ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ገና በመባቻዉ በሙሴ ኪሮስ አማካኝነት ሙከራ አድርገው በግብ ዘቡ ባህሩ ነጋሽ አማካኝነት ኳሱ የወጣባቸዉ አዳማዎች በ6ተኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። በዚህም ከግራ በኩል ዮሴፍ ታረቀኝ ያሻማዉን ኳስ ሙሴ ኪሮስ ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማ ገና በመባቸዉ ጨዋታውን መምራት ጀምሯል።
ገና ከጅምሩ ግብ ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ጫና ፈጥረዉ በመጫወት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ፤ ለአብነትም በሁለቱም ኮሪደሮች በኩል የተሻሙ ኳሶችን ሞሰስ ኦዶ እና በረከት ወልዴ ወደ ግብ ሞክረዉ የነበረ ቢሆንም ኳሶቹ ኢላማቸዉን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።
በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቦና አሊ የፈረሰኞቹ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ያገኘዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ወጥታለች። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ መርሐግብር አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ አማኑኤል ኤርቦ ከናትናኤል ዘለቀ እና ሄኖክ ባገኛቸዉ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ሰይድ ሀብታሙ ኳሶቹን አምክኗቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስም 54ተኛዉ ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ሁለተኛ ግብ አግኝተዋል። በዚህም በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ ቢነያም አይተን ከዮሴፍ ታረቀኝ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ቢኒያም ሳጥን ከገባ በኋላ ግብ ጠባቂዉን ባህሩ ጭምር አታሎ በማለፍ ሁለተኛ ግብ ለአዳማ ማስቆጠር ችሏል።
ምንም እንኳን ግብ አያስቆጥሩ እንጅ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ ወደ ሶስተኛዉ የሜዳ ክፍል የሚደርሱ ሲሆን በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከርቀት ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር ፤ በ77ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ጊዮርጊስ ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብ አግኝተዋል ፤ በዚህም በግራ በኩል ረመዳን የሱፍ ከተገኑ የተቀበለዉን ኳስ ለእያሱ አቀብሎት ተጫዋቹ ኳሷን ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተቀዛቅዞ የቀጠለዉ የቀን አስር ሰዓት ጨዋታም በአዳማ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
* በሊጉ በርካታ የአቻ ዉጤቶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዉ የሆነዉ ሀድያ ሆሳዕና ሀምበሪቾ ዱራሜን 2ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ምሽት አንድ ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ አማካኝነት ፊሽካ በጀመረዉ የምሽቱ ጨዋታ ገና በጅምሩ በተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያልቻሉት ሀድያዎች በአጥቂዉ ዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ጥሩ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በተመሳሳይ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ገና በጅምሩ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ሀምበሪቾዎች በ7ተኛዉ ደቂቃ ላይ በዳግም በቀለ አማካኝነት ከርቀት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም የግብ ዘቡ ፔፔ አልዛየር ኳሷን ተቆጣጥሯል።
በዚህ ሂደት ጀምሮ በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በቀጠለዉ የምሽቱ መርሐግብር ከመሐል ሜዳዉ የኳስ ቅብብል የዘለለ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ሳይደረግበት አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ በጥሩ ንቃት ጨዋታዉን የጀመሩት ሀድያዎች በ53ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማዉን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ነክታ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በግራ መስመር በኩል በምሽቱ ጥሩ በመንቀሳቀስ የተጋጣሚዉን ቡድን የተከላካይ ክፍል ሲረብሽ ያመሸዉ ዳዋ ሁቴሳ ከግራ በኩል ጥሩ ኳስ ለተመስገን ብርሀኑ አቀብሎት ተጫዋቹ በግሩም ብቃት ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ ምላሽ ለመስጠት መንቀሳቀስ የጀመሩት ሀምበሪቾዎች በ72ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በዳግም በቀለ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በድጋሚ በ78ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሀምበሪቾዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ተቃርበዉ የነበረ ቢሆንም የመሀል ተከላካዩ ቃልዓብ ዉብሸት በሚገርም ሁኔታ ከልክሏቸዋል። መደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀር ግን ነብሮቹ ሁለተኛ ግብ አክለዋል ፤ በዚህም ከኋላ ክፍል የተጣለዉን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሱን ከተቆጣጠረ በኋላ ኳሱን ገፍቶ አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂዉ ጋር ከተገናኘ በኋላ ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መርሐግብሩ በሀድያ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።