“The Pride of Ethiopia in AFCON”
በእርግጥ አሁን አሁን በአፍሪካ ዋንጫ
ኩራታችን እየሆነ የመጣ ኢትዮጵያዊ ነው ብንል ቃሉ ግነት የለውም፡፡ በተለያዩ የአህጉሪቱ
የክለቦች ኢንተርናሽናል ውድድሮች በተለይም ደግሞ የአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር በሆነው
የአፍሪካ ዋንጫ ላይ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ታላቅ ስም በተደጋጋሚ ከፍ አድርጎ ማስነሳቱ
በእርግጥም “The Pride of Ethiopia” (የኢትዮጵያ ኩራት) እየሆነ ለመምጣቱ ምስክር ነው፡
፡ ከምንም በላይ ደግሞ ቀደም ባሉት ዓመታት የአፍሪካ የውድድር መድረኮችን ሲያጣብቡ
የነበሩ ኢንተርናሽናል አርቢትሮቻችን ጠፉ እያልን በቁጭት በምንብሰለሰልበት ወቅት “አለሁ”
ብሎ ብቅ ማለቱና የሀገራችንን ስም በተለያዩ ታላላቅ ውድድሮች ላይ ማስጠራቱ እንዲሁም
ብ/ቡድናችን በአፍሪካ ዋንጫ ባለመሳተፉ የሚያድርብንን ቁጭት በመድረኩ ብቸኛው
ወኪላችን ሆኖ በማስረሳቱ ልናመሰግናውና ልናከብረው የሚገባ ድንቅ ልጃችን ነው፤ የዛሬው
እንግዳችን ወጣቱ የካፍ ኤሊት ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ ወዬሳ፡፡
የፊታችን ጥር 6 በጋቦን አስተናጋጅነት ለሚጀመረው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ
ከተመረጡት 17 የካፍ ምርጥ የመሀል ዳኞች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል
አርቢትር በአምላክ ተሰማ የ90 ሚሊየን ህዝብ ውክልናን አንግቦ ወደ ውድድሩ ስፍራ
ከመጓዙ በፊት የሀትሪክ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የፋርማሲስቱን
ኢንተርናሽናል አርቢትር የተጣበበ ጊዜውን ተሻምቶ ቃሉን ተቀብሎት ለአንባቢ በሚመች መልኩ አቅርቦታል፡፡
- ማሰታውቂያ -
——————————
ሀትሪክ፡- በመጀመሪያ የ2017ቱን
የጋቦኑን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲመሩ
ከተመረጡት 17 የካፍ ኤሊት ኢንተርናሽናል
ዳኞች ስም ዝርዝር ውስጥ የአንተና የአገራችን
ስም በመካተቱና የ90 ሚልዮን ህዝብ ስምን
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በመወከልህ እንኳን ደስ
አለህ ማለት እፈልጋለሁ?
በአምላክ፡- እኔም እንኳን አብሮ ደስ አለን
ለማለት እፈልጋለሁ፤ እድሉ የተገኘው በእኔ
ብቻ ሳይሆን በፈጠረኝ አምላክና በሁሉም
ኢትዮጵያዊያን ድጋፍና እገዛ በመሆኑ
ሁላችሁንም እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ ፡፡
ሀትሪክ፡- ከሁለት ወር በፊት አንድ
አስደንጋጭ መረጃ ሰምቼ ነበር፤ በአምላክ
በካፍ የተሰጠን አንድ ፈተናን ማለፍ ባለመቻሉ
ለጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ከሚመረጡት ዳኞች
ዝርዝር ውጪ ይሆናል የሚል?
በአምላክ፡- ነገሩ እንዴት መሰለህ ከ2
ወራት በፊት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን
የጋቦኑን የአፍሪካ ዋንጫን የሚመሩትን
ዳኞች ለመምረጥ ግብፅ ካይሮ ላይ የአካል
ብቃት ፈተና ይሰጥ ነበር፤ እኔም ለዚህ ፈተና
ከተጠሩት ኤሊት ኢንተርናሽናል ዳኞች ውስጥ
አንዱ ስለነበርኩ ለፈተናው የሚረዳኝንና
በብቃት የሚያሳልፈኝን ዝግጅትም አድርጌ
ነበር ወደ ስፍራው የተጓዝኩት። ነገር ግን
ግብፅ እንደደረስኩ ፈተናው እንደ ነገ ሊሰጥ
እንደዛሬ (ICE TERAPHY) የበረዶ ህክምና
ቶሎ ሪከቨር ለማድረግ ይረዳል ሲባል ሰምቼ
እንደዚሁም ግብፃዊያን ዳኞች ሲያደርጉት
አይቼ ICE TERAPHY ተጠቀምኩ።
በነጋታው ግን ያልጠበቅኩት ነገር ተከሰተ፤
ለፈተና ስቀርብ ICE TERAPHY ሰውነቴን
ከማፍታታት ይልቅ በጣም አደንዝዞት ስለነበር
ፈተናውን ለማለፍ የሚያበቃኝን ሚኒማ
ማሟላት ሳልችል ቀረሁ፤ ICE TERAPHY
ለእኔ አዲስና እንግዳ ነገር በመሆኑ ከተሰጡት
ሶሰት የመመዘኛ ፈተናዎች አንዱን ማሟላት
ሳልችል ቀረሁ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ
ከሚመሩት ዳኞች አንዱ ለመሆን ሶስቱንም
መመዘኛዎች በብቀት ማለፍ የግድ ነው፤
ይሄን ባለማሟላቴ ችግሮች ተፈጠሩ፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ታዲያ እንዴት ልትመረጥ
ቻልክ?
በአምላክ፡- ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ
ማለትም ከአንድ ወር በኋላ ካሜሮን አገር ላይ
ለአፍሪካ ዋንጫ የሚያበቃ ተመሳሳይ ፈተና
ይሰጥ ነበር፤ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ማመስገን እፈልጋለሁ፤
እድሉን አግኝቼ ፈተናውን በድጋሚ ተፈትኜ
አለፍኩ ማለት ነው፡፡ ካፍ እንደዚህ አይነቶቹን
የአህጉሪቱን ታላላቅ ውድድሮች የሚመሩ
ዳኞች የሚመዘኑበት የተለያዩ መመዘኛዎች
አውጥቶ ነበር፤ መጨረሻ ምርጫ ውስጥ
ለመግባት እነዚህን መመዘኛዎች በብቃት
ማለፍ የግድ ነበር፤ ያንን በማሳካቴ ከእጄ
ሊወጣ የነበረው ታላቅ እድል ተመልሶ እጄ
ሊገባ ችሏል፡፡
ሀትሪክ፡- ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ
በኩል ብዙዎች ለአንተ የተለየ አድናቆት
እንዳላቸው አውቃለሁ፤ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ
የ90 ሚሊየን ህዝብ ውክልናን ይዘህ የአፍሪካ
ዋንጫ ላይ በብቃት ለመዳኘትና የወከልከውን
ህዝብ ስም ለማስጠራት ምን ያህል ጊዜ…?…
ምን አይነት ዝግጅት አድርገሃል…?
በአምላክ፡- ልምምድ የእለት ተዕለት
ተግባሬ ነው፤ ምንአልባት የአሁኑ የአህጉሪቱ
ትልቅ ውድድር በመሆኑ በአካልም በአእምሮም
የተለየ ትኩረት እንድትሰጠው ትገደድ ይሆናል
እንጂ እኔና ልምምድ ተለያይተን አናውቅም፡፡
በዚህ የተነሳም በሳምንት 6ቀን የተለየ ዝግጅት
ሳደርግ ነው የቆየሁት፤ በሳምንት ውስጥ አንድ
ቀን ብቻ ነው የማርፈው፡፡ የተለያዩ ልምዶችን
በመስራት ነው ስዘጋጅ የቆየሁት፤ በዚህ
አጋጣሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን
በድጋሚ ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ለአገራዊ
ውክልናዬና ለሙያዬ ዋጋና ክብር በመስጠት
የአዲስ አበባ ስቴዲየምን እንድለማመድበት
ፈቅዶልኛል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ጋቦን
እገዛለሁ፤ ውድድሩ ጥቂት ቀናቶች ሲቀሩት
እዚያ እንደገባን ውድድሮችን መምራት
የሚያስችል ብቃት ላይ መሆናችንን በተግባር
ለማረጋገጥ የሚሰጥ ፈተና አለ፤ ያንን ፈተና
በብቃት ለማለፍ ያስችላሉ ብዬ ያመንኩባቸውና
አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን በተሰጠን ልዩ
ማንዋል መሰረት በየቀኑ ከአንድ ቀን በስተቀር
ስዘጋጅ ቆይቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ስለ ዝግጅት ስታነሳ ብዙዎች
ለማመን የሚቸገሩት አንድ ነገር ትዝ
አለኝ፤ የካፍ ባለሙያዎች አገራቸው ላይ
ሆነው የኢንተርናሽናል ዳኞችን ልምምድና
ብቃታቸውን የሚከታተሉበት እጅ ላይ
የሚታሰር ሰአት መሰል ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ
አለ ይባላል… እውነት ይሄ ነገር አለ…?
በአምላክ፡- …አዎን አለ…!
በኢንተርናሽናል ደረጃ የምናጫዉት ዳኞች
እጃችን ላይ የሚታሰር ፖላር አለ፡፡ የአፍሪካ
ዋንጫን እንዲመሩ የተመረጡ ዳኞች ደግም
እጃቸው ለይ ከሚታሰረው ፖላር በተጨማሪ
በዚህ ፖላር አማካይነት ልምምዳቸውንና
ብቃታቸውን የሚከታተሏቸው
ኢንስትራክተሮች አሏቸው፤ ቱኒዚያና ሴኒጋላዊ
ኢንስትራክተሮች ፡፡ እነዚህ ኢንስትራክተሮች
የእኔን ዝግጅትና ያለሁበትን ሁኔታ በየጊዜው
ይከታተላሉ፡፡ እንዴት ነው የሚከታተሉት?
ብለው ለሚጠይቁና ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ
ያህል ልምምዴን ሰርቼ ከጨረስኩ በኋላ እጄ
ላይ የታሰረዉን ፖላር ከኮምፒዩተሩ ጋር
ሳገናኘው ያለውን ዳታ(መረጃ) በሙሉ ለእነሱ
ያስተላልፍላቸዋል፤ እነሱም በዳታዉ መሰረት
(በመረጃዉ መሰረት) የት ቦታ ላይ ምን
አይነት ትሬይኒንግ እንደሰራሁ፤ ምን አይነት
ጫና እንደወሰደኩ፤ካነሰ ወይስ ወይም ከበዛ
የምታስተካክልበትን፤ በርዝ ሬትህ፣ (የልብ
ምትህ) ፣አተነፋፈስህ፣ ፍጥነትህን በተመለከተ
ከዳታው ላይ አይተው የምታሻሽለውን
እንድታሻሻል ጥሩውን አጠናክረህ እንድትቀጥል
የሚከታተሉበትና አቋምን ጠብቀህ እንድትሄድ
የሚያግዙበት ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ይህ ሁኔታ ዳኝነት የት እንደደረሰ
የሚጠቁም ነው፤ ከዚህ መረጃ በመነሳት
ዳኝነት በራሱ ሳይንስ ሆኗል ተለውጧል ብሎ
መናገር ይቻላል?
