*….21 ዳኞች የፊፋን ባጅ ትላንት ተረክበዋል……
የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ የአመቱን ኮከብ አርቢትር የመምረጫ መስፈርትን በአዲስ መንገድ እንደሚጠቀም አስታውቋል።
ኮሚቴው የመምረጫ መስፈርቱ ግልጽ አለመሆን ፌዴራልና ኢንተርናሽናል ዳኞች እያሉ መለየት በዳኞቹ መሃል ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን ገልጾ ይህን ቅሬታ ለማስወገድ ግልጽነት የተሞላ መመሪያ መተግበር መጀመሩን አስታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
ኮሚቴው እንደገለጸው ፕሪሚየር ሊጉ በሚካሄድባቸው ከተሞች የሚደረጉት ውድድሮች ላይ የየከተማው ኮከብ ዳኛ በመምረጥ በርካታ ጊዜ የተመረጠ ዳኛ የአመቱ ኮከብ እንሚደረግና ይህም ከሃሜት የጸዳ ስራ እንደሚሆን ያለውን እምነት ገልጿል።
በዚህም መሰረት በባህርዳር ከተማ በተካሄደው ውድድር 6 ጨዋታ ዋና ዳኛ 8 ጊዜ 4ኛ ዳኛ የነበረው ኢንተርናሽናል አርቢትር አሸብር ሰቦቃና 8 ጨዋታን በረዳት ዳኝነት የመራው ፌዴራል ረዳት ዳኛ ወጋየሁ አየለ ኮከብ ተብለው ተመርጠዋል ።
በድሬዳዋ በነበረው ውድድር ዳኞች በሁለት ዙር የተጓዙ ሲሆን በመጀመሪያው ፌዴራል አርቢትር አባይነህ ሙላትና ኡንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው በሁለተኛው ዙር ደግሞ ፌዴራል አርቢትር ቢኒያም ወ/አገኘሁና ፌዴራል ረዳት ዳኛ አብዱ ይጥና የተመረጡ ሲሆን ኮሚቴው አራቱን ዋናና ረዳት ዳኞች አወዳድሮ 7 ዋናና 4 አራተኛ ዳኛ ሆኖ የሰራው ፌዴራል አርቢትር ቢኒያም ወ/ አገኘሁና 8 ጨዋታን በረዳትነት የመራው ፌዴራል ረዳት ዳኛ አብዱ ይጥናን የድሬዳዋ ከተማ ኮከብ ብሏቸዋል። ከዚህ ምርጫ ውጤት በኋላ ኮከብ የተባሉት ወደ ቀጣይ አዘጋጅ ከተማ በቀጥታ በመሄድ ጨዋታ የሚመሩ መሆናቸው በቀጣይ አመታቶች ዳኝነቱ ወደ ጥራት የሚያዘነብል ለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። የሶስተኛ ከተማ የሆነችው አዳማ ከተማ ደግሞ ከሳምንት በኋላ የሊጉ ውድድር ሲጀመር ኮከቦቿን የምታሳውቅ ይሆናል።
በሌላ በኩል የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኙት 21 አርቢትሮች ፊፋ የላከላቸውን ባጅ ትላንት በጁፒተር ሆቴል ተረክበዋል።ባጁን በወንዶች 7 ዋናና 6 ረዳት እንዲሁ በሴቶች 4 ዋናና 4 ረዳት ዳኞች ተረክበዋል። በዚህም መሰረት በወንዶች ዋና ዳኞች በአምላክ ተሰማ፣ ዶክተር ጏይለየሱስ ባዘዘው፣በላይ ታደሰ፣ ቴዎድሮስ ምትኩ፣ ለማ ንጉሴ ፣አሸብር ሰቦቃ እና ማኑሄ ወልደፃዲቅ በሴቶች ደግሞ ሊዲያ ታፈሰ፣ ፀሐይነሽ አበበ፣መዳብ ወንድ እና
ሲሳይ ራያ ባጃቸውን ተረክበዋል። በወንዶች ረዳት ዳኝነት ትግል ግዛው፣ፋሲካ የጏላሸት፣ ይበቃል ደሳለኝ፣
ተመስገን ሳሙኤል፣ሙስጠፋ መኪና አበራ አብርደው
በሴቶች ረዳት ዳኝነት ወይንሸት አበራ፣ ወጋየሁ ዘውዱ፣ ይልፋሸዋ አየለና ብርቱካን ማሞ ባጁን መረከባቸው ታውቋል።
በዚህ ስነስርዓት ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ አዲሱ ቸፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የዳኞች ኮሚቴው ሰብሳቢ ኮሚሽነር ሸረፋ ደሌቾና ዋና ጸሃፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ተገኝተዋል።