የሀድያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ አካውንት ታገደ
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ለመተካት የተደረገው የወላይታ ድቻ ሙከራ ተቃውሞ ገጠመው
“የሚዲያ ባለቤቶች ስለሚከፈላችሁ ወደ አሰልጣኙ ትወግናላችሁ፤ባጣ ቆየኝ ስላልሆንን አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን አነጋግረነዋል”
አቶ ወንድሙ ሳሙኤል /የወላይታ ድቻ ዋና ስራ አስኪያጅ/“ዋና ስራ አስኪያጁ ከተሾመ ገና 15 ቀናት አልሞሉትም ያልነበረበትን ነው የሚያወራው”
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው
ከ15 ተጨዋቾቹ ጋር በተከሰተው አለመግባባት አሰልጣኙንና ተጨዋቾቹን ያገደው ሀዲያ ሆሳዕና ከደረቅ ቼክ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አካውንት መታገዱ ተሰማ፡፡
ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት የታገዱትን 15 ተጨዋቾች በህግ ጠበቃቸው ብርሃኑ በጋሻው ውክልና ከሀዲያ ሆሳዕና አመራሮች ጋር ለማግባባት የተደረገው ጥረት በክለቡ አመራሮች እንቢተኝነት ድርድሩ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ድርድር ከጀመሩ በኋላ የክለቡ አመራሮች ወደ ኋላ ያፈገፈጉት በደጋፊዎች የሚደርስባቸውን ጫና በመስጋት ሳይሆን እንደማይቀር የገለፀው የውስጥ አዋቂ ምንጫችን የክለቡ አመራሮች በፍትህ አካላት ውሣኔ ይሰጠው ማለታቸውን ተከትሎ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሣኔ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡
ክለቡ ውላቸው የሚያልቀውን ተጨዋቾች ለ2 አመት ማገዱና ደመወዝ መከልከሉ በፍትህ አደባባይ ተቀባይነት ሊያሳጣው እንደሚችል የሚገልፀው ምንጫችን ተጨዋቾቹ በእጃቸው ካለው 15 ደረቅ ቼክ አስራ ሶስቱ ለባንክ ቤት በማስመታታቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንቱን ማገዱ ታውቋል፡፡ እገዳው በብሔራዊ ባንክ በኩል ለሁሉም ባንኮች መተላለፉ የማይቀር በመሆኑ ክለቡን ለሌላ አጣብቂኝ የዳረገው ሆኗል፡፡
ደረቅ ቼኩ ሕግ ክፍል ይዞት ወደ መደበኛ ፍ/ቤት የተመራ መሆኑ የክለቡ አመራሮችን የባሰውኑ ማስደንገጡ አልቀረም፡፡ ተጨዋቾቹ በእጃቸው የያዙት ደረቅ ቼክ እንዳለ ክለቡ ለውይይቱ በሩን መዝጋቱ አስገራሚ አድርጎታል ተብሏል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና ከተጨዋቾቹ ውጪ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን የ7ዐ ሺ ደመወዝ አግዶ ውሉን ማፍረሱ ሌላ የፍትህ ክስ በፌዴሬሽኑ የፍትህ አካላት ስር መቅረቡ የማይቀር መሆኑ ደግሞ ያለውን አስተዳደራዊ ችግር የሚያሳይ ሆኗል፡፡ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና በሀዋሳ ከተማ 3ለዐ የተረታበት ውጤት ከዚያ በፊት ሙሉ ቡድኑ በተረጋጋበት ወቅት አንድም ክለብ አስቆጥሮ አለማወቁ የተፈጠረውን አለመግባባት የክለቡ ቦርድና ጽ/ቤት በሠላም ሊፈቱት አለመቻላቸውን ተከትሎ የመጣ አስደንጋጭ ውጤት ሆኗል፡፡ ሊጉ ሲጠናቀቅ ሀዲያ ሆሳዕና በ24 ጨዋታ በ38 ነጥብና 7 ግብ 4ተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ የባንክ እገዳ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ወደ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ መላኩ ማዶሮ ስልክ ብንደውልም ቴክስት ብናደርግም ምላሽ ባለመስጠታቸው በክለቡ በኩል ያለውን ሂደት መግለፅ አልቻልንም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ወላይታ ድቻ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪንሆ/ ምትክ ጅማ አባጅፋርን ከመውረድ ያላተረፈውን አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ለመቅጠር ወስኗል መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በአሰልጣኝ ዘላለም ስር ምርጥ ውጤትና ማራኪ አጨዋወት ያሳየው ወላይታ ድቻ በ24ጨዋታ 33 ነጥብና 2 ግብ 8ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ ታዲያ የተሰማውና ጅማ አባጅፋርን ከወራጅነት መታደግ ያልቻለው አሰልጣኝ ፀጋዬ ክለቡ 12ኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ የአሰልጣኝ ዘላለም ምትክ ሆኖ ወላይታ ድቻን ለማሰልጠን ተስማምቷል መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የትግራይ ክልል ክለቦች መቐለ 7ዐ እንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራትና ስሁል ሽረ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካልተመለሱ በ6 ክለቦች መሀል የፊታችን ሰኔ 18/2ዐ13 ለሚጀመረው ፍልሚያ ጅማ አባጅፋር እየተዘጋጀ ባለበት ሰዓት ለወላይታ ድቻ ለመፈረም መዘጋጀቱ በርካቶችን ቢያስገርምም አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ግን አጣጥሎታል፡፡ አሰልጣኙ ለሀትሪክ ሲናገር “የወላይታ ድቻ አመራሮች አነጋግረውኛል ነገር ግን ገና የተጠናቀቀ ነገር የለም በአሁን ሰዓት ያለሁት ጅማ ነው ሰኔ 18 ለሚጀመረው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ጅማ አባጅፋርን ለመምራት ከክለቡ አመራሮች ጋር ተነጋግሪያለሁ ተጨዋቾቹ ክፍያ ስላልተፈፀመላቸው ገና አልተሰባሰቡም የእነሱን ቅሬታ አስወግደን ጅማ አባጅፋርን ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ለማቆየት እየተዘጋጀን ነው ከዚህ ውጭ የሚወራው ሁሉ ውሸት ነው” ሲል አስተባብሏል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው “ሶዶ ላይ ምርጥ ምርጥ ወጣቶች አሉ ይሄ ደግሞ ከከፍተኛ ወጪ ክለቡን ይታደጋሉና የ4 አመት ኮንትራት ተሰጥቶኝ ልስራ” ቢልም ተቀባይነት ማጣቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ አሰልጣኞች ለአንድ አመት ብቻ እየፈረሙ ከከለብ ክለብ ይዘዋወራሉ ተብሎ በሚተችበት ፕሪሚየር ሊጉ የወላይታ ድቻ አመራሮች አሰልጣኝ ዘላለምን በደስታ አለማስፈረማቸው መነጋጋሪያነትን ፈጥሯል፡፡ ሀትሪክ ባገኘችው መረጃ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እስከ ሐምሌ 3ዐ/2ዐ13 ድረስ ኮንትራት ያለው ሲሆን የግንቦት፣ የሰኔና ሐምሌ ወር ደመወዝ ያልተከፈለው በመሆኑ የአሠልጣኝ ፀጋዬ የውል ስምምነት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሳሙኤል በተፈጠረው ልዩነት ዙሪያ ሲናገሩ ”አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ኃላፊነቱን ስለማይፈልግ ከቦርዱ ጋር የነበረውን ስብሰባ ረግጦ ወጥቷል ስለዚህ ባጣ ቆየኝ ስላልሆንን አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን አነጋግረነዋል ገና የሚቀሩ ነገሮች አሉ ያለው እውነታ ይሄ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ስለልዩነቱም ሲናገሩ “ከአንድ አሰልጣኝ የማይጠበቅ ተግባር ነው የፈፀመው፡፡ ኮንትራቴ ለ4 አመት ይራዘምልኝ ብሎ አቀረበ ….