በአምላክ፡- በጣም እንጂ..! ዳኘነት ከዘመኑ
ከጊዜው ጋር በጣም አድጓል፤ እግር ኳስ
አሁን እየተለወጠ በጣም ፈጣን እየሆነ ነው፤
አንዳንድ ለውሳኔ የሚያስቸግሩ ከብርሃን
የፈጠኑ ቅፅበቶች በሽርፍራፊ ሰኮንዶች
ውስጥ እየታዩበት ስለሆነ ዳኝነትም በዛው
መጠን ማደግና መለወጥ አለበት፡፡ በሜዳ ላይ
የዳኝነት ስህተቶችን ለማረምና እግር ኳስን
ከበዙ ስህተቶች ለመጠበቅ ሲባልም በየጊዜው
ዳኝነት ላይ አዳዲስ ነገሮች እየተጨመሩበት
ነው፤አሁን በቅርቡ በክለቦች የአለም ዋንጫ
ውድድር ለይ “የቪዲዮ አሲስታንት ሪፊሪ”
ወደ ሚባል ነገር በድጋሚ ዳኛው ምስል አይቶ
ወደ ሚወስንበት ነገር እየተገባ ነው፡፡ ከዘህ
ውጪ ወደ ግል ህይወትህም በመግባት ላይፍ
ስታይልህ ውስጥ ሁሉ ተገብቷል፤ የምግብ
አወሳሰድህ፣ የእረፍት አጠቃቀምህ ለዳኝነት
ሙያህ ስትል መቀየርና መቆጣጠር ግድ
ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ ዳኝነት እያደገ ሳይንስ
እየሆነ በመምጣቱ ሁሉ ነገርን መቀየር
የሚያስገድድበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው
ያለው፡፡
ሀትሪክ፡- እስቲ አሁን አንተ እና እኔን ወደ
አገናኘን ዋናው ጉዳይ እንግባ፤ የካፍ ድረ-ገፅን
ስመለከት ለአፍሪካ ዋንጫ ከተመረጡት 17
ኤሊት ኢንተርናሽናል ዳኞች ውስጥ በአምላክ
ተሰማ ወዬሳ ከኢትዮጵያ አንዱ መሆኑን
ይመሰክራል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በአህጉሪቱ ትልቅ
የውድድር መድረክ ላይ አገርህን ወክለህ
የመቅረብ እድል በማግኘትህ በውስጥህ
የተጠረውን ስሜትና መመረጥህ በራሱ ለአንተ
የሰጠህን ትርጉም ንገረኝ እስቲ?
በአምላክ፡- ይሄን መሰሉን ትልቅ እድል
ማግኘቴ ለእኔ ትርጉሙ ብዙ ነው፤ እኔ
ትንሹ ዳኛ የ90 ሚልዮን ህዝብን ስም ወክዬ
በአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር ላይ የምሳተፍበት
እድልን ማግኘቴ የፈጠረብኝን ስሜት በቃላት
መግለፅ አልችልም፡፡ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ
የውድድር መድረኮችን ያጣበቡ ኢትዮጵያዊያን
ዳኞች አሁን በብዛት አይታዩም ወይም ክፍቱቱ
(ጋፑ) ሰፍቷል በሚባልበት ሰአት በዚህን
መሰሉ መድረክ ላይ “ኢትዮጵያ” የሚለውን
ታላቅ ስም ወክዬ መገኘቴ ለእኔ የላቀ ትርጉም
ነው የሚሰጠኝ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ
ነኝ። ይሄ ስኬት ወይም ክብር የመጣው
ግን በእኔ የግል ጥረት ብቻ አይደለም፤
በዋነኛነት የፈጣሪዬ፣ የቤተሰቦቼ፣ የሙያ
አጋሮቼ፣ የፌዴሬሽኑ፣ የሚዲያው እንዲሁም
ስሳሳት የሚያርመኝ፤ ጥሩ ስሰራ አጨብጭቦ
የሚያበረታታኝ የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ
የሁሉም ድምር ውጤት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን አሁን ኢትዮጵያ በዳኝነት
በኢንተርናሽናል መድረክ በዋናነት እየተጠራች
ያለችው በሴቶች በኤሊት ኢንተርናሽናል
ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ፣ በወንዶች ደግሞ በአንተ
ብቻ ነው፤ ይሄ መሆኑስ ደስታህን የተሟላ
ያደርገዋል?
