ላለፉት አራት ዓመታት የእግር ኳሱን የመጨረሻ
ስልጣን ይዞ የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የስልጣን ጀምበሩ በመጥለቂያዋ የመጨረሻዋ ሰዓት
ላይ ይገኛል፡፡ በፌዴሬሽኑ የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት
በመስከረም መጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አዲስ
ምርጫ ማከናወን ሲገባው ፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤው
የሚካሄድበት ቀንና ስለ ጉባኤው አጀንዳዎች እስካሁን
የተነፈሰው ነገር አለመኖሩ፣ “እግር ኳሱም እንደ
አትሌቲክሱ በስፖርት ውስጥ ባለፉ ሰዎች ይመራ”
የሚለው በአዲሱ ምርጫ ዋዜማ የጠቅላይ ሚኒስትር
ሀይለማሪያም ደሳለኝ ቁም-ነገር ያለው መልዕክት
በፌዴሬሽኑ አካባቢ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል
ስለመባሉ፣ “ክለቦች በፈጠሩት መሞዳሞድ አላግባብ
ከሊጉ ወርጃለሁ” ለሚለው የጅማ አባቡና ክስ እስካሁን
ምላሽ አለመሰጠቱ፣ በብ/ቡድን አሰልጣኝነታቸው በጋና
በሰፊ ውጤት የተሸነፉትና በእሳቸው የሚመራው
ቡድን ከሁለት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻን ሻምፒዮና ውጪ የሆነባቸው አሰልጣኝ
አሸናፊ በቀለ “ልልቀቅ” እያሉ ፌዴሬሽኑ ጥያቄያቸውን ማስታመሙ፣ የአዲሱ የውድድር
ዘመን የኢትጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን እስካሁን አለመታወቁ ክለቦች የቅድመ
ውድድር (ፕሪ-ሲዝን) ዝግጅታቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል የሚሉ
ጥያቄዎችን የሀትሪክ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ እንዲመዝና ወደ
ፌዴሬሽኑ የፅ/ቤት ኃላፊ ጋር ስልክ ደውሎ “ይሄ ሁሉ ለምን?” ሲል ጥያቄዎችን አቅርቦ
ከፅ/ቤት ኃላፊው ከአቶ ወንድምኩን አላዩ ከዚህ በታች ያለውን ምላሽ አግኝቶ ለአንባቢዎቹ
በሚመች መልኩ አቅርቦታል፡፡ ሁሌም ለዝግጅት ክፍላችንና ለአንባቢዎቻችን ጥያቄዎች ዋጋና
ክብር በመስጠት የሚተባበሩን የፅ/ቤት ሀላፊውን አቶ ወንድምኩን አላዩን ለትብብራቸው ከልብ
እናመሰግናለን፡፡
ሀትሪክ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም
ደሳለኝ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ለጀግኖች
አትሌቶቻችን ሽልማት ሲሰጡ የተናገሩት
ንግግር ብዙዎችን የእግር ኳስ ቤተሰቦች
አስደስቷል፤ “እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ እግር
ኳሱንም መምራት ያለባቸው በስፖርቱ
ውስጥ ያለፉ መሆን አለባቸው” የሚል ትልቅ
ቁም ነገር ያለው መልዕክት ማስተላለፋቸው
በፌደሬሽኑ ውስጥ መደናገጥን እንደፈጠረበት
ተሰምቷል? ወሬው ዕውነት አለው?
አቶ ወንድምኩን፡- ዕውነት ለመናገር
ምንም የፈጠረው መደናገጥ የለም የጠቅላይ
ሚኒስትሩን ንግግር ከመደናገጥ ይልቅ
በገንቢ መልዕክትነቱ ነው የወሰድነው፤
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ማንኛውም አካል
እንደተቀበለው ሁሉ እኛም በበጎ መልኩ
እንቀበለዋለን እንጂ የፈጠረው ድንጋጤ
የለም፡፡
ሀትሪክ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማ
ሪያም ደሳለኝ ንግግር የመንግስት አቋም
ከመሆኑ አንፃር “እግር ኳሱንም እንደ
አትሌቲክሱ በስፖርቱ ውስጥ ባለፉና ጊዜ
ባላቸው ሰዎች ይመራ” የሚል ታላቅ ቁምነገር
ያለው መልዕክቱን ባስተላለፉበት በዚህ ወቅት
ከእግር ኳስ ጋር ትውውቅ የሌላቸውና እግር
ኳስ እግር ኳስ የማይሸቱ ሰዎች በድጋሚ
ለመመረጥ መሮጣቸው የመንግስትን ውሳኔ
ካለማክበርና ለእግር ኳሱ ካለማሰብ ጋር
አይያያዝም?
