THE BIG INTERVIEW WITH MICHO
ኢትዮጵያ በዲኤንኤዬ (DNA) ውስጥ ነች ይላሉ ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ፤ ይህን ጥልቅ ፍቅራቸውን ኢትዮጵያዊ በማግባት ጭምር በትዳር አስረውታል፡፡ የፈረንጆቹን ሚሊኒየም መግባት ተከትለው በ1994 ዓ.ም. ወደአፍሪካ መጡ ከዛ በኋላ ግን እውነትም ጨክነው መውጣት ሳይችሉ 19 ዓመታትን አስቆጠሩ፡፡ በምስራቅ፣ በደቡብና በሰሜን አፍሪካ ሰርተዋል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ አልሰሩም ለዚህም ፈረንሳይኛ ቋንቋ አለመቻላቸውን በምክንያትነት ያቀርባሉ፡፡ ፈረንሳይኛ ቋንቋ አለመቻሌ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ እንዳላገኝ አድርጎኛል ይላሉ፡፡ የእግር ኳስ ሜዳ ብቻ ሳይሆን የንግግርም ተሰጥኦ እንዳላቸው ያየነው ለዚህ ቃለምልልስ በተገናኘንበት ወቅት ነው፡፡ የዛሬው ታላቅ እንግዳችን ሚሉቲን ስሬዶዬቪች ሚቾ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ሆነው ከተሾመ ፋንታሁን ጋር በሸራተን አዲስ ሆቴል ስለ 19 ዓመታት የአፍሪካ ቆይታቸው በጥልቀት አውርተዋል፤ መልካም ንባብ፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በመጀመሪያ እጅግ ከተጣበበው ሰዓትዎ ላይ (ይህንን ቃለመጠይቅ እያደረጉ እንኳ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በዋትስአፕ በድምጽና ስልክና በአጭር መልዕክት ውይይት ያደርጉ ነበር) ይህን ቃለመጠይቅ ለማድረግ ፍቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡
ሚሉቲን ሚቾ፡ እኔም ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያ ቃለ-ምልልሴ ነውና ለሰጣችሁኝ ዕድል በጣም አመሰግናለው፡፡
- ማሰታውቂያ -
ሃትሪክ ስፖርት፡ ጥያቄአችንን ስለአስተዳደግዎ በማውራት ብንጀምርስ፤ የልጅነት ዘመንዎ አስቸጋሪ ወቅት ላይ በነበረችው ዩጎዝላቪያ ምን ይመስል ነበር፤ ከዛ አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር እንዴት ወደኳስ ሊገቡ ቻሉ?
ሚሉቲን ሚቾ፡ የተወለድኩት ልክ የዛሬ ሃምሳ ዓመት በ1961 ዓ.ም. በወቅቱ የዩጎዝላቪያ ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ትባል በነበረችው ሃገር ውስጥ በደቡብ ምስራቅ ሰርቢያ በምትገኝ ፕሮኩፕሌ በምትባል መንደር ነው፡፡ የሰርቢያ ታላላቅ የጦር ጀግኖችና መሪዎች ሁሉ የተገኙት ከዚች መንደር ነው፡፡ በአንደኛው ጦርነት ወቅት ታላላቅ ገድላትን የፈጸሙ ታላላቅ ሰዎች ሁሉ የተገኙት ከዚህች ከኔዋ መንደር ነው፡፡ የኔም አያት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ታላቅ ገድል የፈጸመ ጦረኛ ነበር፤ ሚሉቲን የሚለውንም ስም ያገኘሁት ከሱ ነው፡፡ ሚሉቲን የሱ ስም ነው፡፡ እግር ኳስን የጀመርኩት በሰሜን ስላቪያ በሊዩብሊያና ነው፤ ትምህርቴንም የተከታተልኩት በዛው ነው፡፡ ወቅቱ ዩጎዝላቪያ ልትበታተን የቀረበችበት ወቅት ነበርና በዛን ወቅት ለነበርነው ልጆች ጥሩ ወቅት አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበረችው ዩጎዝላቪያ በስምምነት ስትበታተን እኔ ግጭቱ የሃይማኖት ነው ብዬ ነው የማምነው ምክንያቱን፤ በኦርቶዶክስ፣ በእስልምናና በካቶሊክ መካከል የነበረ አለመደማመጥ ሃገሪቱን ለመከፋፈል፣ ዜጎቿን ደግሞ ለስደት፣ ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጓት አልፏል፡፡ እኔ በርግጥ ከኔቶ የቦንብ ጥቃት በስተቀር በቀጥታ የጦርነቱ ተሳታፊ አልነበርኩም ነገር ግን እንደማንኛውም የሃገሪቱ ዜጋ የገፈቱ ቀማሽ ከመሆን አላመለጥኩም፡፡ አሁን የትም ሃገር ተመሳሳይ የብሄር፣ የሃይማኖትና የጎሳ ግጭት ሳይ ያንን ሃገሬ ያለፈችበት ዘመን አስታውስና በጣም አዝናለው፣ የሞተው ሰው፣ የጠፋው ንብረትና የተሰደደው ዜጋ ያሳዝነኛል፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ወደእግር ኳስ እንዴትና መቼ ገቡ?
ሚሉቲን ሚቾ፡ እግር ኳስን የጀመርኩት በስሎቬንያ ነው ከዛም ወደቤልግሬድ ሄድኩ ከዛም ወደ ስፓርታክ ሱቦቲች ከተዛወርኩ በኋላ ብዙም ሳልቆይ የቀኝ እግር ጉልበቴ ላይ በደረሰብኝ ከባድ ጉዳት ምክንያት በጊዜ ኳስ አቆምኩና ወደዩኒቨርሲቲ ተመልሼ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት በእግር ኳስ ሥልጠና ላይ አተኩሬ ተከታተልኩ አስፈላጊውን የስልጠና ፍቃድ ሁሉ ካሟላው በኋላ ወደስልጠናው ገባው ማለት ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በተጫዋችነትዎ ወቅት የሚጫወቱት በየትኛው ቦታ ነበር የሚጫወቱት?
ሚሉቲን ሚቾ፡ እንደንጎሎ ካንቴ ዓይነት ሮጦ የምይጠግብ ታታሪ የተከላካይ አማካይ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ በኛ ሃገር የተከላካይ አማካይ ተጫዋች ሚናን የምንረዳበት መንገድ የተቃራኒ ቡድንን ጨዋታ ማበላሸት (Destroying) ሳይሆን በጥልቀት እየገባ ጨዋታ የሚያቀናብርና ከኋላ ጀምሮ የቡድን ጨዋታን የሚያደራጅ ተጫዋች ነው (Deep playing playe maker building from behind )ለዛም ነው ስሎቫኒያ በወቅቱ የአውሮፓ ብራዚል (Brazil of Europe) ትባል የነበረው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ወደአሰልጣኝት ከገቡ በኋላ በሰርቢያ የነበርዎት የአሰልጣኝነት ገድል ምን ይመስላል?
ሚሉቲን ሚቾ፡ ዩጎዝላቪያ ከመፈራረሷ በፊት ፓሊች በምትባል ስፍራ የዩጎዝላቪያ የእግር ኳስ አዳሪ ትምህርት ቤት ከፍተን ነበር፡፡ ዓላማው ልጆቻችን ስለጦርነት እንዳያስቡና በየመንገዱ ለጦርነት ጥሪ ጆሮ እንዳይሰጡብን በማሰብ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ከ10፣000 በላይ ህጻናት ነበሩት የዚህ ሃገራዊ ፕሮጅክት አባል ሆኜ ለሰራውት ሥራ አሁንም ድረስ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በመጨረሻም ከዚህ ስብስብ ውስጥ 25 ልጆችን መርጬ ከሃያ ዓመት በታች የዩጎዝላቪያን ቡድን አሰልጥኛለው ሁሉም የዚህ ቡድን አባላት በተለያዩ ሃገራት ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ሆነው አልፈዋል፡፡ በዚህ ሙያ ውስጥ ከሰራዋቸው የምኮራባቸው ሥራዎች አንዱ በዚህ ወቅት የሰራውት ሥራ ነው፡፡ ለማሰብ እንኳን ይከብዳል ነገር ግን የዩጎዝላቪያ ሻምፒዮ የሆነ ቡድን መሥራት ችለን ነበር፡፡ ይህን ውጤት ያየ በወቅቱ የፈረንሳይ ዓለም ዓቀፍ ራዲዮ ጋዜጠኛ የነበረ ዡሊዮ ካዳሜሪ የተባለ ኡጋንዳዊ ዘገባ ከመስራት ባሻገር የዩጋንዳው ቪላ ክለብ ዋና ጸኃፊ ከነበሩት ጆን ኬቪን አሂሮ ጋር አስተዋወቀን አሳቸውም ወደዩጋንዳው ቡድን ቪላ አመጡኝ፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ አፍሪካስ በምን ሁኔታ ተቀበለችዎት?
ሚሉቲን ሚቾ፡ አንድ ሰው ወደአፍሪካ ለሥራ ሲመጣ አቅዶና አስቦ ነው የሚመጣው፡፡ ያለውን ትግል፣ ጀብድና ውጤት ሁሉ አቅዶ መምጣት አለበት፡፡ በተለይ እግር ኳስ ብዙ ሃብት የሚፈስበት ትልቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ታላቅ ዝግጅት ይጠይቃል፡፡ በሁሉም የዓለም ክፍል እግር ኳስ ብዙዎች የሚወዱት፣ የሚፈቀር ስፖርት ነው አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ይበልጥ የሚወደድ ስፖርት ነው፡፡ ይህ ቫይረስ ለክፎኝ ነው ከአፍሪካ እግር ኳስ ጋር በፍቅር ወድቄ እንድቀር ያደረገኝ፡፡ ዛሬ ላይ ከ19 ዓመታት በኋላ ከ200 በላይ ተጫዋቾች በኔ ምክንያት ህይወታቸው ተቀይሮ ሳይ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡
አፍሪካ በወቅቱ አዲስ ተግዳሮት ነበር ስለዚህ ለራሴ እንዲህ ብዬ ነገርኩት “ሚቾ በጦርነት ከፈራረሰች ሃገር ነው የመጣኸው ስለዚህ በምንም ነገር እንዳትደነቅ፡፡” እኔ ከምዕራብ አውሮፓ ሃብታም ሃገራት እንደመጡት አውሮፓውያን ከትዕቢት ጋር አይደለም የመጣሁት፡፡ እኔ ወደአፍሪካ የመጣሁት ያለኝን ሰጥቼ አፍሪካ የምትሰጠኝን በክፍት ልብ (Open Heart) ለመቀበል አፍሪካ ያላትን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ በማክበር ለመከበር ስለነበር ሃገሬን በልቤ (My country in my heart) ዕውቀቴን በጭንቅላቴ (My knowledge in my head) ይዤ ከከለሬ ውጭ (under my skin) አፍሪካውያን ከሆኑት በላይ አፍሪካዊ (To be an African more than Africans) መሆን አለብኝ ስል ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ የኔ የስኬት ምስጢር ሆኖ እስከዛሬ ድረስ የረዳኝ ይሄ ነው፣ በአንድ ወቅት አንድ ጥናት አይቼ ነበር እናም 78 አውሮጳውያን አሰልጣኞች ወደአፍሪካ መጥተው ተመልሰዋል ዛሬ ላይ ማንም አያስታውሳቸውም እኔ ግን ይኸው ከመጣው ጀምሬ አስራ ዘጠነኛ ዓመቴን ያዝኩ፤ አፍሪካ የህይወቴ አንድ አካል ሆናለች፣ አፍሪካ በዲኤንኤዬ ውስጥ ነች፡፡ አስራ ዘጠኝ ዓመታት ያለመዋዠቅ በሄድኩበት ሁሉ ከ60% በላይ የማሸነፍ ንጻሬ (Ratio) ያለው አሰልጣኝ ለመሆን የበቃሁት በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በመጡበት ዓመት በቪላ ክለብ ታላቅ ገድል ነው የፈጸሙት ሚስጥሩ ምን ይሆን?
በሶስት ዓመታት ከ78 ጨዋታዎች የተሸነፍኩት በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው፡፡ ቁልፉ መሠጠትና ቁርጠኝነት ነው አብረውኝ ሰሩትን በሙሉ ከልብ አመሰግናለው ተጫዋቾቼ፣ አሰልጣኞች፣ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለው በኋላም ወደጊዮርጊስ ይዤው የመጣሁት ግብ ጠባቂው ዴኒስ ኦንያንጎ የዚህ ቡድን ውጤት ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ሶስት ተከታታይ ዓመታት ሶስት ዋንጫ፣ አንድ የሃገሪቱን የጥሎማለፍ ዋንጫ ዓመቱን ሙሉ አንድ ሽንፈት ብቻ ከዚህ ሁሉ ውጤት በላይ ምን ፈልገው ለቀቁ በዛ ላይ ጁላይ 18፣ 2004 አ.ኤ.አ. መልቀቂያ አስገብተው ጁላይ 19፣ 2004 አ.ኤ.አ. የጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ ድርድሩ ሥራ ላይ እንዳሉ ነበርና ይህ ለቪላ ክህደት አይደለም?
ለስምንት ወራት ደሞዝ አልሰጡኝም ነበር፣ ይሁን እንጂ ከሜዳ ውጭ አንድም ጨዋታ አልተሸነፍንም ነበር፡፡ ደሞዜን እንዲከፍሉኝ በቂ ጊዜ ሰጠዋቸው ነገር ግን አልሆነም፡፡ የመጀመሪያውን ዓመት በነበሩት ልጆች ጨረስን ሁለተኛው ዓመት ላይ ከኮካ ላይ የታዳጊዎች ሻምፒዮን ዴኒስ ኦንያንጎና ኢማኑኤል ኦኩኒን ጨምሮ 18 ታዳጊዎችን መልምለን እስከብሔራዊ ቡድን ድረስ የደረሱ ዩጋንዳዊያን ከዋክብትን ማፍራት ችለናል፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በጊዮርጊስ ቤትስ የነበርዎት የመጀመሪያ ቀናት እንዴት ነበሩ?
ኢትዮጵያ የተለየ ልምድ የቀሰምኩባት ሃገር ናት፡፡ ከዩጋንዳ በጣም የተለየች ሃገር ነበረች፤ በመጀመሪያዎቹ ቀናት የባህል መጣረስ ገጥሞኛል ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ብቸኛ አፍሪካዊት ሃገር በመሆኗ የራሱ ኩራት ያለው ኩሩ ሕዝብ ሃገር ናት፡፡ ሕይወት በየትኛው መንገድ እንደምትወስድህ አታውቅማና እኔንም በተለይ በ1996/97 እና 1997/98 ወደሩዋንዳ ሴካፋ ከተሳተፈው ቡድን ጋር አብሬ ከሰራዋቸው ሰዎች ከተጫዋች ጀምሮ እሰከአስተዳደርና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ድረስ በሙሉ የተከበሩ ሰዎች ጋር አምጥታ ቀላቀለችኝ፡፡ 1997 ነሐሴና መስከረም በቀን እስከ 7 ሰዓታት እንሰራ ነበር፡፡ ያ ትውልድ የአረብ ሃገራት ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የነበረውን ኢኤንኤንፒአይ፣ የጋናውን ኸርትስ ኦቭ ኦክ ማሸነፍ የቻለ ታሪካዊ ቡድን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን በቴክኒክ የላቁ፣ ለስኬት ከሥራ ውጭ አቋራጭ መንገድ እንደሌለው የተረዱ ተጫዋቾች አሏት እሱን በአካል ብቃትና በታክቲክ አዘጋጅቶ ማቅረብ ነበር የኛ ሥራ፣ ለሁለት ዓመታት በሚገባ ስናደር የነበረውም እሱን ነው፡፡ እኔ የመጣውበት ወቅት ጊዮርጊስ በሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ ነበረበት ስለነበር ተጫዋቾችቹም ድል ተርበው ነበር አስተዳደሩም የጠየቅነውን ሁሉ ያደረግልን ነበር፡፡ ከዛ በተጨማሪ እንደዳኛቸው ደምሴ ዓይነት ሰው በአሰልጣኝ ቡድን ውስጥ ካለህ በጣም እድለኛ ነህ፡፡ ዳኛቸው በጣም የተለየ ሰው ነው፡፡ እስከዛሬም ድረስ ወንድሜና ጓደኛዬ ነው፡፡ አሁንም ቤተሰብ ነን ይህ የሆነው ከሱ ቅንነት የተነሳ ነው፡፡ ዳኛቸው በኔ ልብ ውስጥ የተለየ ሥፍራ አለው፡፡ እንደተጫዋች ጊዮርጊስ ውስጥ ብዙ ገድል መጻፍ የቻለ ጀግና እግር ኳሰኛ ነው፡፡ እንደአሰልጣኝ ደግሞ በዛን ወቅት የተሰራው ሥራ ሁሉ ያለሱ ሊሰራ አይችልም ነበር፡፡ የሰራነውን ሁሉ የሰራነው እንደወንድም እንደጓደኛ መክረን ተስማምተን ነው፡፡ እንደሰው በደግና በክፉ ጊዜ አብረውህ የሚሆኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሰልጣኝ ስትሆን ደግሞ በምታሸንፍበት ወቅት ሁሉም አብሮህ ነው ስትሸነፍ ግን አብሮህ የሚሆነው እንደዳኛቸው ዓይነት የእግር ኳስ ምንነት የገባቸው በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ መቼም ዳኛቸውን አመስግኜ መጨረስ የምችል አይመስለኝም (I cannot thank Dagnachew enough)፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከዛም የሃገርዎትን ልጅ ኮስታ ፓፒችን ተክተው ወደኦርላንዶ ፓይሬትስ አመሩ ምናልባት የሄዱት በፓፒች ጥቆማ (Recommendation) ነው?
በፍጹም እሱ ቃለምልልስ (Job Interview) እስከዛሬ ካደረኳቸው የሥራ ቃለ-ምልልሶች ሁሉ በጣም ከባዱ ነው፡፡ ከክለቡ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አይቪን ንኮዛ ጋር ነበር ቃለምልልሱን ያረኩት፤ በወቅቱ እነካሉሻ ብዋሊያ፣ ኋላ ላይ አውስትራሊያና የኮሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ የነበረው ኪቭ ቬርዲክን የመሳሰሉ ተቀናቃኞች አብረውኝ ነበሩ፡፡ ሁሉንም አሸንፌ እግር ኳስን በጥልቀት በመተንተን ብቃቴ፣ የደቡብ አፍሪካን የክለቡን ታሪክ የመረዳት ችሎታዬ ታምኖብኝ ነው የተቀጠርኩት እንጂ በፍጹም በኮስታ ጥቆማ አልነበረም፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ፓፒች በኢትዮጵያ ተቀጥረው ሁለት ሳምንት እንኳን ሳይሞላቸው ጠፍተው መሄዳቸውን ያውቃሉ?
አውቃለው እኔም ነኝ ወደዚህ እንዲመጣ ያገናኘሁት በደንብ እንተዋወቃለን ነገር ግን በባህሪ እንለያያለን፡፡ እኔ ወደአንድ ሃገር ስሄድ ያለኝን ስታንዳርድ ይዤ ሳይሆን የሃገሪቱን ህዝብ መስዬ ነው፡፡ በኔ ስታንዳርድ ሰውን አልለካም በነሱ ስታንዳርደ ነው ተመሳስዬ የምኖረው፡፡ የኔና የኮስታ ልዩነት ይሄ ነው
ሃትሪክ ስፖርት፡ ወደጊርጊስ ሲመጡ ዴኒስ ኦንያንጎን ከቪላ ይዘው መጡ ከኢትዮጵያ ደግሞ ወደኦርላንዶ ፓይሬትስ ሲሄዱ ፍቅሩን ይዘው ሄዱ?
100 ፍቅሩ አዳማ እየተጫወተ የታክሲ አሽከርካሪ ነበር፡፡ ወደጊዮርጊስ ሲመጣ ደግሞ በቡናና በጊዮርጊስ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በመጨረሻም ጊዮርጊስ አሸንፎ ለሁለት ዓመታት ተጫወተ በወቅቱ ከሳሚባጆፔ፣ አብራሃም ኩዲሞሬ እና ሙሉዓለም ረጋሳ ፊት ወታደር ነበር፡፡ በዛን ወቅት ቅድም የገለጽኩልህ ታታሪ ቡድን ውጤት ነበር፡፡ ወደኦርላንዶ ፓይሬትስ ስሄድ ይዤው ሄድኩ በዛም እጅግ የተከበረ ተጫዋች ሆኖ ነው ያሳለፈው፣ ለኦርላንዶ፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድና ቢድቬትዝ ዊትዝን የመሳሰሉ ታላላቅ ክለቦች ተጫውቷል ከሱፐር ስፖርት ጋር 3 ዋንጫ አንስቷል፡፡ አንድ ወቅት ላይ ጠፍቶብኝ ነበር ከዛም ብዙ ክለቦችና ሃገራት ውስጥ ተዟዙሮ ሲጫወት እንደቆየ ሰማው በድጋሚ ወደፓይሬትዝ ስሄድ ተገናኘን እሱ አሁንም እዛ ነው የሚኖረው እናም ምን ያህል ሃገሪቱ እንደተስማማችው መገመት ትችላለህ
ሃትሪክ ስፖርት፡ በጊዮርጊስ አብረው ከሰሯቸው ተጫዋቾጭ የተለየ ችሎታ አላቸው የሚሏቸው ተጫዋቾች አሉ?
ከግብ ጠባቂው ደያስ አዱኛ ጀምረህ እስከ የፊት አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ድረስ ሁሉንም አሁን እስከአባታቸው ስም በስም ልጠራልህ እችላለው ሁሉም ለቡድኑ አስፈላጊ ነበሩ፡፡ እኔ በነገርህ ላይ ተጫዋቾችን የሚያሰለጥን ብቻ ሳይሆን ከልብ የሚወድ አሰልጣኝ ነኝ አሁን ድረስ ከተጫዋቾጬ ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያለኝ፡፡ በሄድኩበት ሁሉ ቪላ መጀመሪያ ስመጣ የቡድኑ አምበል የነበረው ተጫዋች ነው ኋላ ላይ ስልጣን ሲይዝ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረኝ፡፡ በኦርላንዶ ፓይሬትስ የመጀመሪያ የመጫወት ዕድል የሰጠውት ሃፒ ጄሌ እስካሁን ድረስ የቡድኑ አምበል ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. በዘራፊዎች የተገደለው ሴንዞ መዪዋ ሕይወቱ ባያልፍ ኑሮ አሁን ድረስ የደቡብ አፍሪካ ቡድን ዋና በረኛ የሚሆነው እሱ ነበር እናም ለኔ ሁሉም ተጫዋች እኩል ነው፡፡ እግር ኳስ ሰጥቶ የመቀበል ጉዳይ ነው፡፡ ለተጫዋቾቼ ልቤን እሰጣቸውና እነሱ ነፍሳቸውን ለክለባቸው እንዲሰጡ ነው የማደርጋቸው፡፡”I will give them my heart and I take their soul forbthe team.”
