በአሰልጣኝ ዩርዳኖስ አባይ የሚሰለጥነዉ ድሬዳዋ ከተማ ከተከታታይ አምስት ድል አልባ ጉዞዎች በኋላ በዛሬዉ ዕለት የአሰልጣኝ ስዩም ከበደን ቡድን ሲዳማ ቡና 2ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በውድድር አመቱ ጥሩ የሚባል አጀማመር ማድረግ ችሎ የነበረዉ እና በተለይ ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉ ወደ ከተማዉ ካቀና በኋላ በጥሩ ብቃት ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ጭሞር ተስፋን አሳይቶ የነበረዉ ድሬዳዋ ከተማ በቅርብ ሳምንታት ገጥሞት ከነበረዉ የዉጤት መንገጫገጭ በመጠኑም ቢሆን ነቃ ያለበትን ዉጤት በዛሬዉ ዕለት ማስመዝገብ ሲችል በተቃራኒው ከተከታታይ አቻዎች በኋላ በተከታታይ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙትን ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በማሸነፍ መነቃቃት ላይ የነበረዉ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 22 ከፍ በማድረግ ወደ ሰንጠረዡ አናት ላይ መጠጋት የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ፊሽካ የጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ገና በመባቻዉ በ2ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል። በዚህም የድሬዳዋ ከተማዉ የፊት መሰመር ተጫዋች ያሬድ ታደሰ ከአሰጋኸኝ ጴጥሮስ የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥን ወጭ አክርሮ በመምታት አስደናቂ ግብ በማስቆጠር ክለቡ ገና በጨዋታው መጀመሪያ ላይ እንዲመራ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ሲዳማ ቡናዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በመጠኑም ቢሆን ተጭነው መጫወት ቢጀምሩም ነገር ግን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸዉ ያን ያህል በግብ ሙከራ የታጀበ ሳይሆን ቀርቷል ፤ በተቃራኒው የመሪነት ግቧን ካስቆጠሩ በኋላ በጥልቀት ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት በመልሶ ማጥቃታ ተጨማሪ ጎሎ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎችም በተመሳሳይ በጨዋታው የመጀመሪያ 25 ያህል ደቂቃዎች ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ምንም እንኳን ኢላማውን የተጠበቀ አይሁን እንጅ በአንድ ሁለት አጋጣሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ የነበረዉ ሳልሀዲን ሰይድ በ28ተኛዉ ደቂቃ ላይ ለግብ ምክንያት ለመሆን ተቃርቦ ነበር በዚህም ፤ የመስመር ተከላካዩ ይስሀቅ ለፊት መስመር አጥቂዉ ሳልሀዲን ሰይድ ያሻገረዉን ኳስ የድሬዳዋዉ ተከላካይ እያሱ ለገሰ ለመውጣት በሚሞክርበት ሰዓት ኳሷ ተጨርፋ ወደ ግብነት ልትቀየር የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ፍሬዉ ጌታሁን እንደምንም አዉጥቷታል።
ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸዉን ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ኳሶችን በአጥቂያቸዉ ሳልሀዲን እና ይገዙ አማካኝነት ሲሞክሩ የነበሩት ሲዳማዎች ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ተሻሽለዉ የተመለሱት ሲዳማዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ግብ ለሚስቆጠር ከየአቅጣጫው ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተዉሏል። በዚህም በ66ተኛዉ ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች በፈጠሩት ስህተት የተገኘዉን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ግብ ጠባቂዉ ፍሬዉ ጌታሁን እንደምንም ኳሷን ግብ ከመሆን ታድጓታል።
በተቃራኒው መሪነታቸውን አስጠብቀዉ በመልሶ ማጥቃት በሚገኙ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ጨዋታዉ ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች በቀሩበት ሰዓት ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባዉ አቤል አሰበ ከተከላካዩ አበዱለጢፍ መሐመድ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታዉን 2ለ1 በሆነ ዉጤት እንዲያሸንፍ ማድረግ ችሏል።