በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ24ተኛ ሳምንት መርሐግብር ሁለተኛ ዕለት ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸዉን ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
ተመጣጣኝ በሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ቡድን ሀድያ ሆሳዕና በፈጣን የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች የተሻለ ነገርን ለመፍጠር ሲጥሩ ፤ በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ የመሐል ክፍሉን ተቆጣጥረዉ ወደ ሳጥን ለመድረስ እና ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ16ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ የኋላሸት ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ ከሜዳ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል ፤ በዚህም ተጫዋቹ በሰራዉ ጥፋት የተገኘዉን ቅጣት ምትም ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
የቁጥር ብልጫ እና የጨዋታ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ክትፎዎቹ በ29 ነኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከግራ መስመር በኩል ወደ ግብ የላከዉን ኳስ ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለ ጨርፎ አውጥቶታል። በጎዶሎ ተጫዋች ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እና በመጠኑም ቢሆንም ብልጫ የተወሰደባቸዉ ሀድያዎች በ32ተኛዉ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ብርሀኑ በቀለ ከመሐል ሜዳ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን የቅጣት ምት ኳስ ግብ ጠባቂዉ ጀማል ያዘዉ ተቆጣጥሯታል።
ከዚች የቅጣት ምት ሙከራ ከሰባት ደቂቃም በኋላም በ36ተኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አርፌጮ ከግራ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ያሻማዉን ኳስ ግርማ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ሲሆን ግብ ጠባቂዉ ጀማል ጣሰዉም ኳሷ አምልጣዉ የነበረ ቢሆንም ክትፎዎቹ እንደምንም ተረባርበዉ ኳሷን አውጥተዋል።
ከዕረፍት መልስ በተጋጣሚያቸው ላይ ያለውን የቁጥር ማነስ ተጠቅመዉ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት እና በአብዛኛው የጨዋታ ወቅት ላይ ግን በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን በችኮላ ሲያመክኑ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ69ነኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል መነሻዉን ያደረገን ኳስ አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ በቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ በሚመልስበት ወቅም በጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረዉ አቤል ነጋሽ በድጋሚ ኳሷን ወደ ግብ ቢልክም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ የግብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ በድጋሚ ኳሷን አውጥቷታል።
በተቃራኒው በአጥቂዉ ጌታነህ ከበደ ፣ የኋላሸት እና አለቤል የመሳሰሉ ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግባቸዉ የነበሩት ነብሮቹ ገና ከጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች አንስቶ በጎዶሎ ተጫዋች ሲጫወቱ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በአብዝሀኛዉ በመከላከሉ ስራ ላይ ተጠምደዉ የነበሩት ሀድያዎች በሙሉ ዘጠና ደቂቃው ግብ ሳይቆጠርባቸዉ የምሽቱ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።