ሃትሪክ ስፖርት፡ ሴንዞ መዪዋ ማነው?
ሴንዞ መዪዋ ከደርባን የተገኘ ህይወቱን ለመቀየር ተፍ ተፍ የሚል ምስኪን ታዳጊ ነበር፡፡ እኔ ነኝ በመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታዬ ዕድል የሰጠውት ኋላ ላይ ግን የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ መሆን ችሎ ነበር፤ በህይወት ቢኖር ደግሞ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ሃፒ ጄሌም እንደዛው ነው የመጀመሪያ የመጫወት ዕድል ያገኘው በኔ ነው ነገር ግን እስካሁን ድረስ ለ14 ዓመታት ወሳኝ ተጫዋች ሆኖ ከክለቡ ጋር አለ፡፡ የቡድኑ አምበልም እሱ ነው ለነዚህ ሁለት ልጆች የተለየ ፍቅር አለኝ፡፡
እስኪ ማንም ልብ ብሎት የማያውቀውን አንድ ሚስጥር ልንገርህ በ3 አፍሪካ ዋንጫዎች በ2012፣ በ2013 እና በ2017 የሆነ ነው፡፡ በ2002 ወደአልሂላል ስሄድ አህመድ መሃመድ ቢሻ የተባለ ተጫዋች የመጀመሪያ የመጫወት ዕድል የሰጠውት እኔ ነኝ፤ ኋላ ላይ ግን በ2004ቱ የኢኳቶሪያል ጊኒ የአፍሪካ ዋንጫ ለሃገሩ ሱዳን ከ36 ዓመታት በኋላ ጎል አስቆጠረ፡፡ አዳነ ግርማ እኔ ወደጊዮርጊስ ከመምጣቴ በፊት ተከላካይ ነበር እኔ ነኝ ከዳኛቸው ጋር ተነጋግረን ወደአጥቂነት የቀየርኩት፡፡ አዳነ ግርማ ገዳይ አጥቂ ከመሆን አልፎ በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ለሃገሩ ከ31 ዓመታት በኋላ ጎል ያስቆጠረው አዳነ ነው፡፡ ዩጋንዳ ውስጥ ደግሞ ፋሩክ ሚያ ተማሪ ነበር እኔ ወደብሔራዊ ቡድን ስጠራው፡፡ ከትምህርት ቤት ነው ወደብሔራዊ ቡድን የጠራውት ፋሩክ ደግሞ ሃገሩ ዩጋንዳ ከ39 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ግብ ስታስቆጥር የተቆጠረው በፋሩክ ነው፡፡ ኢኩቹ ካሱንጎ የተባለ የኮንጎ ዜግነት የነበረው ስደተኛ የቪላ ክለብ ኳስ አቀባይ (Ball Boy) ሆኖ ተቀጥሮ ይሰራ ነበር፡፡ ሰውነቱ (Physical) ያምራል አንድ ቀን ጠራውትና ኳስ መጫወት ትፈልጋለህ? አልኩት አዎ አለኝ ቀይርና ግባ አልኩት በሶስት ወራት ውስጥ የተለየ አጥቂ ሆኖ የሴካፋ የክለቦች ውድድር እንድናሸንፍ ረድቶናል፡፡ ኢኩቹ ኋላ ላይ ዜግነቱን ሁሉ ቀይሮ በዩጋንዳ ፓስፖርት ለዩጋንዳ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ አውሮፓ የመጫወት ዕድል አግኝኖ እንደሄደ ፓስፖርቱንም ዜግነቱንም ትቶ በሄደበት ቀረ እንጂ በጣም ታሪካዊ ተጫዋች ነበር፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከዛ ወደያንግ አፍሪካ
እዛም የነበረኝ ጊዜ እጅግ አስደሳች ነገር ግን በጣም አጭር ነበር፡፡ ለምን መሰለህ ትቼ የወጣውት ህዝቡ በጣም በአስማት (Magic) ያምናል፡፡ እኔ በእግዚአብሔር፣ ከእግዚአብሔር በታች ደግሞ በሥራ ብቻ የማምን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነኝ፡፡ በያንግ አፍሪካ እኔ ከወጣው በኋላ ሶስት ዋንጫዎችን ማሸነፍ የቻለ ትልቅ ቡድን መሥራት ችያለው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ተመልሰው ወደፈረሰኞች ቤት ተመለሱ ሁለተኛው ማንዴት ምን ይመስላል?
ከሳለሃዲንና ከአዳነ በስተቀር አብዛኞቹ ተጫዋቾች ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ ከ1999 እስከ 2002 ዓ.ም. በክለቦችና በአቶ አሸብር በሚመራው ፌዴሬሽን መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ነበር፡፡ ይህ ውዝግብ ሃገሪቱ የዓለም ዓቀፍ ውድድሮችን ጭምር እንዳትጫወት በፊፋ እንድትታገድ አድርጓት ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አለመኖራቸው ወደውስጥ ለማሰብ በቂ ጊዜና ቦታ ፈቅዶልን ነበር፡፡ ቦሌ በሚገኘው የክለቡ የልምምድ ሜዳ ቁጥራቸው ወደ 3000 የሚጠጉ ታዳጊዎችን መልምለን ከመሃላቸው እንደኤልያስ ማሞ፣ ሞገስ ታደሰ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ አሉላ ግርማን የመሳሰሉ 25 ልጆች ማግኘት ችለናል፡፡ እነዚህ ልጆች ሶሰት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሸንፈዋል እነአሉላ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድን አባላት ነበሩ፤ ምንተስኖት ትናንት እንኳን ሆሳዕና ላይ ግብ ያስቆጠረው እሱ ነው፣ ኤሊያስን ከጊዮርጊስ ጋር ለድሬዳዋ ሲጫወት ሜዳ ላይ ተገኝቼ ተመልክቼዋለው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ 2007/8፣ በተለይ 2008/9 የሶስትዮሽ ድል ባለቤት ነበራችሁ እስቲ ስለነበረው ነገር ይንገሩን፡፡
ሳላሃዲን በወቅቱ የነበረውን አቅም (Potential) ማመን አትችልም፡፡ እኔ እንግሊዝ ፕሪሚየር ለግ ላይ በመጫወት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ይሆናል የሚል ሃሳብ ነበረኝ፡፡ በርግጥ ታላላቅ ሊጎች ላይ ተጫውቷል፤ በግብጽ፣ ሱዳን፣ ቤልጂየምና ሞሮኮ ተጫውቷል አሁንም ጥሩ አቅም አለው በቀደም ዕለት ሲጫወት እያየውት ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የማትቆጣጠረው ከአንተ አቅም በላይ የሆነ ነገር ይከሰታል፡፡ ሳላህ ላይም የተከሰተው ያ ነው፡፡ ከመሄዴ በፊት ሰበታ ላይ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ እያደረግን ያልጠበቅነው ነገር ተከሰተ፡፡
እዚህ ጨዋታ ላይ በተከሰተ ችግር ምክንያት ሚኬሌ፣ አዳነና ሳላህ ከእግር ኳስ እንዲገለሉ የሚል ውሳኔ ተወሰነባቸው፡፡ ሳላህ በተለይ በጣም በስነልቦና ተጎድቶ ነበር፤ ሰርቢያ ድረስ ይዤው ሄጄ ነበር፡፡ ወደአልሂላል ስሄድ ይዤው መሄድ ፈልጌ ነበር ይዜው ሄጄ ቢሆን ኑሮ ምናልባትም የሳላህ ህይወቱ ተቀይሮ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ በ2003 ዓ.ም. ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የተጫወተው ቡድን አባል ሊሆን የሚችልበት ዕድል ነበር ነገር ግን ከጊዮርጊስ ጋር ተስማምተን ከሳላህ ጋር ተስማምተን በቪዛ ምክንያት ብለው ከአውሮፕላን ላይ አወረዱት፡፡ አስበው በመጨረሻው ሰዓት ከሃገር አትወጣም ተብሎ ቀረ ያንን ጨዋታ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ብዙ ሰው ዓይን ውስጥ መግባት ይችል ነበር፡፡ ሳላህ ያን ጊዜ ከነበረው አቅም ሩቡን (A quarter) እንኳን አልተጠቀመውም ችግሩ ምንድነው ከሳላ ጋር አብሮ ማጥናት ይጠይቃል፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከአምስቱ ዋንጫዎች ለርስዎ የበለጠ ትርጉም ያለው የቱ ነው?
ምናልባት በ18 ነጥቦች በልጠህ የጨረስከውን የመጀመሪያ ዋንጫ ልትል ትችላለህ፤ ነገር ግን ሁሉም ሽልማት የራሱ ዋጋ አለው ለኔ ግን ደደቢትን በ27 ነጥቦች ቀድመን የጨረስንበትን የ2002ቱን ዋንጫ እመርጣለው፤ ይህ ድል ምናልባትም በራሱ በጊዮርጊስ እንኳን ላይደገም ይችላል፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በሁለቱም ወቅት አብረዎት ከሰሩ ተጫዋቾች ውስጥ ለርስዎ የተለየ የሚሉት ተጫዋች አለ?
በህይወት ውስጥ የሚታዩና የማይታዩ ድሎችን (Visible and Invisible Trophies) ታገኛለህ፡፡ ወደሱዳን ልሄድ ስል ሳርቤት አካባቢ በሚገኝ አንድ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤት ለተጫዋቾቼ ግብዣ አዘጋጀው፡፡ አብረውኝ በመስራታቸው የሚሰማቸውን ስሜት ነገሩኝ እንደአሰልጣኝ ሳይሆን እንደታላቅ ወንድም ነበር የማያቸውና እነሱም ደግሞ ለነሱ ከአሰልጣኝም በላይ እንደሆንኩ ይነግሩኝ ነበር፡፡ የዛን ዕለት የተማርኩትን ትምህርት ልረሳው አልችልም:: ይህ አሁን የምነግርህ ቡድን እነደጉ ደበበ፣ አበባው ቡጣቆ፣ አሉላ ግርማ የነበሩበት ቡድን ኋላ ላይ ከ31 ዓመታት በኋላ በአቶ ሰውነት እየተመራ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈውን ቡድን ነው፡፡ ሱዳን ላይ ሳላሃዲንና አዳነ አግብተው ኢትዮጵያ ወደውድድሩ ስታልፍ የነበረውን ስሜት መለስ ብለህ ስታስበው ስሜቱ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ በየሄድኩበት ክለብም ሆን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቼ ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ከተጫዋች ተጫዋች መለየት በፍጹም አልችልም፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከዛም ለሌላ ገድል ወደሱዳን በሱዳን በሁለት ዓመታት ሁለት የሊግ ዋንጫ፣ የሃገሪቱን የጥሎማለፍ ዋንጫ በመጀመሪያው ዓመት የኮንፌዴሬሽን፣ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ የሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ የዚህ ሁሉ ውጤት ሚስጥሩ ምን ይሆን?
በአልሂላል ሚስጥሩ ብዙ ዓመታትን አብረው የተጫወቱ ልጆች መኖራቸው ነው፡፡ ከአስራ አንዱ ልጆች ዘጠኙ ከ8-10 ዓመታት አብረው ተጫውተዋል፡፡ ጊዮርጊስ ለሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ሰቴጅ ሲያልፍ የሆነው ይሄ ነው፡፡ አብሮ መጨዋት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የጠንካራ ቡድን አሰልጣኝ ስትሆን የምታሰለጥነው ክለብ ብቻ አይደልም ብሔራዊ ቡድንም ጭምር ነው፡፡ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ያለጠንካራ ክለብ ሊመሰረት አይችልም፡፡
ወደአንድ ክለብ ስመጣ እማራለው ብዬ አልመጣም ቀድሜ ተምሬ ተዘጋጅቼ ነው የምመጣው፡፡ የመጀመሪያውን የዩጋንዳ ሥራዬን ከመያዜ በፊት በቃለመጠይቅ ወቅት ስለእግር ኳስ፣ ስለዩጋንዳና ስለቪላ ክለብ በሚገባ ተዘጋጅቼ እንሱ ስለረሳቸው ከሚያውቁት በላይ ነው የነገርኳቸው፡፡ የክለቡ አለቃ ለአምበሉ ኤድዋርድ ዋትሰን ሲያስተዋውቀኝ ዋትሰን ስለራሱ ከሚያውቀው በላይ ስለግል ህይወቱ ስለእግር ኳስ፣ ስለድክመቶቹና ስለጥንካሬው ስነግረው አፉን አ ብሎ ነበር የሚሰማኝ፡፡ አፍሪካ ውስጥ እንደኔ ለጥቃቅን ነገሮች ሁሉ በኔ ደረጃ ትኩረት የሚሰጥ አሰልጣኝ የለም፡፡
ባለፈው ለአለም የክለቦች ዋንጫ ካታር ሄጄ ነበር፤ ከአውሮፕላን ስወርድ ፓስፖርት ተቆጣጣሪው ሱዳናዊ ነበር በደንብ ያውቀኛል፡፡ ወደሆቴላችን ስንሄድ ታክሲውን ያሽከረክር የነበረ ዩጋንዳዊ እሱም እንደዛው በደንብ ያውቀኛል፡፡ ስታዲየም ስንገባ ግብጻውያን፣ ሱዳናውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ዩጋንዳውያን ሁሉ አርሴን ቬንገርና ሞሪሲዮ ፖቼቲኖ እሰከሚገርማቸው ድረስ ሚቾ ሚቾ ሲሉ ፖቼቲኖ ምንድነው አለኝ ይህን ህዝብ ስወደውና ሳገለግለው የኖርኩትን ውለታ እየመለሰልኝ ነው አልኩት፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከአልሂላል ወደ ሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ሽግግሩ ምን ይመስል ነበር?
ሩዋንዳ የነበረኝ ልምድ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ እኔ ከመሄዴ በፊት የነበረው አሰልጣኝ ጋናዊው ሴላስ ቴቴ ነበር፡፡ ሴላስ ይህን ቡድን ከመያዙ በፊት ከጋና ጋር ከሃያ ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ባለቤት ነበር፡፡ ይህንን ቡድን ፓስፖርት አስቀይሮ የያዘውን ቡድን የመሸከም ኃላፊነት ነበር የወደቀብኝ፡፡ ስለዚህ እኔ ደግሞ ከ17ዓመት ብሔራዊ ቡድኑን ያዝኩና ታዳጊዎች መርጬ ከታዳጊዎች ጋር መሥራት ጀመርኩ በአንድ ዓመት ውስጥ የሴካፋ የዋንጫ ተፋላሚ መሆን የቻለ ቡድን ማግኘት ቻልን፣ ለዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ለመግባት ጫፍ ደርሰን በዩጋንዳ በፍጹም ቅጣት ምት ተሸንፈን ቀረን፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከሩዋንዳ በርካታ ዓመታትን ወዳሳለፉበት ወደዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን
እኔ ወደዩጋንዳ ስሄድ ልክ በ1999 ዓ.ም. ወደጊርጊስ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ስመጣ እንደነበረው ዓይነት ነገር ነበር የገጠመኝ፡፡ እራሴ በቪላ ያሰለጠንኳቸው ልጆች እንደውም የ9 ዓመታት የማስተማር ልምድ ጨምሬበት፡፡ ከዚህ ትውልድ ጋር በጋራ ላይቤሪያንና አንጎላን አሸንፈን በወሳኝ ጨዋታ ከሴኔጋል ጋር በ38ኛው ደቂቃ አንድ ተጫዋች በቀይ ወጥቶብን በመጨረሻው ደቂቃ ግብ ተቆጥሮብን ነው ከውድድሩ የወጣነው፡፡ በተሾምኩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፌዴሬሽኑ ኃላፊ የነበሩት ሎሪየስ ሞሊንሻ ተነስተው በምትካቸው ምክትላቸው የነበሩት ሞሴስ ማጎጎ ሲሾሙ ምክትላቸው ደግሞ የኔ የቪላ ክለብ አምበል የነበረው ኤዲጋርድ ዋትሰን ነበር እና እኔ ወደሱዳን የሄድኩት በደንብ በሚያውቁኝ ሰዎች ነው፡፡ ስለዚህም ለብሔራዊ ቡድኑ የሚሆን ማስተር ፕላን አዘጋጀው እሱን ማስተር ፕላን መተግበር ጀመርን ለዛም ነው 2017፣ 2019 ዩጋንዳ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ቋሚ ተሳታፊ የሆነችው፡፡ ዕቅዳችን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አልነበረም፡፡
ሱዳን 2012 ላይ አለፈች ከዛ የለም፣ ኢትዮጵያ 2013 አለፈች ከዛ ተመልሶ የለም ኬንያ ለማለፍ ስንት ዓመታትን እንደጠበቀች አስብ ፡፡ ስለዚህ ዓላማችን ለማለፍ ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ የሆነ ስርኣትና መዋቅር መገንባት ነበር፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በሄዱበት ሁሉ ከታዳጊዎች ጋር ያለዎት ትስስር የጸና ነው፡፡ በርካታ ታዳጊዎች በርስዎ የመጀመሪያ ዕድል አግኘተዋል
ባለፈው ዓመት በሃገራት የእግር ኳስ ደረጃ ሰርቢያ ብራዚል፣ አርጀንቲናና ፈረንሳይን ተከትላ አራተኛ ሃገር መሆን ችላ ነበር፡፡ ሰባት ሚሊዮን ህዝብ ማለትም ከአዲስ አበባ ያነሰ ሕዝብ ብዛት ያላት ሃገር ከ450 በላይ ተጫዋቾችን ወደተለያዩ ሃገራት ኤክስፖርት ታደርጋለች፡፡ ይህ በሃገሪቱ ውስጥ ትልቅ ምርታማነት እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ ዓይን፣ ስሜትና እምቅ ችሎታን የማንበብ ብቃት ካለህ ይህን ማድረግ ቀላል ነው፡፡ እኔ በሃገሬ አንድን ተጫዋች ስናይ አሁን ያለበትን ደረጃ ሳይሆን ለመሻሻልና ለማደግ ያለውን አቅም ነው የምናየው አንዳንድ ተጫዋቾች ስታያቸው የሚገርም ብቃት ኖሯቸው የመቃኘት ብቃታቸውን ግን ጨርሰዋል ይህን ምን ታደርገዋል፡፡ ታዳጊ ተጫዋች ልክ እንደስፖንጅ ነው የሰጠኸውን ሁሉ ይቀበላላል ለዚህ ነው፡፡ አንተ እንደምትፈልገው ለማስተካከል ዕድል አለህ፡፡ ቅድም በነገርኩህ ማስተር ፕላን ይህንን ነው ያረግነው የሞከርነው፡፡ ከዛ በኋላ ኢትዮጵያ ላይ የተደረገውን የሴካፋ ውድድር ማሸነፍ ቻልን፣ ደጋግመን የአፍሪካ ማጣሪያ ለማለፍ ቻልን፡፡ ዩጋንዳ በ2001 እ.ኤ.አ. አንድ ጨዋታ ብቻ ከሜዳ ውጭ አሸነፈች ከዛ በአስር ዓመቱ በ2011 እ.ኤ.አ. ሌላ ጨዋታ ከሜዳ ውጭ አሸነፈች፤ ነገር ግን በ2013 እ.ኤ.አ. ኣና በ2017 እ.ኤ.አ. መካከል 13 ጨዋታዎችን ከሜዳ ውጭ አሸንፋለች፡፡ በሜዳው ጥሩ የነበረ ከሜዳው ውጭ ግን ምንም ማድረግ የማይችል አየህ ለዚ ነው ስትራቴጂ ያስፈለገን፡፡ በሙሉ የሜዳላይና ከሜዳ ውጭ ያሉ ችግሮቻችን ላይ በቴዎሪና በተግባር መሥራት ይጠይቅ ነበር፤ ደጋፊ፣ የአየር ሁኔታ፣ የኔዳ አለመመቸት፣ ዳኛ፣ የተቀናቀኝ አጨዋወት የመሳሰሉት ሁሉ ማለት ነው፡፡ የፌዴሬሽኑን ርዳታ ተጨምሮበት በርካታ የወዳጅነት ጨዋታዎች በማዘጋጀት ችግሮቻችንን ማረም ቻልን፡፡ ለምሳሌ 2014 ከዓለም ዋንጫው በፊት የናይጄሪያን ቡድን በወዳጅነት ገጥመን ነበር፤ እነቪንሰነት ኢንያማ ያሉበት ለዓለም ዋንጫ የሚዘጋጅ የናይጄሪያን ብሔራዊ ቡድን ተወውና አውሮፓ መጫወት በአውሮፕላን በረው በማያውቁ ልጆች ገጥመን ለዛውም ናይጄሪያ ላይ ገጥመን አንድ ለባዶ አሸንፈን ተመለስን፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ የዩጋንዳን ብሔራዊ ቡድንን በምን ምክንያት ለቀቁ?
ለስድስት ወራት ደሞዝ አልተከፈለኝም፡፡ መንግስት የኔን ጥቅማ ጥቅም ለመክፈል ፍላጎት ስላልነበረው ወቅቱ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ አንድ የመልስ ጨዋታ ብቻ ነበር የቀረን፤ ለዛውም ግብጽን አንድ ለባዶ አሸንፈን የመልስ ጨዋታ ብቻ፡፡ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ከየት ላምጣ ቤቴን ሸጬ ልክፈልህ አለኝ፡፡ እኔም ቤተሰብ አለኝ፣ ሙያዬን መንዝሬ የምኖር ባለሙያ ነኝ፤ በርግጥ ጨክኜ የምሄድ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ እኔ ስሄድ ሁለት ነገር ተፈጠረ አንድ እኔ ሥራ አግኝቼ ወደደቡብ አፍሪካ ሄድኩ፤ ሁለት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት እኔ በመሄዴ ለምን ብለው ጠይቀው ሥርዓቱ እንዲስተካከል መንገድ ተከፈተ ማለት ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ዳግም ወደኦርላንዶ ፓይሬትስ?
