በ26ኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ዕለት ጨዋታዎች ቀዳሚ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ኢትዮጵያ መድኅንን በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች 2 – 0 አሸንፏል ።
ኢትዮጵያ መድኅኖች በ25ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ
ፀጋሰው ድማሙ ፣ አሚር ሙደሲር እና ሐቢብ ከማልን ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና ኪቲካ ጀማን ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ። ወልቂጤ ከተማም በበኩላቸው በድሬዳዋ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ተመሳሳይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ጀማል ጣሰው ፣ ማቲያስ ወልደአረጋይ እና ኤፍሬም ዘካሪያስን በፋሪስ አሎው ፣ ብዙአየሁ ስይፉ እና አቡበከር ሳኒ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ወልቂጤ ከተማዎች በጥሩ አንዱ ሁለት ቅብብሎሽ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ኢትዮጵያ መድኅኖች በበኩላቸው በፈጣን እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል ።
- ማሰታውቂያ -
በመሀል ሜዳው ላይ ብልጫ ለመውሰድ በነበረው ጥረት የተሻሉ የነበሩት ሰራተኞቹ ከኢትዮጵያ መድኅን በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስም ችለዋል ።
በኢትዮጵያ መድኅን በኩልም በተለይም በሜዳው የግራ መስመር በኩል በፈጣን እንቅስቃሴ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ሙከራዎች ውጤታማ አልነበሩም ።
በ21ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በወልቂጤ ከተማ በኩል የተደረገ ቀዳሚ የግብ ሙከራ አጋጣሚ ነበር ።
በኢትዮጵያ መድኅን በኩልም ከደቂቃዎች በኋላ በሀቢብ ከማል ካደረጉት የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ ፋሪስ አሎውን የፈተነ የግብ ዕድል ለመፍጠር አልቻሉም ።
በወልቂጤ ከተማዎች በብዛት በቀኝ መስመር በኩል ይደረጉ የነበሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በግብ ሙከራዎት የታጀቡ አልነበሩም ።
በ34ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ሀሙ ከቆመ ኳስ ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ኑሪ ለመያዝ ሞክሮ በሰአት አጠባበቅ ስህተት ጌታነህ ጋር የደረሰውን ኳስ አጥቂው በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ቢልከውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል ።
ወልቂጤ ከተማዎች ጨናቸውን አጠናክረው በቀጠሉበት ጊዜ ላዬ አቤል ነጋሽ በ37ኛው ደቂቃ የግብ ሙከራ አድርጎ አቡበከር ኑሪ ያደነበት ኳስ እና ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ጌታነህ ከበደ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ለአቤል ለማቀበል ሲሞክር ሀቢብ መሀመድ ያወጣው ኳስ ተጠቃሽ ናቸው ።
ተመስገን በጅሮንድ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከውን ኳስ አብዱልከሪም ወርቂ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ አስቆጥሮታል ።
በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ የ1 – 0 መሪነት ተጠናቋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ግብ ያስተናገዱት ኢትዮጵያ መድኅኖች ብልጫውን ወስደው በጀመሩት የሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል ።
በ55ኛው ደቂቃ ላይ ሐቢብ ከማል በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ፈሪስ አሎው መልሶበታል ።
በ65ኛው ደቂቃ ላይም ሀቢብ ከማል ከፒተር ሳይመን ጋር በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ይዞ የገባውን ኳስ በግቡ ትይዩ ለነበረው ብሩክ ሙሉጌታ የቀነሰውን ኳስ ብሩክ ሳያገኘው ቀርቷል ።
ነገር ግን በመልሶ ማጥቃት ለመንቀሳቀስ ሲጥሩ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ70ኛው ደቂቃ ላይ 2ኛውን ግብ አስቆጥረዋል ። በድጋሚ በጌታነህ ከበደ ።
ከቀኝ መስመር በረጅም የተሻገረ ኳስ ያገኘውን ጌታነህ ከበደ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል ።
ከግቡ መቆጠር በኋላም ኢትዮጵያ መድኅኖች ተጭነው ይጫወታሉ ተብሎ ቢጠበቅም በሁለት ግብ ልዩነት መሪ የሆኑት ወልቂጤ ከተማዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት የቻሉበት እንቅስቃሴ ለማድረግ ችለዋል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ጠንካራ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።