በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር የ16ተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘዉን ለገጣፎ ለገዳዲን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሰንጠረዙ አናት ከፍ ማድረግ ችሏል።
በውድድር አመቱ አጋማሽ ወደ ስብስቡ የቀላቀላቸዉን በርካታ የሚባሉ ተጫዋቾች በቋሚ አሰላለፍ ማካተት የቻለዉ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ከዛሬዉ ጨዋታ አስቀድሞ በርከት ባሉ ጨዋታዎች ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማሳካት የተቸገረዉ ሀዋሳ ከተማ ተመጣጣኝ በሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ ጨዋታቸዉን ጀምረዋል።
በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጨዋታዎች በጥቂቱም ቢሆን ለየት ያለዉ ለገጣፎ ለገዳዲ በመስመር በኩል ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ለመግባት እና አንዳች ነገር ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ ነገር ግን እምብዛም በሙከራ ረገድ አንዳች ነገርን ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በተቃራኒው ሀይቆቹ ሀዋሳ ከተማዎች የፊት መስመር አጥቂያቸውን ሙጅብ ቃሲም ኢላማ ባደረጉ ኳሶች እና አልፎ አልፎም በመስመር በኩል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ዉጥናቸዉ ሰምሮ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተመልክተናል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለው እና እምብዛም ተጠቃሽ ሙከራ ባልተደረገበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግን በ43ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል። በዚሁ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል ለገጣፎዎች የሀዋሳዉ አማካይ ኤፍሬም አሻሞ ላይ ጥፋት መስራታቸዉን ተከትሎ ተገኘዉን ቅጣት ምት ኢዮብ አለማየሁ ሲያሻማዉ ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረዉ ተከላካዮ በረከት ሳሙኤል በግንባሩ ወደ ግብነት በመቀየር ሀይቆቹ የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት እንዲያጠናቅቁ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን ለገጣፎ ለገዳዲዎች ተሽለዉ ሲመለሱ በተቃራኒው ጨዋታውን በመምራት ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ግን በጥልቀት ወደራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተዉ በመልሶ ማጥቃት ከሚገኙ ኳሶች አንዳች ነገር ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
ምንም እንኳን ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለተኛዉ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ማሳየት ቢችሉም በሙከራ ረግድ ግን የተቀዛቀዘ አጋማሽ ሆኖ ቀጥሏል። በተለይ ደግሞ ጫና ፈጥሮ ሲያጠቃ የነበረዉ ለገጣፎ በቁመተ መለሎዉ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠዉ አማካኝነት ወደ ሁለት የሚጠጉ ተጠቃሽ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ኳስ እና መረብን ግን ማገናኘት ተስኗቸው ተስተውሏል።
በሀይቆቹ በኩል የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር መሪነታቸውን አስጠብቀዉ ለመዉጣት በሚመስል መልኩ በጥልቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው በመከላከል ሰጫወቱ የነበረ ሲሆን ፤ በተለይ ደግሞ በመጨረሻዎቹ አስር ያህል ደቂቃዎች ሲፈተኑም ተስተውሏል ፤ በዚህም በጥሩ ፍጥነት ሲያጠቁ የነበሩት ለገጣፎዎች በ80ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ግብ ማግባት ዕድል አጊኝተዉ ነበር ፤ የፊት መስመር ተጫዋቹ ኢብሳ አለማየሁ ከርቀት አክሮ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂዉ ሲልሰዉ በድጋሚ ያገኘዉ ተጫዋቹ በግንባሩ ወደ ግብ ቢሞክርም ተከላካዮ ሰይድ ሀሰን እንደምንም ኳሷን ወደ ዉጭ አውጥቷታል። ከዚች ሙከራ በኋላ ምንም እንኳን አስደንጋጭ የሚባል ሙከራን አያድርጉ እንጅ ተጭነዉ ይጫወቱ የነበሩት ለገጣፎዎች በጥብቅ መከላከል ላይ የነበሩት ሀዋሳዎች ጥሰዉ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዉ በጨዋታው አንድ ለዜሮ ሽንፈት ለማስተናገድ ተገደዋል።