ትላንት ጅማሮውን ያደረገው የ 10ኛ ሳምንት ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ዛሬም ቀጥሎ ሲደረግ ፈረሰኞቹ ባህርዳር ከነማን አስተናግደው በሀይደር ሸረፋ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ከባለፈው ሳምንት አሰላለፉቸው የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ለመግባት ቢያስቡም የጣናው ሞገዶች ግብ ጠባቂ ሀሪትሰን ሄሱ መልበሻ ክፍል ውስጥ ከእለቱ ዳኛ ጋር በፈጠረው እሰጣ ገባ ከጨዋታ በፊት በቀይ ካርድ በመወገድ ከቋሚ አሰላለፍ ውጭ ለመሆን ተገዷል። በምትኩ ፅዮን መርዕድን ወደ ቋሚ አሰላለፍ መልሰው ወደ ሜዳ ሊገቡ ተገደዋል። በዚህም ወደ ሀድያ አቅንተው ነጥብ የተጋሩት ፈረሰኞቹ ባለፈው ሳምንት ያልተጠቀመባቸውን አቡዱልከሪም መሀመድ፣አቤል ያለው፣ሙሉአለም በቋሚ አሰላለፍ ወደ ሜዳ ይዘው ሲገቡ ባህርዳሮች ከወልዋሎ በሜዳቸው ሶስት ነጥብ ማሳካት የቻለው አሰላለፍ ያለተጠቀመባቸውን ተጫዋቾች ሳሙኤል ተስፋዮ፣ሄኖክ አቻሜለህ፣ ሳምሶን ጥላሁንን ጨምሮ በቀይ ካርድ የወጣው ሀሪትሰን ሄሱ ምትክ መርዕድ ፅዮንን ይዘው ገብተዋል።
9:00 ላይ የጀመረው ይህ ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ እንደሚመሩት ቢታወቅም በግል ጉዳይ ምክንያት ጨዋታውን መምራት ሳይችሉ ቀርተው በምትካቸው ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ እየተመራ የጀመረው ይህ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖቾ ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ ግብ ደርሰው የግብ እድሎች ለመፍጠር ሲታትሩ የታየ ሲሆን። በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ቢኖራቸውም ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ ቅ/ጊዮርጊስ የተሻሉ ቢሆኑም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ግን የጣናው ሞገዶች የተሻሉ ነበሩ። በሙከራ ረገድ ቀዳሚ የነበረት ባህርዳሮች 4ኛው ደቂቃ ላይ በዜናው ፈረደ አማካኝነት ጥቃት ቢሰነዝሩም ግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ በቀላሉ ተቆጣጥሯታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ መልስ የሰጡት ጊዮርጊሶች አብዱልከሪም መሀመድ አክርሮ የመታውን ኳስ በባህርዳር ተከላካዮች ተጨርፋ ወጥታበታለች።
- ማሰታውቂያ -
ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ከመፈለጋቸው የተነሳ ሁለቱም ቡድኖች ኳሶቻቸው ይቆራረጡ ስለነበር ተከላካዮችን ለስህተት ሲዳርግ ተስተውሏል። በዚህም ማማዱ ሲዲቤ የተከላካዮቹን መዘናጋት ተከትሎ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርም ማታሲ በቀላሉ ይዞበታል። በባህርዳሮች በኩል አስቆጪ የነበረችው ኳስ ግርማ ዲሳሳ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥኑ እየገፋ ሲሄድ ኳሷ ከእግሩ አምልጣ ወጥታበት ግብ ጠባቂው ፖትሪስ ማታሲ ቀድሞ የተቆጣጠረበት ነበረች። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ ጋዲሳ መብራቴ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አገባው ሲባል በግቡ ቋሚ ለጥቂት ወጥታበታለች። ጨዋታው ግብ ሳያስተናግድ 0-0 በሆነ ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ። ይህ ነው የሚባል አስደንጋጭ ሙከራ ባንመለከትበትም ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ ኳስ ተቆጣጥረው በመጫወት የተሻለ በመሆን አሸንፈው የወጡበትን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከዚህ ባለፈም ሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ ታይተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ዜናው ፈረደ ከግብ ጠባቂው ፖትሪክ ማታሲ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረችው ኳስ አስቆጪ ነበረች። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ መስመር በኩል ምንተስኖት አዳነ ያሻገረለትን ኳስ ሀይደር ሸረፋ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር እንዲሁም ባህርዳር ከነማ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።
ሆኖም ግን በተቃራኒ የግብ ክልል ሲደርሱ የሚታዩት ድክመቶች ሁለቱም ቡድኖች ግብ ከማስቆጠር ተቆጥበዋል። 81ኛው ደቂቃ የባህርዳር ከተማው ሳሙኤል ተስፋዬ አቤል ያለው ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታው በዚህ ውጤት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በ17 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ መቀመጥ ሲችሉ ሽንፈት ያስተናገዱት የጣናው ሞገዶች በ14 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።