የ2015 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ በቀዳሚነት ከቀን 7:00 ጀምሮ በተደረገው ጨዋታ የአምናው ሻምፕዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ መድኅንን 7 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል ።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድኀን በቋሚ አሰላለፉ አቡበከር ኑሪ ፤ አብዱልከሪም መሀመድ ፤ አስጨናቂ ፀጋዬ ፤ ተመስገን ተስፋዬ ፤ ተካልኝ ደጀኔ ፤ አሚር ሙደሲር ፤ ዮናስ ገረመው ፤ ሐብታሙ ሸዋለም ፤ ሐቢብ ከማል ፤ ያሬድ ዳርዛ እና ብሩክ ሙሉጌታ የተካተቱ ሲሆን በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ቻርለስ ሉክዋጎ ፤ ሔኖክ አዱኛ ፤ ደስታ ደሙ ፤ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ፤ ረመዳን ዩሱፍ ፤ ጋቶች ፓኖም ፤ በረከት ወልዴ ፤ ዳዊት ተፈራ ፤ ቸርነች ጉግሳ ፤ እስማኤል ኦሮ አጎሮ እና ቢንያም በላይ በቋሚ አስራ አንዱ መካተት የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን ከኋላ መስርተው በመውጣት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ። ከዚህ ባለፈ በተለያዩ አጋጣሚዎች በፈጣን እንቅስቃሴዎች ወደ ግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 10ኛው ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ አቡበከር ኑሪ ተቆጣጥሮታል ።
በኢትዮጵያ መድኅን በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ሲያደርጉ የነበረው ጥረት ውጤታማ ያልነበረ ሲሆን አንድም የግብ ሙከራም ሆነ የተጋጣሚያቸውን ተከላካይ የፈተነ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ነበር እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ የዘለቁት ።
ጨዋታው 21ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፈረሰኞቹ መሪ የሆኑበትን ግብ በግዙፉ አጥቂያቸው እስማኤል ኦሮ አጎሮ አማካኝነት አስቆጥረዋል ። ተጫዋቹ ከሳጥን ውጪ ጀርባውን ለግብ ሰጥቶ የተቀበለውን ኳስ ዞሮ ወደ ግብ በመምታት አስደናቂ ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉት ሻምፕየኖቹ ምንም እንኳን አጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ድረስ ይህ ነው የተባለ ጠንካራ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ቢቆዩም ወደ እረፍት ሲያመሩ ግን መሪነታቸውን ወደ 3 ለ 0 አስፍተው ነበር ።
በ43ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ ኦሮ አጎሮ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ከቸርነት ጉግሳ የደረሰውን ኳስ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሔኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለቸርነት ጉግሳ ቀንሶለት የነበረ ቢሆንም ቸርነት ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ከዚህ ዕድል በኋላ የተገኘውን የማዕዘን ምት ዳዊት ተፈራ ሲያሻማ የቡድኑ አምበል ፍሪምፖንግ ሜንሱ ኳሱን ካልታሰበ ቦታ በግንባር ገጭቶ ግብ ማድረግ ችሏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ3 ለ 0 መሪነት ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሰከንዶች ዕድሜ ግብ ተቆጥሮበታል ። ቢንያም በላይ ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ወደ መሀል የቀነሰለትን ኳስ ተጠቅሞ ቶጎአዊው አጥቂ እስማኤል ኦሮ አጎሮ ሀትሪክ የሰራበትን ግብ አስቆጥሯል ።
በቀጣዮቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ አሁንም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫቸውን በማስቀጠል ከኋላ ተመስርተው በሚሄዱ ኳሶች ሌሎች ግቦችንም ማግኘት ችለዋል ።
በተለይም በግራ መስመር ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ለሻምፕየኖቹ መልካም የሚባል ሲሆን ከዚሁ አቅጣጫ በተነሳ ኳስ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መሪነታቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል ።
በዚህ አጋጣሚ ቢንያም በላይ ከቸርነት ጉግሳ የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ሲሞክር በአቡበከር ኑሪ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ቸርነት ጉግሳ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
በጨዋታም ሆነ በግብ ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ መድኅኖች በ59ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን በሀቢብ ከማል አማካኝነት አድርገው ቻርለስ ሉክዋጎ በቀላሉ ተቆጣጥሮታል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በፈረሰኞቹ በኩል ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ሔኖክ አዱኛ አግኝቶ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሶ ወጥቷል ።
67ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ሁለት የኢትዮጵያ መድኅን ተከላካዮችን በማለፍ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ፀጋሰው ድማሙ በራሱ መርብ ላይ በማሳረፍ የቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነት ወደ ስድስት ለዜሮ ከፍ እንዲል አድርጓል ።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ርቀው የቆዩት ኢትዮጵያ መድኅኖች በመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ላይ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም 79ኛው ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ጠንካራ የግብ ሙከራ አድርጎ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ከተመለሰበት ውጪ ሌላ የግብ አጋጣሚን መፍጠር አልቻሉም ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን ወደ ሰባት ግብ ልዩነት ከፍ አድርገዋል ። የግቡ አስቆጣሪ ተገኑ ተሾመ ሲሆን ከሀይደር ሸረፋ በረጅም የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋለ ኢትዮጵያ መድኅኖች የማሰሰተዛዘኛ ግብ ያስቆጠሩ ሲሆን በሳጥን ውስጥ ሀቢብ ከማል ያቀበለውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ አስቆጥሯል ።
ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ7 ለ 1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ረቡዕ መስከረም 25 10:00 ላይ ኢትዮጵያ መድኅን ከአርባምንጭ ከተማ ሲጫወት ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በተከታዩ ቀን መስከረም 26 ቀን 7:00 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን የሚገጥም ይሆናል ።