አቶ ወንድምኩን፡- መንግስት ፌዴሬ
ሽኖችን በተመለከተ የመደገፍና የማገዝ ስራ
ነው እንጂ የሚሰራው በፌዴሬሽኖች ምርጫ
ጣልቃ ይገባል ብዬ አልገምትም፤ በዚህ ጉዳይ
ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ ነው ብዬ
ባላስብም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት
ተከትሎ ውሳኔው መሆን ያለበት የጠቅላላ
ጉባኤው ነው። ይበጃሉ ለእግር ኳሱ እድገት
ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሰዎች የመጠቆምና
የመምረጥ መብቱ የእነሱ ነው፤ ከዚህ ውጪ
እገሌ ባለሙያ ነው እገሌ አይደለም ብሉ
መደምደም ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ እግር
ኳስ የብዙ ዲሲፒሊኖች ስብስብ ወይም
ሰፊ ነገር ነው፤ የዳኝነት፣ የማርኬቲንግ፣
የቴክኒክ፣ የእግር ኳስ ልማት ሙያን የያዘ
ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልል ወይም እጩዎችን
የሚልከው አካል ይሄንን መሰረት ያደረገ፤
ለእግር ኳሱ እድገት ይበጃሉ፣ ይጠቀማሉ
ያላቸውን ሙያተኛችን መርጦ ይልካል ብለን
ነው የምንጠብቀው፡፡
ሀትሪክ፡- የብሄራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ
አሸናፊ በቀለ “ጣልቃ ተገብቶልኛል” የሚል
ምክንያት አቅርበው ብሄራዊ ቡድኑን
የመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፤ በአሰልጣኙ
ጥያቄና ፍላጎት መሰረት ፌዴሬሽኑ
ማስተናገድ ያልቻለው ለምንድነው?
አቶ ወንድምኩን፡- የብሄራዊ ቡድኑን
አሰልጣኝ የመልቀቂያ ጥያቄን በተመለከተ
እንዳልከው “ልልቀቅ” ብለው ጠይቀዋል፤
እሁን አሰልጣኙ ያሉት ሞሮኮ ነው ነገ (እሁድ
ማለታቸው ነው) ይገባሉ፡፡ ስለዚህ የእሳቸው
ጉዳይ በሚቀጥለው ሳምንት የሚታወቅ
ይሆናል፡፡ እኛ ግን አሰልጣኙ ከእኛ ጋር
እንዳሉ ነው የምናውቀው፤በእኛ በኩል
በጥያቄያቸው መሰረት ስራቸውን እንዲቀጥሉ
ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል፡፡
ሀትሪክ፡- አሰልጣኙ ኃላፊነቱን
ከተረከቡ በኋላ በጋና ብሄራዊ ቡድን የግብ
ናዳ ወርዶባቸው 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት
ተሸንፈዋል፤ ከእኛ በዙም በማትሻለው
ሱዳን ተሸንፈው ከቻን ውድድር ውጭ
አድርገውናል፤አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና
ዮሃንስ ሳህሌ ያሳኩትን የቻን ተሳትፎ
በእሳቸው ጊዜ በደካማዋ ሱዳን ተሸንፈው
አሳጥተውናል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ጋር ሲዋዋሉም
ለአፍሪካ ዋንጫና ለቻን ውድድር አሳልፋለሁ
ቢሉም አንዱንም ሳያሳኩ ደካማ ውጤት
እያላቸው ይሄን ያህል ማስታመም ያስፈለገው
ለምንድነው?
አቶ ወንድምኩን፡- እውነት ለመናገር
በአሰልጣኙ አጭር የስልጠና ጊዜ ውጤት
ማጣታችን አሳዝኖናል፤ በተለይ በተደጋጋሚ
ከተሳተፍንባቸው የቻን ውድድር ውጭ
መሆናችን ከሁለት ዓመት በኋላ አሰልጣኙ
ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት ነው፤ ይሄንን
መካድ አይቻልም፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ
ጅማሪያችንም በሰፊ ጎል በመሸነፍ ቢጀምርም
ወደ አፍሪካ ዋነጫ የመመለስ ዕድላችን
ተሟጦ አላለቀም፤ እንደውም በካፍ አዲሱ
የውደድር ፎርማት (አሰራር) መሰረት እድሉ
አሁንም አለን። በቀጣይ ምን መሆን አለበት?
ጥያቄያቸው እንዴት ነው የሚስተናግደው?
የሚለው ከሞሮኮ ከተመለሱ በኋላ ጊዜ ወስደን
የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- እስካሁን ባስመዘገቡት ውጤት
ደስተኛ ስለሆናችሁ ነው “ልልቀቅ” እያሉ
“አትለቅም” ለማለት የወሰናችሁት?
አቶ ወንድምኩን፡- በጋና በሰፊ
ወጤት ተሸንፈናል፤ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ
ከተሰማሟቸው ነገሮች አንዱን ማሳካት
እንደተሳናቸው የሚታወቅ ነው፤ ሌላውን ጊዜ
ወስደን ነው የምናየው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
የስልጣን ዘመኑ ተጠናቋል ማለት ይቻላል፤
ከዚህ አንፃር ጠቅላላ ጉባኤ በያዝነው ወር
መጥራት ሲገባችሁ ወደ ህዳር ወር ለመግፋት
እያሰባችሁ ያላችሁት በሚል የሚወራ ነገር
አለ፤ ለምን በደንቡ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ
አልጠራችሁም?
አቶ ወንድምኩን፡-ጠቅላላ ጉባኤውን
አልገፋነውም፤ በደንቡ መሰረት በጥቅምት ወር
መጨረሻ አካባቢ ጉባኤው እንደሚካሄድ እቅድ
ተይዟል፡፡ ለምን አሁን ዘገየ የሚል ቅሬታ
ሊቀርብ እንደቻለ አልገባኝም? ምንአልባት
ቶሎ እንዲካሄድ ተፈልጎ ከሆነ አላውቅም
እንጂ ባለፈው ዓመትም ህዳር 25 አካባቢ ነው
ጉባኤው የተካሄደው፤ ከዚያ በፊትም የነበረውን
ጉባኤም ያካሄድነው በተመሳሳይ ጊዜ ነው።
አሁንም ለጉባኤው የሚያስፈልጉ መሰረታዊ
ነገሮችን እያስተካከልን ነው ፤ጉባኤውም
በጥቅምት ወር መጨረሻ ይካሄዳል፡፡ በቀጣይ
ጊዜያት ለጉባኤው ተሳታፊዎች አጀንዳዎችን
በተመለከተ ተዘጋጅተው እንደመጡ
እንልክላቸዋለን፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ያለው የፌዴሬሽኑ
አመራር ስልጣኑን ምርጫ ተካሂዶ ባያስረክብም
የስልጣን ዘመኑ ተጠናቆ ለጉባኤው መሳካት
አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የሚያከናውኑበት ጊዜ
መሆኑ ይታወቃል፤ ፌዴሬሽኑ ግን ከዚህ
በተቃራው ሆኖ በስልጣኑ የመጨረሻ ሰዓት
ደንቦችን የማሻሻል፣ የማስተካከል ስራ ላይ
መጠመዱ ብዙ ቅሬታዎችን እያስነሳ ነው
በዚህ ላይ ምን ትላለህ?
አቶ ወንድምኩን፡– ፌዴሬሽኑ በአሁን
ሰአት ያን ያህል ቅሬታ የሚያስነሳ ስራ እየሰራ
እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ አንዳንድ የአሰራር
ማሻሻያና ደንቦችን ማስተካከያ ቢያደርግም
የዝውውር መመሪያ የውድድር ደንቦችና
የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የማሻሻያ ሃሳብ
ሊያቀርብ ይችላል፡፡ በደንቡ መሰረት ፌዴሬሽኑ
ይሄንን ቢያደርግም የሚያፀድቀው የሚሻረውና
የሚያሻሽለው ጠቅላላ ጉባኤው እንደሆነ
መታወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን ምንድነው ካፍና
ፊፋ አሰራሮቻቸውን አሻሽለዋል፡፡ እያንዳንዱ
አባል አገርም ከፊፋና ከካፍ አንፃር የራሱን
ደንብ መከለስ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ የሴቶች ተሳትፎ አለ፤ ይሄንን ጉዳይ
ደግሞ ባለፈው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይሄንን
የሚያሻሽል አካል ሰይሟል፡፡ ስለዚህ ይሄ
የሰየመው አካል ያሻሻለውን የስራ አሰፈፃሚ
ኮሚቴ የሚቀበለው ከሆነ ለጠቅላላ ጉባኤው
የሚቀርብ ነው የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፌደሬሽኑ በመጨረሻው ሰአት
እየሮጠባቸው ካሉ ነገሮች አንዱ በድጋሚ
በስልጣን ለመቆየት የሚያስችለውን የደንብ
ማሻሻያ ለማድረግ እየተጣደፈ ነው፡፡ በተለይ
የክልል ውክልናን በተመለከተ 11 ክልሎች 11
ሰዎችን ዕጩ አድርገው በማቅረብ ያለ ድምፅ
በቀጥታ በስራ አስፈፃሚው ወንበር እንዲያገኙ
የሚያደርግ የደንብ ማሻሻያ እያደረገ ነው
በሚል የሚቀርብ ወቀሳ አለ ይሄ እውነት
ነው?
አቶ ወንድምኩን፡- ይሄ መሰረተ ቢስ
ወሬ ነው…! በፍፁም እንደዚህ አይነት
አሰራር ሊኖር አይችልም፤ ዕጩዎች ሊቀርቡ
የሚችለው በአለም አቀፍ ደንብ መሰረት
ነው፡፡ ውክልና አንዴት ይሆናል? በክለቦች
ብዛት፣ በክልሎች፣ በማህበራት የሚለው ነው
መታየት ያለበት፤ እያንዳንዱ እንዴት ነው
ድምፅ ወይም ውክልና መስጠት ያለበት?
የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ አንድ ያለው
እውነታ ግን ያለፈው የመተዳደሪያ ደንብ
አለ ከዚያ ብዙም የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡
፡ አሁን ምን አይነት የማሻሻያ ሃሳብ
እንደሚቀርብ አልታወቀም፡፡ ገና ማሻሻያውን
የሚሰሩት ሰዎች ምን አይነት ማሻሻያ
ለስራ አሰፈፃሚው ኮሚቴው እንደሚያቀርቡ
ባልታወቀበት ሁኔታ ቀድሞ እንዲህ ነው
ማለት አይቻልም፡፡
ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑ በመጨረሻው
ሰአት በማስተካከያ ሰበብ የሚዲያውን ነፃነት
የሚገፋ የሚያሸማቅቅ አንቀፅ በመተዳደሪያው
ደንብ ውስጥ ለማካተት እንቅልፍ እያጣ ነው
በሚል የሚቀርበው ጠንከር ያለ ወቀሳ ሌላው
ነው ፤ እግር ኳሱን ከመቼውም ጊዜ በላይ
እያገዘና ለእድገቱ ትልቁን ሚና እየተጫወተ
ያለውን ሚዲያ አፍ ለማዘጋት በማሰብ ነው
ማስተካከያ ማድረግ የፈለጋችሁት?
አቶ ወንድምኩን፡- አረ በፍፁም…!