ከ10 ከግማሽ ዓመታት፣ ከ127 ወራት በኋላ በጣም ስሜታዊ የሚያደርግ ዳግም መገናኘት (Emotional Return) ወደቤቴ የመመለስ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ የክለቡ ፕሬዝዳንት ዶክተር አይቪን ንኮዛ አፍሪካ ውስጥ የእግር ኳስ አባቴ ማለት ናቸው፡፡ ያለሳቸው ርዳታ በአፍሪካ እግር ኳስ አሁን ያለውበት ከፍታ ላይ በፍጹም አልደርስም ነበር፡፡ እኔ ከሄድኩበት ሁለት ዓመታት በፊት 11 ሆነው ነበር የጨረሱት ለዛውም ከወራጅ ቀጠና በሁለት ነጥብ ብቻ ከፍ ብለው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት የአፍሪካን ሃብታም ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንን ተከትለን ሁለተኛ ሆነን አጠናቀቅን፡፡ በሁለተኛውም ዓመት እንደዛው ሻምፒዮንስ ሊግ የግሩፕ ስቴጅ ፣ የሊጉ ሁለተኛ የቴሌኮመም ካፕ የዋንጫ ተፋላሚ ሆነን በማጠናቀቅ ኦርላንዶ ፓይሬትስ የሚገባው ክብር ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ ቻልን፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከኦርላንዶ የለቀቁበትስ ምክንያት?
ምን መሰለህ የመጀመሪያው ዓመት ሁለተኛ ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ አስር ዓመት ብትቆይ ሁለተኛ የተሻሉ ተጫዋቾችን ማምጣትና ቡድንህን ማጠናከር እስካልቻልክ ድረስ ሁሌም ሁለተኛ፡፡ በተለይ ሁለት ተጫዋቾች የቪድቪትዝ ዊትዝ የመሃል ተከላካይ ክላኒ ታይሰን እና የራጃ ካዛብላነካውን አጥቂ ቤን ማላንጎን እንዲገዙልኝ ጠይቄ ተጫዋቾቹ አልመጡም በተለይ ቤን ማላንጎ በነጻ የሚመጣበት ዕድል እያለ ማለት ነው፡፡ እነዚ ልጆች ቢመጡ በቡድናችን ውስጥ ትልቅ ልዩነት መፍጠር እንደሚችሉ አውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ በስምምነት ለመለየየት ፈለግኩ ለቀቅኩ፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ዱሻን ኖንኮቪች ማን ናቸው?
ዱሻን ኖንኮቪች ነፍሱን ይማረውና ታዋቂ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ዛማሌክን አሰልጥኖ ነበር፡፡ ለኔ ደግሞ አጎቴም ጭምር ነው፡፡ ዛማሌክን ተረከብኩኝ ነገር ግን በአስተዳደር ላይ በተሰራ ስህተት ከደሞዝ አያያ ዝ ጋር በተያያዘ ቡድኑ ችግር ውስጥ ገባ የገንዘብ እጥረት፣ ይህም ሆኖ ግን የግብጽን የጥሎማለፍ ዋንጫ አንድም ጎል ሳይቆጠርብን ማግኘት ቻልን፡፡ ይህ ዋንጫ በአፍሪካ ምድር ያገኘሁት 16 ዋንጫ ማለት ነው፡፡ ከ3 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ድልድል ደረስን፡፡ ሁለት ምርጥ ወጣት ተጫዋቾችን ግብ ጠባቂው መሃመድ ሶፍኬ አጥቂ እና ሌላ ደግሞ አሁን ድረስ የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ መሃመድ ሙስታፋን አስተዋወቄ ከዛማሌክ ጋር በስምምነት ተለያየን ማለት ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ባንድ ወቅት ለደቡብ አፍሪካ ጋዜጠኛ ብለው ነበር ምን ማለት ፈልገው ነው “Zamalek wanted me in 2017 but Orlando snatched me” ይህ አባባል አሁን የዛማሌክ ተራ ነው ወደዛማሌክ ሄድኩኝ ለማለት ነው?
የዩጋንዳን ብሔራዊ ቡድን ይዤ ግብጽን ስንገጥም ዛማሌኮች ፈልገውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ፓይሬትስን መርጬ ሄድኩ ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ጥያቄው ተመልሶ ሲመጣ ለአዲስ ቻሌንጅ ወደ ዛማሌክ ሄድኩ፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ “I look to remain a servant and and soldier of the game on this magnificient Continent”ይህ አባባል ምን ለማለት ፈልገው ነው?
መጀመሪያ ወደአፍሪካ ስመጣ ይህን ያህል ጊዜ እቆያለው ብዬ አልመጣውም፡፡ የሚባል ቫይረስ ከነደፈኝ በኋላ ግን አፍሪካን መተው አልቻልኩም የአፍሪካ እግር ኳስ በርካታ አዞ የያዘ ትንሽ ሃይቅ ነው፡፡ በዚህ አህጉር ውስጥ ባሉ 54 በርካታ ወዳጅ አፍርቻለው በስምንት ሃገራት ውስጥ መልካም ሥራ ሰርቻለው፤የአፍሪካ እግር ኳስ አለቃ አህመድ አህመድን ጨምሮ በርካታ ወዳጆች አሉኝ፡፡ ከመጣው ጊዜ ጀምሮ የዚህን አህጉር እያገለገልኩ ነው፤ እያገለገልኩ እቀጥላለው፡፡ ከ3ቀናት በፊት ከሳኡዲ አራቢያ የአሰልጥነን ጥያቄ መጥቶልኝ ነበር ነገር ግን አልተቀበልኩትም አሁን ግን በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ አንድ ትልቅ ብሔራዊ ቡድን እረከባለው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ስለኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በደምና በአጥንቴ ውስጥ ያለች፣ ባህሏና ስርኣቷ ለነፍሴ የሚስማማኝ የአፍሪካ እግር ኳስ ምሳሌ የምትሆን ሃገር ናት፡፡ ኃያል የእግር ኳስ ፍቅር ያለው ልበ-ንጹህ ህዝብ ያላት ሃገር ናት እኔ እራሴን የማየው የኢትዮጵያዊ ዲኤንኤ ያለው በአፍሪካ ውስጥ የሚኖር የሰርቢያ ድብ አድርጌ ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ በዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ሩዋንዳ፣ ግብጽ፤ አምስት የምስራቅ አፍሪካ አንድ የደቡብ እና አንድ የሰሜን ሃገራት ውስጥ ሰርተዋል፡፡ መካከለኛና ምዕራብ አፍሪካ ባለመፈለግ ነው ወይስ ዕድሉን አላገኙትም?
በቀደም የተገናኘን ዕለት ነግሬህ ነበር እንደቀልድ ወስደኸዋል ማለት ነው፡፡ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ብችል ኑሮ አንድ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገር ይዤ ሁለት ዋንጫ በልቼ ነበር፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ አማርኛ አቀላጥፈው ያወራሉ
መጀመሪያ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እፍጨረጨራለው ነገር ግን አሁንም ይከብደኛል፡፡ ብዙ ጊዜ እዚ ስለማልኖር እንጂ እዚ ብሆን ምናልባት እስካሁን በደንብ መናገር እችል ነበር፡፡ ነገር ግን በሄድኩበት ሁሉ ኢትዮጵያውያንን ሳገኝ በአማርኛ ለመናገር እሞክራለው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ እኛ አሁን ያለንበት ወቅት የርስዎ ሃገር ዩጎዝላቪያ ከሃያ ዓመታት እንደነበረችበት ዓይነት መንታ መንገድ፤ አንድነት ወይም ሞት ምን የሚሉን ነገር አለ?
