በ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ መከላከያ ከአምስት ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል ።
መከላከያ በ10ኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ብቻ በማድረግ ተሾመ በላቸውን በአቤል ጌታቸው ቀይረው ሲያስገቡ በወልቂጤ ከተማ በኩል ደግሞ ከሀድያ ሆሳዕና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዳግም ንጉሴ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ በሀይሉ ተሻገር ፣ ሙሉጌታ ወልደ ጊዮርጊስ ምትክ ዋሁብ አዳምስ ፣ አበባው ቡጣቆ ፣ ፋሲል አበባየሁ እና አብዱልከሪም ወርቁን ጨዋታውን እንዲጀምሩ አድርገዋል ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በጥሩ ፉክክር ተጀምሮ ገና በአምስተኛው ደቂቃ ላይ ነበር ግብ ያስተናገደው ። ጫላ ተሺታ ከአብዱልከሪም ወርቁ የደረሰውን ኳስ በማስቆጠር ወልቂጤ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል ። ከግቡ በኋላም ጨዋታው በጥሩ መንፈስ ሲቀጥል በማጥቃቱ ረገድ መከላከያዎች የተሻለ ሆነው የታዩ ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ምንም እንኳን ከግቡ በኋላ ሌሎች ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን በሁለቱም በኩል ሳይደረጉ ቢቆይም 37ኛ ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ ተቆጥሯል ። በመከላከያ በኩል ከቅጣት ምት የመጣውን ኳስ የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ ኳሱን ለማውጣት ባደረገው ጥረት ኳሱን ያገኘው ተሾመ በላቸው ኳስን ከመረብ በማገናኘት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
የመከላከያዎች የበላይነት በግልፅ በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ኳሱን በመቆጣጠር እና በተለያዩ አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉበት ነበር ። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች የሚነጠቁ ኳሶች በፈጣን ሽግግር በመውሰድ የመከላከያን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ጥረቶችን አድርዋል ።
74ኛ ደቂቃ ላይ በመከላከያ በኩል ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ሀይሉ የወልቂጤው ግብ ጠባቂ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ቡድኑን ዳግም መሪ ያደረገ ግብ ማስቆጠር ችሏል ። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሶስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት መከላከያዎች መሪነታቸውን ከፍ ያደረጉበትን እና አሸናፊነታቸው አስተማማኝ ያደረጉበት ግብ አግኝተዋል ። ግሩም ሀጎስ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ በወልቂጤ ከተማ መረብ ላይ በማሳረፍ የጨዋታውን ውጤት ወደ 3 ለ 1 ቀይሮታል ።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 14 በማድረስ ከወራጅ ቀጠና በመውጣት ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ተሸናፊው ወልቂጤ ከተማ በነበረበት 16 ነጥብ ቢቆይም በተቆጠሩበት ግቦች ምክንያት ወደ 6ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል ።
በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ መከላከያ ወላይታ ድቻን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ቅዲስ ጊዮርጊስን የሚገጥሙ ይሆናል ።