አይ 2 አመት ይሁን ውጤት ካመጣህ ኮንትራትህ እየታደሰ እስከ 15 አመት ልትሰራ ትችላለህ ብለን ለ2 አመት በሚል ከተስማማን በኋላ ነዳጅ፣ አልጋ፣ ምግብ… እያለ የሚፈልገውን ጥቅማጥቅም ገልጾልን እኛም ተቀብለነው የመጨረሻ ደመወዝና የፊርማ ክፍያህን አሳውቀን ስንለው ቆይ አሁን ማቅረብ አልችልም” ሲል መልሶልናል “በኋላ ላይ ከተገደድኩ ግን ከጓደኞቼና ከአሰልጣኞች ጋር ተነጋግሬ ልምጣ 1ዐ ደቂቃ ጠብቁኝ ብሎን ከወጣ በኋላ ሳይመለስ ቀርቷል፡፡ ብንጠብቀውም አልመጣም ስልክ ልንደውል ብንፈልግም የምናውቃቸውን ሁሉንም ስልኮች ዘግቶ ሄደ ይሄም በኃላፊነቱ ለመቀጠል አለመፈለጉን ያሳያል፡፡ አሰልጣኙ የፈፀመው የወረደ ተግባር ነው የቤት ውሻ እንኳን አክብረኸው ነው የሚያከብርህ እሱ ግን ያከበረውን ቦርዱን ሳያከብር ረግጦ ሄዷል ያለው እውነት ይሄ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አቶ ወንድሙ በውዝግቡ ዙሪያ ወገንተኝነት ታይቶበታል ያሉትን ሚዲያውን ተችተዋል…. “ፌስቡክ ላይ የሚራገበው ሚዲያው የሚያወራው ልክ አይደለም አሰልጣኙ የሚያወራው የራሱን ሲቪ ለመጠበቅ ይመስላል የሚዲያ ባለቤቶች ስለሚከፈላችሁ ወደ አሰልጣኙ ትወግናላችሁ አብዛኛው የሚዲያ ባለሙያ ለአንድ ወገን መወገኑን ማቆም አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ ሲፈርም ደመወዙ ይከፈለው የነበረው ከናንተ አቅም ጋር ተገናዝቦ ያለን አቅም ይሄ ነው ብላችሁት ከሆነ አሁንስ ይሄን ሃሳብ ለምን ሰረዛችሁ በሚል ከሀትሪክ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ወንድሙ “ይሄ ውሸት ነው ከቤት አምጥተን ስናስፈርመው 5ዐ ሺ ብር ይከፈለኝ ብሎ እኛም ተስማምተን ነው ብር ከሌለ 5ዐ ሺ ብር ሲከፈለው የነበረው ከየት መጥቶ ነው” ሲሉ ቅሬታውን አጣጥለውታል፡፡
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ግን የዋና ስራ አስኪያጁን ሃሳብ “በውሸት የተሞላ ነው” ሲል አጣጥሎታል፡፡ “ሲጀምር ዋና ስራ አስኪያጁ ከተሾመ ገና 15 ቀናት አልሞሉትም የት ነበረና ነው ስለዚያ ጊዜ የሚያወራው… ያልነበረበትን ነው የሚያወራው በኔ በኩል ያለው እውነት ደመወዝ የለንም ብለው ያቀረቡትን ክፍያ ነው የተቀበልኩት አሁን ግን ብሩን ንገረን የሚሉት አብዝቶብን ሳንሰማማ ተለያየን ሲሉ ፈልገው ነው… ደመወዝኮ የሚገባልን በ5ዐ ቀን ነው ሰው 3ዐ ቀን ሰርቶ ደመወዙን ሲቀበል እኛ የ3ዐ ቀን ስራችንን ደመወዝ የምናገኘው በ5ዐ ቀኑ ነው ባለፈው ገና በ3 ቀን አሻሽለው በ47 ቀን ከፈሉን” ሲል ተችቷል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም “አዲስ መጪ ተጨዋቾች የቦርዱን አመራሮች አያውቁም ፕሬዚዳንቱ ጋር ደውዬ ኧረ ኑና እዩዋቸው ስለው መብታችሁ ተነካ እንዴ ካልተነካ ምን እናደርጋለን ብሎ መልሶልኛል የክለቡን ምስጢር እንጠብቅ ብለን እንጂ ብዙ የምንናገረው ጉድ ነበረን፡፡ አሁን ጊዜው አይደለምና ትቼዋለሁ፡፡ አሁንም ግን የግንቦት ወር ደመወዝ ገና አልተከፈለንም በኔ እምነት ክለቡ በተገቢ መንገድ እየተመራ ነው ብዬ አላምንም” ሲል አሰልጣኙ ለሀትሪክ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
አስተያየት ይስጡ