ውድ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያን እግር ኳስ እንደሚወድ አንድ የኢትዮጵያ ወዳጅ አድምጡኝ፤ ኮት ዲቯር በ2006 ዓ.ም. ለፍጻሜ በደረሱበት ወቅት ድሮግባና ጓደኞቹ ልትከፈል የነበረች ሃገራቸውን አንድ አረጉበት፡፡ እኔም እባካችሁ እግር ኳስ ያለውን የማስታረቅ፣ የማግባባት አንድ የማድረግ ኃይሉን ተጠቀሙበት፡፡ ከየትኛውም ሃይማኖት ወይም ጎሳ ልትመጡ ትችላላችሁ ከአንድነት ውጭ ምንም የተሻለ አማራጭ የላችሁም፣ የኛ መበታተን ትምህርት ሊሆናችሁ ይገባል፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ከጊዮርጊስ አመራሮች ጋር በተራ ታይተዋል ከጊዮርጊስና ከብሔራዊ ቡድኑ አንዱን ይይዛሉ እየተባለ ነው፤ እውነት ነው?
ሁለቱም አይሆንም አብራሃምም አቶ ሰውነትም ጥሩ ወዳጆቼ ናቸው የወዳጅ ወሬ ነው ያወራነው፤ አብርሃም መብራህቱ በጣም ወዳጄ ወንጂን ሲያሰለጥን በተቃራኒ ተጫውተናል ከዛ በላይ በየመን የሰራውን ታላቅ ሥራ ሁሉ አውቃለው፣ አደንቃለው፡፡ ሌላው የሃገሬ ልጅ ዥቮይኖቭ በያዘው ቡድን ላይ ከጀርባ በፍጹም ልደራደር አልችልም፡፡ በሰርቢያዊ ጀርባ ቡድን የምይዝ ቢሆን ኑሮ ቪዳድ ካዛብላንካን እይዝ ነበር ግን አልፈልግም፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ክለብዎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ዋንጫ ሳያገኝ ከመዝለቅ ባሻገር አሁንም አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አይገኝም ምክንያቱ ምን ይሆን?
አንድ ምሳሌ ልስጥህ 2006፣ 2008 እና 2010 በተከታታይ ዋንጫ በላ ከዛ በኋላ 2012፣ 2013 እና 2015 ማጣሪያ እነኳን ማለፍ አልቻሉም ችግሩ በዕቅድ የትውልድ ሽግግር ማድረግ አለመቻል ነው አንድ ቡድን በአግባቡ ከትውልድ ወደትውልድ መሸጋገር አለበት፡፡ ማንኛውም ቡድን ባርሴሎና፣ ማድሪድ እንዲሁም ማንችስተር ዩናይትድ የሽግግር ወቅት አለው፡፡ ለቡድኑ ለአሰልጣኞች፣ ለተጫቾች ክብር አለኝ ነገር ግን አሁን ጊዮርጊስ አሁን ሽግግር ላይ ነው፡፡ ተከላካዩ ከነደጉ ወደነ አስቻለው፣ ሚድፊልዱና አጥቂው ደግሞ ከነሳላሃዲን ወደአዳዲስ ልጆች መሸጋገር አለበት፡፡ የጊርጊስን ማህበረሰብ የም;ጠይቀው ይህ ሽግግር ጊዜ ስለሚፈልግ በትዕግስት እንዲጠብቁ ነው ነገር ግን እንደአንድ የጊዮርጊስ ደጋፊ ይህ ያለውጤት ጉዙ ዘንድሮ ቢያበቃ እኔም ደስ ይለኛል ምክንያቱም አንድ ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ዕድል ነው፣ ሁለተኛ ሲሆን መገጣጠም ነው ሶስተኛ ከሆነ ግን ልምድ ነው፡፡ በዮጊርጊስ ቤት የመሸነፍ ልምድ የለም፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከአውሮፓ የምን ክለብ ደጋፊ ኖት?
እኔ ወጣት የነበርኩበት ትውልድ የሊቨርፑል ታላቅነት የነበረበት ዘመን ነው፡፡ ከልጅነቴ ሳድግ ርደሰታረ ቤልግሬድን እየደገፍኩ ነው ያደግኩት ይህም ክለብ ከሊቨርፑል ጋር ልዩ ግንኙነት አለው፡፡ የርገን ክሎፕ አእምሮ የሚባለው ሰርቢያዊ ዤኮ ቩቫች ነው ከኔምጋር በአንድ ፕሮጀክት ሰርተናል በሱም አማካኝነት የየርገን ክሎፕን ህልምና ዕቅድ ለማየት ዕድል ነበረኝ፣ ሰውዬውን ከሜይንዝ ጀምሮ፣ በቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከዛም በሊቨርፑል የሰራውን ነገር አደንቃለው፡፡ ስለዚህ በነዚና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሊቨርፑል ደስ ይለኛል፡፡ ፕሮፋይል አሰልጣኝ ቡድን የለውም ነገ የት እንደምትሄድ አታውቀውም፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ይበልጥ የሚያደንቁት አሰልጣኝ?
የሁላችንም የሰርቢያውያን አባት ሚላን ሚላኒቸ ነው፡፡ የመጀመሪያው የሪያል ማድሪድ የውጭ አሰልጣኝ ነው፡፡ ቶሚስላቭ ኢቪች ደግሞ በዞን መጫንን ከቅርጫት ኳስ ቀድቶ ወደእግር ኳስ ያስተዋወቀ የእግር ኳስ ሊቅ የፈጠረ ሊቅ ነው፡፡ ዮሃን ክሩይፍ ከሁሉም የተለየ ሰው ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ትርፍ ጊዜዎን በምን ያሳልፋሉ?
ከእግር ኳስ ውጭ ጊዜ የለኝም፡፡ እግር ኳስ ምግቤ፣ መጠጤ ነው፣ የምተነፍሰው አየር ነው፡፡ ሁሉም ነገሬ እግር ኳሽ ነው ከእግር ኳስ ውጭ አንድም ደቂቃ የለኝም፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ኢትዮጵያዊት ሚሰት አግብተው ሶስት የሚያማምሩ ልጃገረዶችን አፍርተዋል እስቲ ቤተሰብዎን አስተዋውቁን?
ቤተሰቤ የሕይወቴ ምሰሶ ነው፡፡ ሁሉም ነገሬ ቤተሰቤ ነው፤ ባለቤቴ ፍቅር ትባላለች ከፍቅር ጋር ሶስት ሴት ልጆችን አፍርተናል፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን ሃበሣ ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ከአብናት ሶስተኛዋ ደግሞ ታምራ ትባላለች፣ በትምህራታቸው ጎበዞች ናቸው፡፡ በስኬት እንድጓዝ የሚረዱኝ እነሱ ናቸው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ከሁሉ አስበልጠው የሚወዱት መጽሃፍ?
የምወደው መጽሃፍ የማርሴሎ ቢየልሳ አውቶ-ባዮግራፊ ነው
ሃትሪክ ስፖርት፡ የሚወዱት ኢትዮጵያዊ ምግብ?
ጎመን በስጋ
ሃትሪክ ስፖርት፡ የሚወዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ መዳረሻ?
ላሊበላ
ሃትሪክ ስፖርት፡ ምናልባት አንድ ቀን አውሮፓ ውስጥ የማሰልጠን ሃሳብ ይኖርዎት ይሆን?
ከዛማሌክ ስለቅ ከአምስቱ ታላላቅ ክለቦች ውጭ ብዙ እድሎች ነበሩኝ ከቤልጂየም፣ ቱርክና ፖርቱጋል የአሰልጥነን ጥያቄዎች ነበሩ ነገር ግን ነፍሴን ጥዬ መሄድ አልችልም፣ ነፍሴ አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡
ሃትሪክ ስፖርት፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት ያሰቡት ነገር ይኖር ይሆን?
በርግጠኝነት ጡረታ ስወጣ ሃሳቦች አሉኝ አሁን ግማሽ ግማሽ ሆኖ መስራት የምችል አይመስለኝም ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ ትልልቅ ሃሳቦች አሉኝ፡፡