ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማሪያምና
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው:-
ዋሊያዎቹ ከፈርኦኖቹ ጋር ለሚኖራቸው ሰላማዊ ጦርነት ተመረጡ…
” ከግብጽ ጋር ተሞክሮ አለኝ ምንም ፍርሃት የለብኝም ካይሮ ላይ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን 3 ለ 1 የረታንበትን ውጤት አንረሳውም አይረሱትምም” ሲሉ አዲሱ የዋሊያዎቹ አለቃ ኢንስትራክተር ዳንኤል
ገ/ማሪያም ተናገሩ።
ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የነበረው ውል በስምምነት ከተቋጨ በኋላ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝነት ቦታ ክፍት ሆኖ ቆይቶ ከሳምንታቶች በፊት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው የተመረጡት ኢንስትራክተር ዳንኤል
ገ/ማሪያም ፌዴሬሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ ከማላዊና ከግብፅ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የሚደረገውን የ180 ደቂቃ ፍልሚያን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ ሲሾም ባህርዳር ከተማን ወደ ጠንካራ አቋም የመለሱትና የዋንጫ ተፎካካሪ ያደረጉት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛውን በምክትል አሰልጣኝነት ሾሟል። ከቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጀምሮ ሀገራዊ ጥሪ ሲቀርብለት በጎ ምላሽ የሚሰጠው የባህርዳር ከተማም ከፌዴሬሽኑ የቀረበለትን ጥያቄ በአዎንታዊ ጎኑ በመቀበል አሰልጣኙ የቀረበላቸውን አገራዊ ጥሪ መቀበሉን ማስታወቁ ሙገሳ አስችሮታል።
አዲሱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ከሹመቱ በኋላ ሲናገሩ “በጣም ተደስቻለሁ የማንኛውም ተጨዋች ሆነ አሰልጣኝ ትልቁ ግቡ የሀገሩን ባንዲራ ወክሎ መወዳደር ነው በግሌ እንኳን ሜዳ ውስጥ የሚፋለም ቡድን መምራት ቀርቶ ቡድኑን በመሪነት ይዞ መጓዝ የሚፈጥረው ኩራት ለየት እንደሚል እረዳለሁ
በሀላፊነት ታምኖብኝ በመመረጤ ፌዴሬሽኑን አመሰግናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ወክሎ ግብፅን የመፋለም እድል ቢያገኝ በደስታ እንደሚቀበለው እምነቴ ነው ከዋናው ቡድን ጋር ባይሆንም ምክትል ሆኜ ግብጾችን የገጠምንበት ጨዋታ አልረሳውም እነ አቡበከር ናስር የተካተቱበት ከ17 አመት በታች ቡድናችን ካይሮ ላይ ግብጽን 3ለ1 የረታበትን ጨዋታ አልረሳውም በተቻለ መጠን ሁለቱንም የማላዊና ግብፅ ጨዋታን ለማሸነፍ እንጥራለን በተለይ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ሆኜ ሳይሆን በተጨዋችነት ሜዳ ውስጥ ግብጽን መፋለም እመርጥ ነበር” ሲሉ ለጨዋታው የሰጡትን ትኩረት አስረድተዋል።
ስደተኛው ብሄራዊ ቡድናችን በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ታንዛኒያ ላይ ግብፅን 2ለ0 በማሸነፍ የበርካታ አመታት ደካማ ታሪክን ገደብ እንዳስበጀለት ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ካይሮ ላይ ግብፅን የረታበትን ምርጥ ውጤት የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ምክትል በመሆን ያሳኩት ኢንስትራክተር ዳንኤል
ገ/ማሪያምና ምክትላቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጋር በመሆን ካይሮ በፈርኦኖች ምድር ዳግም ታሪክ ይከስቱ ይሆን..? የሚለው የመላው ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ሆኗል።