ሚዲያውን በተመለከተ ምንም የተሰራ ነገር
የለም፤ ያለ ሚዲያው እገዛ የትም መድረስ
እንደማይቻል እናውቃለን፡፡ ከዚህ ይልቅ በእኛ
በኩል ሚዲያውን በተመለከተ ከመቼውም
ጊዜ የተሻለ ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ
የመስራት ሃሳቡ ነው እኛ ጋር ያለው፡
፡ በአዲሱ አመት ፍፁም ግልፅነት ያለው
ለሚዲያው የተመቻቸ ዘመናዊ አሰራርን
የመዘርጋት ሃሳቡ ነው ያለን፡፡ ለምሳሌ
ሚዲያው ስራዎችን በቀላሉ እንዲሰራ አዲስ
አበባ ስቴዲየም በሚሰቀለው ትልቅ ስክሪን
አማካይነት ስቴዲየም ውስጥ ተቀምጦ መረጃ
የሚያገኝበት መንገድ የሚመቻችበት ስራችንን
እያጠናቀቅን ነው፤ እኔ የማውቀው ይሄንን
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ጅማ አባቡና ከፕሪምዬር ሊጉ
የወረደኩት ክለቦች ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር
በተያያዘ በፈፀሙት የስፖርታዊ ጨዋነት
ግድፈት ነው በሚል የተለያዩ መረጃዋች
በማቅረብ በተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረበ ነው፤
የዚህ ክለብ ቅሬታ ምን ምላሽ አገኘ?
አቶ ወንድምኩን፡- ትክክል ነው ጅማ
አባቡና ጥያቄ አቅርቧል፤ በጥያቄው መሰረት
መልስ ለመስጠት እየተደረገ ያለው የማጣራት
ስራ አልተጠናቀቀም፡፡ ይሄን ጉዳይ እንዲያጣራ
የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ መጀመሪያ ላይ
አካባቢ የመጡ ቅሬታዎች ነበሩ እነዛን መሰረት
አድርጎ የተወሰነ ርቀት ያህል ሄዶባቸዋል፡
፡ በየጊዜው አዳደስ መረጃዎች፣ ጥቆማዎች
ስለመጡ እነዛን ጉዳዮች እንደገና የማየት
ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እነዚህን ጥቆማዎች
መሰረት በማድረግ አጣርቶ የማያዳግም
እርምጃ መውሰድ ስለሚገባ በዚህ ነገር ላይ
እየተሰራ ነው ያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ በፊት አጣሪ ኮሚቴ
ተቋቁሞ የጨዋታ ማጭበርበርን (match
fixing) የሚጠቁም መረጃ አላገኘሁም ብሎ
መግለጫ የሰጠበት ሁኔታ ነበር፤ ይሄ ነገር
አንተ ከምትለው ጋር አይጋጭም?
አቶ ወንድምኩን፡- ትክክል ነው…
አጣሪ ኮሚቴው በወቅቱ የሰጠው መግለጫ
እስካሁን የተደረሰበት ነገር ምንድነው?
ምንምን አይነት ስራዎች ተሰሩ የሚለውን
ለህዝቡ ግልፅ የማድረግ ስራ ነው የተሰራው
እንጂ ውሳኔውን አይደለም ያሳወቁት፤ ውሳኔ
ለሚሰጠው አካል ተጨማሪ ግብዓት የሚሆኑ
ነገሮች ናቸው የቀረቡት፡፡ የአጣሪ ኮሚቴው፣
የፖሊስ፣ ይመለከታቸዋል ተብለው የተጠሩ
ተጫዋቾች ቃል የተወደሰበት ሁኔታ ነው
ያለው፤ በዚህ መሰረት የተሰበሰቡ የተያዙ
መረጃዎች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ከፖሊስ
ወይም የወንጀል ምርምራ አንዳንድ የተጀመሩ
የማጣራት ስራዎች አሉ፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ
ተጣርተው ካለቁ በኋላ በእርግጠኝነት በአጭር
ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ብለን እንጠብቃለን፡
፡ ውጤቱ እንደደረሰን የምናሳውቀው ነው
የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- አንት ከምትለው በተቃራኒ
ያለ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት
ፌደሬሽኑ ጅማ አባቡና ያቀረበውን ጥቆማ
በተመለከተ ለመወሰን እንደተቸገረና በውጤቱ
መሰረት አጥፊው ላይ እርምጃ ከመውሰድ
ይልቅ ማቻቻልን በመምረጥ የፕሪምዬር
ሊጉን ክለቦች ቁጥር ወደ 17 ለማሳደግ እያሰበ
ነው የሚል ነገር ይነሳል ሰለዚህ ጉዳይ ምን
ትላለህ?
አቶ ወንድምኩን፡-በፍፁም አይደረግም…
!አንድን ስህተት በሌላ ስህተት የማረም ስራን
እንደማንሰራ ላረጋግጥህል እችላለሁ፤ ተፈጠረ
የተባለውን ችግር አጣርቶ የማያዳግም ውሳኔን
መስጠት እንጂ ስህተትን በስህተት የማረምን
መንገድ አንመርጥም፡፡ ወደ 17 ሊያድግ ነው
ሲባል ምን ማለት ነው? ከምን መነሻነትስ?
የክለቦችን ቁጥር በየአመቱ እንደተፈለገው
የሚጨመርና የሚቀነስ ነገር አይደለም፡፡
የክለቦች ቁጥር ይደግ ቢባል እንኳን ከፍተኛ
ጥናት ተደርጎበት፣በቴክኒክ ሙያተኞች
ታይቶ ታምኖበት፣ከዓለም አቀፍ መርህ
ጋር ተነፃፅሮ እንጂ ለማቻቻል ሲባል የክለቦች
ቁጥር አያድግም፤ እንዲህ ማድረግም ተገቢ
አሰራር አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ
ጥናቶች እየተሰሩ ነው፤ ነገር ገን አሁን
ባለንበት ሁኔታ ወይም የተፈጠረውን ችግር
ተከትሎ የክለቦችን ቁጥር የሚያስጨምር
አንዳችም መሰረታዊ ምክንያት የለም፡፡
ሀትሪክ፡- በማጣራት ሂደቱ በተገኘው
ውጤት መሰረት መረጃዎች ከተገኙ
ፌዴሬሽኑ ምን አይነት ውሳኔዎችን እስከምን
ድረስ ይወስዳል ብሎ መገመት ይቻላል?
አቶ ወንድምኩን፡- ይሄ የጨዋታ
ማጭበርበር (match fixing) የእግር ኳስ
እድገታችን ነቀርሳ በመሆኑ ብዙ ትርጉም
ወይም መልዕክት የሚያስተላልፍ የማያዳግም
ውሳኔ ሊወስድ እንደሚችል ነው የምገምተው፡
፡ በኢትዮጵያ እግር ከኳስ ውስጥ ለብዙ
አመታት ውጤት የማስለወጥ (match
fixing) እንቅሰቃሴዎች እንደነበሩ ይሰማል፤
ነገር ግን ተጨባጭ ነገሮች ስላልተገኙ ምንም
የተወሰደ አስተማሪ እርምጃ የለም፡፡ አሁን
ግን የጨዋታ ማጭበርበር (match fixing)
በተመለከቱ የሚሸቱ ነገሮች በመኖራቸውና
ይሄንን ለማጋለጥ ደፍረው የመጡ ሰዎችና
አካላት በመኖራቸው ምክንያት ይሄ ጉዳይ
በጥብቅ ተይዟል፡፡ መረጃዎች ከተጠናቀቁ
በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤን ሳይሆን
ውድቀቱን የሚያፋጥኑ ነገሮች ተሰርተው
ከሆነ ከተገኙ የማያዳግም ትምህርት
የሚሆን እርምጃ ፌደሬሽኑ ከመውሰድ ወደ
ኋላ እንደማይል ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፤
በዲሲፕሊን ኮሚቴው ከዚያ በስራ አስፈፃሚ
ኮሚቴው ከታየ በኋላ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ
ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- እንደተባለው ፌዴሬሽኑ
የመወሰን አቅሙ ካለው የወረደው ጅማ
አባቡና በሊጉ እንዲቆይ፤ ያልወረደውን ቡድን
ደግሞ እስከማውረድ የሚያደርስ ወይም
የነጥብ ቅነሳና የእገዳ ውሳኔ ሊተላለፍ ይችላል
ብሉ ማሰብስ ይቻላል?
አቶ ወንድምኩን፡- ነገሮች በማጣራት
ስራ ላይ እያሉ እንዲህ ያደረጋል የሚል
መልስ ይሰጠኛል ብለህ እንዳታስብ፤ እንደዚህ
አይነት ምላሽ ለመስጠትም ጊዜው ገና ነው፡፡
የማጣራት ሂደቱ ከተፈፀመ በኋላ የሚሆነውን
በትዕግስት ማየት ነው የሚሻለው፤ ከዚህ
ውጭ ጅማ አባቡና ይወርዳል፤ አይወርድም
ብሎ ለመናገር ገና በጠዋት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ
ፌዴሬሽን በቅርቡ አሰልጣኞች ወደ ሞሮኮ
ተጉዘው ስልጠና የሚያገኙበት እድል
ማመቻቸቱ የሚደነቅ ነው፤ ነገር ግን
ስልጠናው በካፍና በፊፋ የስልጠና ማንዋል
ውስጥ ያልታቀፈና እውቅና የሌለው ነው
በሚል ብዙዎች ስልጠናውን ይተቻሉ፤ በዚህ
ላይ አንተ ምን ትላለህ?
አቶ ወንድምኩን፡- ይሄ ስልጠና የካፍ
ከፍተኛ የቴክኒክ ባለሙያዎች ኃላፊዎች
በሚገባ የሚያውቁት ነው፤ ስለ ስልጠናው
በቂ እውቀት አላቸው፡፡ የሞሮኮ የስልጠና
ማዕከልም በአውሮፓ ደረጃ የሚወዳደር
ትልቅ ማዕከል እንደሆነም በሚገባ ያውቃሉ
ሰለዚህ እኛ ዞሮ ዞሮ አሰልጣኛቻችን ተጨማሪ
የሚዲያ ማሻሻያ ግብአት እንዲያገኙ ነው
ሃሳባችን፡፡
ሀትሪክ፡- እኔ በጥያቄ እያነሳሁ ያለሁት
ሃሳቡ የተቀደሰ ነው፤ግን የአለም አቀፍና
የአህጉሪቱ እግር ኳስ እውቅና የሌለው ስልጠና
ከሆነ ጥቅሙ ምንድነው የሚለው ነው?
አቶ ወንድምኩን፡- እኛ ባለን መረጃ
መሰረት ከዚያም ያገኘናቸው መረጃዎች
እንደሚጠቁሙን የተሻለ ስልጠና
ማግኘታቸውን ነው፤ አሰልጣኞቹንም
ስለጥቅምና ጉዳቱ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ይ ሄ
ስልጠና ደረጃቸውን የማይመጥን ሆኖ ከተገኘ
እኛ ኃላፊነቱን እንወስዳለን፤ እሰካሁን ባለን
መረጃ መሰረት ይሄ ስልጠና በካፍ የሚታወቅ
ከፍተኛ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መሆኑንና
በአውሮፓ ደረጃ በሚመደብ ሁሉን ነገር
ባሟላ የስልጠና ማዕከል ውስጥ እንደሚሰጥ
ነው፤ ሞሮኮ በአፍሪካ ያላት ደረጃ ይታወቃል፤
አካዳሚዎቿ፣ የስልጠና ማዕከሎቿ በአውሮፓ
ደረጃ የሚመደቡ ናቸው፡፡ በእኛ በኩል
ከስልጠናው በዘለለ አብሮ ተባብሮ መሰራት
የሚቻልበትን ዕድል ከመፍጠሩ አንፃር እንደ
ጥሩ ጅምር ሊታይ ይችላል እንጂ የካፍና
የፊፋ እውቅና አልተሰጠውም ብሉ ዝቅ
ማድረግ ተገቢ ነው አልልም፡፡
ሀትሪክ፡- የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ
ፕሪምዬር ሊግ መቼ ይጀመራል…? ቁርጥ
ያለ ምላሽ ስጠኝ?
አቶ ወንድምኩን፡-አሁን ባለው ሁኔታ
የሚጀመርበትን ትክክለኛውን ቀን ለመናገር
ሁኔታዎች አስቸጋሪ አድርገውብናል፤በተለይ
የወቅቱ የተፈጥሮ ሁኔታ ማለትም ዝናቡ
የመጫወቻ ሜዳዎችን በጥሩ ሁኔታ
ለውድድር ዝግጁ ለማድረግ አስቸጋሪ
አድርጎብናል፡፡ የክልሉቹን ተወውና የአዲስ
አበባ ስቴዲየምን ለውድድር ብቁና ምቹ
ለማድረግ፣ ለማስተካከል የሚወስደው ጊዜ
ውድድሩ የሚጀመርበትን ቀን ይወስነዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ክለቦች በቅድመ-ዝግጅት(preseason) ላይ ቢገኙም ዝግጅታቸውን
በፕሪምየር ሊጉ መርሃ ግብሩ መሰረት
ለማከናወን እንደተቸገሩ ይናገራሉ፤ የሜዳውስ
ይሁን የውድድሩ ፕሮግራምስ (Fixtuer) መቼ
ይወጣል?
