በ26ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሀድያ ሆሳዕናን 2 – 1 ረቷል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች ባህር ዳር ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታው ሲገቡ ከለገጣፎ ለገዳዲ አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ራምኬል ጀምስን እና መሐመድ ኑርናስርን በክዋኩ ዷህ እና አብዱልከሪም ወርቁ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
ሀዋሳ ከጣለው ዝናብ ሀዋሳ በተጀመረው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የግብ ዕድሎችን ለማግኘት የጣሩበት እና ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ሁለተኛ ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡና በአማኑኤል ዮሐንስ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ከግራ መስመር የተሻገረውን እና ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በአግባቡ ሳይቆጣጠረው የቀረውን ኳስ ተጠቅሞ የቡናማዎቹ አምበል ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በፈጣን ሽግግሮች በተለይም በመስመር በኩል የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶች ተደርገዋል ።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል የኢትዮጵያ ቡናን የመጨረሻ የመከላከል መስመር መስበር የሚችሉ ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ፊት በማድረስ ሙከራዎች ለማድረግ ጥረዋል ።
ከግቡ በኋላ የተደረገው የጨዋታው ሁለተኛ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራም ወደ ግብነት ተቀይሯል ። ኢትዮጵያ ቡና ። መስፍን ታፈሰ ።
ከግራ መስመር ከሮቤል ተክለሚካኤል የተሻማውን ኳስ በመጠቀም መስፍን ታፈሰ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብ አገናኝቷል ።
በ26ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የግብ ሙከራ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ብሩክ ማርቆስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ መልሶታል ። ወድያውኑ በመልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ መስፍን ታፈሰ ለአብዱልከሪም ወርቁ ያቀበለውን ኳስ አብዱልከሪም ወደ ግብ ሞክሮ ፔፔ ሰይዶ አውጥቶበታል ።
በጨዋታ እንቅስቃሴ በኳስ የተመታው መስፍን ታፈሰ ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ በጫላ ተሺታ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል በአጋማሹ ለግብ የቀረቡበትን አጋጣሚ በፈጠሩበት ሁኔታ ላይ ተመስገን ብርሀኑ ከግርማ በቀለ የተሰነጠቀለትን ኳስ ለመጠቀም ሲሞክር በረከት ቀድሞ በመውጣት የመለሰውን ኳስ ግርማ በቀለ በድጋሚ አግኝቶ ወደ ግብ ቢሎከውም ክዋኩ ዷህ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በኢትዮጵያ ቡና የ2 – 0 መሪነት ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሳቢ ፉክክር የታየበት ሲሆን በተለይም ባዬ ገዛኸኝን ቀይረው ያስገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳዩበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተለይም በሮቤል ተክለሚካኤል የተፈጠሩ ግልፅ የግብ ዕድሎች ያመከኑበት ነበር ።
በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ተክለሚካኤል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጫላ ተሺታ በግንባር ገጭቶ ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ብሩክ በየነ ከሮቤል ያገኘውን ኳስ በማይታመን ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ጨዋታው 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ከቤራዎቹ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል ። በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘው የሄዱትን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አርፏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች አቻ ለመሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
በጨዋታው በጉዳት ምክንያት መስፍን ታፈሰን በጉዳት ያጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ተከላካያቸውን ኩዋኩ ዷህን በድንገተኛ ህመም ቀይረው ለማስወጣት ተገደዋል ። ጋናዊው ተከላካይም ህመሙ ከፍተኛ በመሆኑ በአምቡላን ወደ ሆስፒታል አምርቷል ። በምትኩም ራምኬል ጀምስ ተቀይሮ ገብቷል ።
ፈጣን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እያሳየ በቀጠለው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ቢያደርጉም የቡናማዎቹ የኋላ ክፍል በቀላሉ ለማለፍ ተቸግረው ቆይተዋል ።
በመጨረሻም ቡናማውቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሯቸውን ግቦች አስጠብቀው በመውጣት ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል ።