በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ሶስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በያዝነዉ አመት ወደ ሊጉ ያደጉት ኢትዮጵያ መድን እና ለገጣፎ ለገዳዲ ተገናኝተው መድን 4ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ተመጣጣኝ የሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴን ሲያስመለክተን የነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ገና በመባቻዉ ግብ ተስተናግዶበታል። በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ከቲካ ጀማል ከመሐል የላከዉን ኳስ በፍጥነት ሩጦ የተቆጣጠረው ሀቢብ ከማል በ9ኛዉ ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
የመጀመሪያዋ ግብ ስትቆጠር አመቻችቶ ማቀበል የቻለዉ ኪቲካ ጀማል በ12ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ የግብ ሙከራ ማድረግ ችሎም የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢሊማዋን ስታ ለጥቂት ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
ምንም እንኳን ተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር የነበረዉ ቢሆንም በሙከራ ረገድ በጥቂቱ ብልጫ የተወሰደባቸው ለገጣፎዎች በ16ኛዉ ደቂቃ ላይ ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ከርቀት አክሮሮ የመታት ኳስ ግብ ጠባቂዉን ከቡበከር ኑሪን የፈተነች ነበረች ፤ ገና በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዉ ይመሩ የነበሩት መድኖች መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል በዚህም ሀብታሙ ሸዋለም ያሻማውን ኳስ ባሲሩ ዑመር ማስቆጠር ችሏል።
አሁንም ወደ ጨዋታዉ ሪትም መመለስ ያልቻሉት የለገጣፎዎች በ32ኛዉ ደቂቃ ላይ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከሬ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ቁመተ መለሎዉ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠዉ ከኪሩቤል ወንድሙ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ቢሞክርም የግብ አግዳሚዉ መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ ተሽለዉ የተመለሱት ለገጣፎዎች የመድኑ ተከላካይ ቴዎድሮስ ኳስ በእጅ በመንካቱ ምክንያት በ48ኛዉ ደቃ ላይ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ኪሩቤል ወንድሙ አስቆጥሮ ወደ ጨዋታዉ መልሷቸዋል።
ከዚች ግብ በኋላ የአቻነቷን ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ የነበሩት ለገጣፎዎች በተቃራኒው በ74ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ተከላካዩ መዝገቡ በሰራዉ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ሲችል በጨዋታው መጠናቂቃ ደቂቃ ላይ ደግሞ እዮብ ገ/ማርያም አራተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታዉ በመድን 4ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።