በአምላክ፡- በርካታ ዳኞች በዚህን መሰሉ
ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነው ባይ የደስታዬን
መጠን ይበልጥ ከፍ ያደርገው ነበር፡፡ በእርግጥ
ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በአፍሪካ በዳኘነት ብቃት
ብቻ ሳይሆን በጨዋነታቻውም ትልቅ ክብርና
ስም ነው ያላቸው፡፡ ቀደም ባሉት አመታት
ታላላቅ ውድድሮችን የመሩ፣ የአገራቸውን ስም
ከፍ አድርገው ያስጠሩ፣ባንዲራዋን ያውለበለቡ
ስመ-ጥር ዳኞችን ያፈራች አገር ናት፡፡
ይሄ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክፍተት
የፈጠረበት ሁኔታ ቢኖርም በአሁን ሰአት ከእኛ
ውጪ በተለያዩ ካታጎሪዎች ስመ-ጥር ዳኞችና
ረዳት ዳኞች ብቅ እያሉ ነው፡፡ ኤሊት ኤ፣
ኤሊት ቢ፣ በያንግ ታለንት እና አፕካሚንግ
ሪፈሪ ካታጎሪ ውስጥ በርካታ ዳኞቻችን ብቅ
እያሉ ነው፡፡ ይሄ መሆኑ የቀድሞ ስማችንና
ክብራችንን መልሰን እንድንይዝ ይረዳናል፤
ይሄንን ወደ ኤሊት ኤ ማሳደግ ቀጣይ ስራችን
መሆን አለበት፡፡ ያኔ የተፈጠረው ክፍተት
ይሞላና ከአንድና ከሁለት ዳኞች በተጨማሪ
በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በውድድር
መድረኮች ላይ በብዛት ይታያሉ፡፡
ሀትሪክ፡- ስለዚህ “አታስቡ በቅርቡ በርካታ
በአምላኮችና ሊዲያዎችን እናያለን” እያልክ
ነው?
በአምላክ፡- አትጠራጠር…! በአጭር ጊዜ
ውስጥ ነገሮች ይለወጣሉ፤ እኔ በአጋጣሚ
በዚህ መስመር ውስጥ ልገኝ እንጂ በርካታ
ኢትዮጵያዊያን በመድረኩ ላይ መታየታቸው
አይቀሬ ነው፡፡ አሁን የተጀመረውንና
የተያዘውን መስመር አስፋፍተን መሄድና
ማሳደግ ነው የሚጠበቀው፡፡
ሀትሪክ፡- 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ
ዳኝተሃል፤ ከዚህ ውድድር ወይም ያለፈው
የአፍሪካ ዋንጫ ምን አስተምሮህ አልፏል?
በአምላክ፡- አንድም ብትሆን… ትንሽም
ብትሆን… ስህተት መስራት እንደሌለብኝ
አስተምሮኝ አልፏል፤ በዚህን መሰሉ የአገሪቱ
ትልቅ ውድድር ትንሽ የምትላት ስህተት ትልቅ
ዋጋ እንደምታስከፍል በተግባር የተማርኩበት
የአፍሪካ ዋንጫ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡
ከዚህ ውጪ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ትላልቅ
ውድድሮችን መምራት የሚያጎናፅፈውን
ደስታና ኩራት በተግባር አይቼበታለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከፍተኛ ፍጥነትን በተላበሰውና
ኳስ መደበቂያ ያጣች ይመስል ፋታ
የማይሰጠውን የካሜሮንና የጊኒን ጨዋታ
በበቃት በመምራትህ በዛ ያለውን ሙገሳ
ቢያጎናፅፍህም፤በተቃራኒው አስወቅሶሃል
አስተችቶሃልም የሚል ነገር አለ፤ ይሄ ነገር
እውነት ነው?
በአምላክ፡- እንዳልከው የካሜሮንና
የጊኒ ጨዋታ በፍጥነት የተሞላ እረፍት
የሌለው ጨዋታ ነበር፤ በዚህ ጨዋታ
ብዙዎች ቢያስመሰግኑኝም እንዲት ትንሽ
ስህተት ከወቀሳ አለዳነችኝም፡፡ በዚህች ትንሽ
ስህተት ሳቢያም ቶሎ ወደ አገሬ እንድመለስ
የተደረገበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ትንሽ
ስህተት ትልቅ ዋጋን እንደምታስከፍል ያለፈው
የአፍሪካ ዋጫ አስተምሮኛል ያልኩትም ለዚሁ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ምን ቢፈጠር ነው ይሄን ያህል?
በአምላክ፡- ይሄ ነገር ከተመልካቹ ይልቅ
ለባለሙያተኞች ነው ይበልጥ ግልፅ የሚሆነው፤
በሁለቱ አገሮች ጨዋታ ለይ የጊኒው ብሄራዊ
ቡድን ተጨዋች በካሜሮን ግብ ክልል ውሰጥ
ይገፋና ይወድቃል፤በወቅቱ እኔ ከእንቅስቃሴው
ትንሽ ራቅ ባለ እይታ ውስጥ ስለነበርኩ
ሲገፋ አይቻለሁ ግን የፍፁም ቅጣት ምት
(ፔናሊቲ) ለመስጠት እርግጠኛ አልነበርኩም፡
፡ በእግር ኳስ ህግ ደግሞ የፍፁም ቅጣት ምት
(ፔናሊቲ) 100 ፐርሰንት እርግጠኛ ካልሆንክ
የፍፁም ቅጣት ምት (ፔናሊቲ) መስጠት
አይመከርም፡፡ እኔም 100 ፐርሰንት እርግጠኛ
ሰላልነበርኩ አልሰጠሁም፡፡ ከጨዋታው በኋላ
በድጋሚ ምስል በቪዲዮ ግምገማ በሚደረግበት
ጊዜ መምህራኖቼ በወቅቱ የተፈጠረው
ክሰትት የፍፁም ቅጣት ምት ያሰጥ ነበር
የሚል አንድምታ ያለው አስተየየት ሰጥተው
ተገምግሜበት ነበር፡፡ ይሄ ክፍተት ተፈጥሮብኝ
ረዥም ጉዞ እንዳልጓዝ አድርጎኛል፡፡ ይሄ
ከባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ትልቁ ቁም ነገር
ያገኘሁበት አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሰጠኝን
የመጀመሪያ ጨዋታ ያለምንም አስተያየት
(ግምገማ) በብቃት ከእግዚአብሄር እርዳታ ጋር
መጨረስ እንዳለብኝ ተምሬበታለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ለሁለተኛ ጊዜ የአህጉሪቱን
ትልቅ ውድድር እንድትመራ ተመርጠሃል፤
ህልምህ የአፍሪካ ዋንጫን በመምራት ብቻ
ይገደባል የሚል እምነት ስለሌለኝ አለም
ዋንጫንስ አሻግረህ አታልምም?
በአምላክ፡- ህልሜ ትልቅ ብቻ ሳይሆን
ሩቅም ነው፤ ቀደም ሲል በአፍሪካ ዋንጫ
የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድርን እስከ
ሰሚ ፋይናል የደረሱ ዳኞች ነበሩ፡፡ አሁን
ደግሞ በሴት እህቶቻችን አገራችንን የሚያኮራ
የዳኘነት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ዘንድሮ ሴት
ዳኞቻችን(ሊዲያ ታፈሰን ማለቱ ነው) የአፍሪካ
የመክፈቻ ጨዋታና የደረጃ ጨዋታ በብቃት
መርተው ተመስግነው የተመለሱበት ሁኔታ
ተፈጠሯል፤ ዳኞቻችን በአፍሪካ የውድድር
መድረክ ጠፋ በሚባልበት በዚህ ወቅት ይሄን
መሰሉ ስኬት መመዝገቡና መመስገናቸው
የበለጠ እምነት እንዲጣልብንና በተደጋጋሚ
እድል እንድናገኝ ይረዳል፡፡ የእኔ ሃሳብና
ፍላጎት ወደእነዚህ ስኬቶች መጠጋት ነው፡፡
ትልቁን የአለም ዋንጫ ሴት የሙያ ጓደኞቼ
እንዳሳኩት እኔም ማሳካት ነው ምኞቴ ነው፤
በአጠቃላይ ህልሜ በአፍሪካ ዋንጫ ተገድቦ
መቅረት ሳይሆን ወደ አለም ዋንጫም
መጠጋትም ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚያ በፊት ግን በአምላክ
ከአንድ ጨዋታ በዘለለ በአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ
ፍፃሜና የፍፃሜ ጨዋታ ሲመራ የምናየው
መቼ ነው?
በአምላክ፡- ዛሬ ላይ ሆኜ ይህንን
በእርግጠኝነት መናገር አልችልም፤እነዚህን
ነገሮችን ለማሳካት የአቅሜን ዝግጅት
አድርጌያለሁ፡፡ አሁን ማለት የምችለው
የአፍሪካ ዋንጫን ሴሚ ፋይናል ድረስ
ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ሲያጫወቱ አይቻለሁ፡
፡ እኔም በዚህን ጊዜ አድርገዋለሁ ባልልም
የእነሱን ታሪክ ለመጋራትና ለማሳካት ግን
ጠንክሬ መስራቴን እቀጥላለሁ፡፡ እንደ እኔ
ጥረት እንደ እግዚአብሄር እርዳታ ግን አንድ
ቀን ተሳክቶ ማየቴ አይቀርም፡፡
ሀትሪክ፡- በአፍሪካ ትልቅ ክብር ካላቸው
ዳኞች አንዱ መሆንህን አውቃለሁ፤ ለአገሪቱ
ታላቅ ውድድር ከተመረጡት 17 ኤሊት
ኢንተርርናሽናል ዳኞች ውስጥ አንዱ መሆንህ
በራሱ ምስክር ነው፡፡ እንደው ለመሆኑ በአፍሪካ
ያገኘኸው ክብርና አመኔታስ በአገሬ አግኝቻለሁ
ብለህ ታምናለህ ወይስ ነገሩ ነብይ…በአገሩ…
ሆኖብሃል?
በአምላክ፡- በእውነት ለመናገር በአገሬ
ትልቅ ክብርና አመኔታ አለኝ፤ በዚህም
ደስተኛ ነኝ፤ እኮራለሁም። በአፍሪካም ይሁን
በአለም ከሚኖርህ ክብር ይልቅ በአገርህ
በህዝብህ የምታገኘው ክብርና አመኔታ
ይበልጣል፤ ዋጋውም የማይተመን ነው፡፡
በአገርህ ያለው ክብርና አመኔታ ከምንም ነገር
ይበልጣል፤ እኔ ደግሞ በዚህ በኩል በጣም
እድለኛ ነኝ፡፡ ከወገኔ ከህዝቤ የጎደለኝ ነገር
የለም፤ በሙያዬ ትልቅ ክብርም አመኔታም
አለኝ፡፡ በየሄድኩበት ቦታ በክልልም በአዲስ
አበባም ስሜን ጭምር እየጠሩ ያላቸውን
ክብርና ፍቅር ድጋፋቸውምን በተለያዩ መንገድ
ሲገልፁልኝ ማቴየም የሚያረጋግጥልኝ ይሄንኑ
ነው፡፡ በእኛ አገር ዳኝነት ነፃነት ነው፤ ዳኝነት
ፍቅር ነው፤ ከማንኛውም ሙያ በበለጠ
በነፃነት የምትሰራው ሙያ ቢኖር ዳኝነት ነው
ለእኔ፤ በዳኝነት የሚመጡ ተቋውሞዎችም
ድጋፎችም ምክንያታቸው አንድ ነገር ነው
እሱም ከፍቅር፣ የተሻለ ደረጃ ደርሰህ ከማየት
እንደሆነነው የምረዳው፡፡ እነዚህ ነገሮች በአገሬ
ምንም እንዳልጎደለብኝ፤ ትልቅ ክብር እንዳለኝ
ማረጋገጫዬ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- ለአፍሪካ ዋንጫ በብቸኛነት
መመረጥህ ክብርንና አህጉራዊ እውቅናን
አትርፎልሃል፤ በጥቅም በኩልስ ይዞልህ
የሚመጣው ነገር አለ?
በአምላክ፡- በነገራችን ላይ የዳኝነት ሙያ
ከጥቅም አንፃር የሚመዘን አይደለም፡፡ የዳኝነት
ሙያም በዋጋ አይተመንም፤ ምን አልባት
ጥቅም አለው ካልክና እንደ ጥቅም የምታስበው
የአገርህን ስም ከፍ አድርገህ ማስጠራትህንና
የህሊና እርካታ ብቻ ነው፤ እውነት ለመናገር
የዳኝነት ሙያ በገንዘብ የማይገዛ ትልቅ
እርካታን ያጎናፅፍሃል፤ በዳኝነትም ሆነ
ለአፍሪካ ዋንጫ በመመረጤ ያተረፍኩት
ትርፍ በዋናነት ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ
ውጪ ግን ወጣ ብለህ ካየኸው ምንም ጥቅም
የሌለው ነው ብዬ ባልደመድምም ሙያው
የሚያመጣው ጥቅም አለ፡፡ በተለይ በዚህን
መሰሉ አህጉራዊ ዉድድር ከፍተኛ ጥቅም
የምታገኝበት ሀቅ አለ፡፡ ለእኔ ግን ከሚገኘው
ገንዘብ ይልቅ ክብሩ እና የህሊና እርካታው
ይበልጥብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የ2017 የዘንድሮውን የአፍሪካ
ዋንጫ ፌብርዋሪ 5 ማን ካፍ አድርጎ ያነሳዋል
ብለህ ከወዲሁ ትገምታለህ?
በአምላክ፡- ከወዲሁ መተንበይ ከባድ
ቢሆንም ውስጤ ግን ይሄንን ዋንጫ ግብፅ
ታነሳዋለች እያለ ደጋግሞ ይነግረኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ
በድንቅ ችሉታው ጎልቶ ይወጣል ብለህ
ከወዲሁ ከፍ ያለ ግምትን የምትስጠው ለማን
ነው?
በአምላክ፡- ግብፆችን ከአንድም ሀለት
ጊዜ ስላጫወትኳቸውና ስላየኋቸው ነው
መሰል እሁንም ይሄንን እድል የምስጠው
ለግብፁ መሐመድ ሳላህ ነው፡፡ ለጣሊያኑ ሮማ
የሚጫወተው ሳላህ ፍጥነትን፣ ጉልበትን፣
ከድንቅ ጥበብ ጋር አጣምሮ የያዘ ተጨዋች
በመሆኑ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋጫ ልዩ
ክስተት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ዘንድሮ
አፍሪካ ከዚህ ተጨዋች ብዙ ተአምር ታያለች
ብዩ አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከታዋቂ ኤሊት ኢንተርናሽናል
ዳኞች ውስጥ የአንተ የቅርብ ሰው፤ በየጊዜው
የምትደዋወለዉና እንደ ጓደኛ የምታወራው
ኢንተርናሽናል ዳኛ ማነው?
በአምላክ፡- በሙያው ልወዳደረዉ
የምፈልገው፤ ከዚህ ባለፈ ደግሞ እንደ ቅርብ
ጓደኛ የማወራውና የማየው የዛምቢያዉ ኤሊት
ኢንተርናሽናል ዳኛ Janny Sikazwe ነው፡፡
ይሄ ዳኛ በቅርቡ የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና
ዉድድር ለይ ሳይቀር ጨዋታ የመራ ጥሩ
አቋም ያለው ዳኛ ነው፤ከእኔ ጋር ደግሞ
ቤተሰባዊ ሊባል የሚችል ቅርርብ አለን፡፡
ሀትሪክ፡- በአምላክ ገና ወጣትና ጥሩ
ብቃት ያለህ ኤሊት ኢንተርናሽናል ዳኛ
እንደሆንክ አውቃለሁ፤ እንደው የጣፋጩ
ቆይታችን ማሳረጊያ እንዲሆን መች ፊሽካህን
ትሰቅላለህ…? ይሄ ከበድ የሚል ከሆነ ደግሞ
ከዚህ በኋላ ስንት አመት ለማጫወት ታስባለህ?
የሚለው የመጨረሻ ጥያቄ ብናደርገውስ…?
በአምላክ፡- /በጣም እየሳቀ/ …እኔ እኮ
… ገና ነኝ… /አሁንም እየሳቀ/… ደግሞም
በአምላክ ይሄንን የመወሰን ስልጣን የለውም፤
ሁሉን የሚያውቀውና የሚወስነው አምላክ
ነው። ለጥያቄህ መልስ ለመስጠት ያህል ግን
ከዚህ በኋላ ስድስት አመት በጥሩ ብቃት
ማጨወት ብችል ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- በአምላክ ለነበረን ቆይታ ከልብ
አመሰግናለሁ፤ የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታህ
የተሳካ በግልህም እንደ አገርም ስምህ ከፍ
ብሎ የሚጠራበት ጥሩ ጊዜን እንድታስልፍ
ምኞቴ ነው፤ መልካም ጉዞ መልካም የአፍሪካ
ዋንጫ ቆይታ ይሁንልህ፡፡
በአምላክ፡- በእውነት ለመልካሙ ምኞችህ
እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፤ የአንተ መመረጥ
የአገር መመረጥ ነው ብለህ ለዚህ ካበቃኝ
የስፖርት ቤተሰብጋር ጋር ስላገናኘኸኝ በድጋሚ
አመሰግናለሁ፡፡