አታለኸኛል በሚል ቢጫ ካርድ መስጠታቸው ለተመልካቹ አነጋጋሪ ነበር፡፡
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በሁለቱም በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ ስንመለከት ባለሜዳዎቹ አሁንም የአቻነት ግብ ከማግኘት ባሻገር ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የነበራቸው ተነሳሽነት ፡መጠነኛም ቢሆን የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ጥሩ ነበር፡፡በዚህም በወሰዱት የጨዋታ ብልጫ ልክ ግብ ማስቆጠሩ ላይ ትልቅ የቡድኑ ችግር ነበር፡፡ደደቢቶች በጨዋታ ግልፅ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ አጥቂው ጌታነህ በቅጣት ምት ወደ ግብ የሞከራትን የመቐለውግብ ጠባቂ በቀላሉ አውጥቶበታል፡፡
በእንግዳዎቹ መቐሌዎች በኩል ከመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተሽለው በተንቀሳቀሱበት በዚህኛው አጋማሽ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡በዚህም በ54ኛውና 63ኛው ደቂቃ በቢስማርክና አማኑኤል አማካኝነት ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን ሲያደርጉ፡በ87ኛው ደቂቃ በደደቢት የግብ ክልል ውስጥ አጥቂው አማኑኤል በደደቢቱ ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ ተጠልፎ በመውደቁ የመሃል ዳኛው የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ አማኑኤል ወደ ግብነት ቀይሮ ፡የቡድኑን ሁለተኛ ግብ ሲያስቆጥር ተከላካዩ ከድር በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
ደደቢቶች ከግቧ መቆጠር በሇላ በ89ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት ስዩም ተስፋዬ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ አስራት መገርሳ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡
መቐለዎች ነጥባቸውን 32 በማድረስ ከጨዋታው በፊት ከነበሩበት 6ኛደረጃ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ብለው ወደ መሪዎቹ የበለጠ በመጠጋት ወርቃማ ድል ሲያስመዘግቡ ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ነገ ጅማ አባጅፋር እስኪጫዎት ሊጉን መምራት የሚያስችላቸውን መልካም አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቢባክንም በደረጃ ሰንጠረዡ አሁንም በ33ነጥብ በ2ኛነት ተቀምጠዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
☞አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ_ደደቢተ
በጨዋታው ጥሩ ተጫውተን ተሸንፈናል፡፡የጨዋታውን ውጤት የወሰኑት ዳኛው ናቸው፡፡የማያሻማ ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል፡፡በአንፃሩ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብናል፡፡ከዚህ ባሻገር ያለአግባብ ተጨዋች በቀይ ካርድ ወጥቶብናል፡፡ስለዳኝነቱ ብዙ እናገር ነበር፡፡ግን ከዚህ በላይ ብናገር ቅጣት ይከተለኛል፡፡
☞ አሰልጣኝ ዬሃንስ ሳህሌ-መቐለ ከተማ
በጨዋታው የተሻልን ስለነበርን አሸንፈናል፡፡ያገኘናቸውን በርካታ የግብ ዕድሎች በአግባቡ ባንጠቀምም የማሸነፊያ ግቦችን አስቆጥረን በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ፡፡