አቶ ወንድምኩን፡- የፕሪምየር ሊጉ
ጨዋታ ከመጀመሩ ቢያንስ ከ20 እና ከ25 ቀን
በፊት ይወጣል፡፡
ሀትሪክ፡- የኮከብ ተጨዋች ምርጫን
በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት
ኮርፖሬሽን(EBC) ጋር ውዝግብ ነበራችሁ
(EBC) እሁድ ምሽት በሽራተን አዲስ ኮከብ
ተጨዋቾችን የመረጠው ልዩነታችሁ ተፈቶ
ነው?
አቶ ወንድምኩን፡- ከኢትዮጵያ ብሮ
ድካስት ኮርፖሬሽን(EBC) ጋር ያለን ልዩነት
አልተፈታም፤ ከጣቢያው ጋር የማርኬቲንግ፣
የብሮድካስት ጉዳይም ገና ያለየለት ነው፤
በአዲሱ አመት ሁሉም ነገር ይለይለታል ብለን
እንጠብቃለን፡፡ በተቻለን መጠን እኛም እንደ
ተቋም መብታችንን ለማስከበር እንጥራለን፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
ከተጠናቀቀ ወራቶች ተቆጥረዋል፤ ሌላ ተቋም
ሲሸልም ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከተው እግር
ኳስ ፌዴሬሽን እስካሁን ለኮኮቦች ሽልማትና
እውቅና አልሰጠም፡፡ የኮከብ ተጫዋቾችን
ምርጫን ሳታደርጉ ወደ አዲሱ አመት
ውድድር ልትገቡ ነው? ወይስ ሽልማቱ
ታጠፈ…?
አቶ ወንድምኩን፡- የተለያዩ ችግሮች
ነበሩብን፤ በተለይ በአጭር የፅሁፍ
መልዕክት ድምፅ የማሰባሰቡ ስራ ላይ
ችግሮች ተፈጥረውብን ቆይተዋል፡፡ በዚህ
በኩል በተለይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት
ኮርፖሬሽን(EBC) በተመሳሳይ ያለውን
የሚዲያውን ኃይል ተጠቅሞ በፅሁፍ
መልዕክት ድምፅ ማሰባሰቡ የእኛን ድምፅ
የማሰባሰብ ስራን አቀዝቅዞብናል፤አሁን
የእነሱ ስለተጠናቀቀ በቀጣይ የምንሄድበትና
ምርጫውን የምናከናውን ነው የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ
ብሮድካስት ኮርፖሬሽን(EBC) የኮቦችን
ምርጫን እንዴት ያየዋል? ለሽልማቱስ
እውቅና ይሰጣል…?
አቶ ወንድምኩን፡- በእኛ በኩል እውቅና
የምንሰጥበት ሁኔታ የለም፤ ከእኛ ጋር
የሚያገናኘው ነገርም የለም።
ሀትሪክ፡-በመጨረሻ የምትለው ካለ…?
አቶ ወንድምኩን፡- ፌዴሬሽናችን በዚህ
አመት በርካታ ውድድሮችን አከናውኗል፤
ትላልቅ ስራዎችን ሲሰራም ቆይታል፤
ውድድሮቻችንም እየሰፉ መጥተዋል፤ አለም
አቀፍ ግንኙነተችንም ተጠናክሯል፡፡ ይሄንን
አጠናክረን ለመቀጠል ሁሉም የስፖርት
ቤተሰብ መረባረብ ይኖርበታል፡፡ ክለቦችን
ከመፍረስ መታደግ ያሰፈልጋል፡፡ በአገር
ደረጃ የስፖርት ካውንስል ተቋቁሞ ኃላፊነቱን
የሚወስድበት ስፖርቱም በትክክለኛው
አቅጣጫ እንዲሄድ ድጋፍ እንዲያደርግ ነው
መልዕክቴ፤ ከዚህ ውጭ በአዲሱ አመት
መልካም የውድድር ዘመን እንዲሆነ ነው
ምኞቴ፡፡