” ትልቅ ነክ ተብዬ በታዳጊ ቡድን ውስጥ ሳልካተት ቀርቻለሁ ”
” ኳስን መስርቶ ለሚጫወት ቡድን የሚሆን ብቃት አለኝ ”
” እግርኳስ መዝናኛዬም እንጀራዬም ነው “
መነሻውን ከአርባምንጭ ከተማ ያደረገው ወጣት በደደቢት ታዳጊ ቡድን የእግር ኳስ ህይወቱን ሀ ብሎ ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን መጫወት ችሏል ። የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ፋሲል አማረ ።
- ማሰታውቂያ -
ፋሲል ስለ እግርኳስ ህይወቱ አጀማመር እና አሁን ያለበትን ሁኔታ አጫውቶናል ፤ በሰውነቱ ግዝፈት ምክንያት በታዳጊ ቡድን ውሰጥ የመግባት ዕድሉ ተሰናክሎበት ነበር ፤ አርባምንጭ ላይ አሁን ላይ ስላለው የታዳጊዎች ሁኔታም ያለን አለ ፤ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ስለሚነሳው ከፍተኛ ገንዘብም ሀሳቡን አጋርቶናል ፤ በኢትዮጵያ ውሰጥ ማልያውን ለብሶ መጫወት የሚፈልገውን ክለብም ጠቅሶልናል ። ሙሉ ቃለ ምልልሱን እንዲህ አቀረብንላችሁ ።
ሀትሪክ – የእግርኳስ አጀማመርክ ምን ይመስላል ?
ፋሲል – እግርኳስን የጀመርኩት አርባምንጭ ከተማ ላይ ፕሮጀክት ጎዳና የሚባል አሰልጣኝ ነበረ ወጣት ነው ሰፈር ውስጥ ሰብስቦ ያሰራን ነበረ ። ወደ ሶስት አመት እሱጋር ሰርቻለሁ ። ከዛ ደደቢት ፕሮጀክት 2005 አካባቢ ለመክፈት መጡና ብዙ ልጆች ምልመላ አደረጉ ቦታው ላይ አልነበርኩም ነበረ ። ከዛ 2005 እና 2006 ከሰሩ በኋላ 2007 ላይ አሰልጣኙ አይሀለሁ ብሎኝ እዛ የሙከራ ዕድል አግኝቼ አስገባኝና አስፈረመኝ ።
ከዛ ከ2007 እስከ 2011 ድረስ በደደቢት የአርባምንጭ አካዳሚ ውሰጥ ቆየሁ ። ዋናው ቡድን የሊግ ጨዋታ ለመጫወት በመጡበት ማግስት የደደቢት ሊቀመንበር የነበረው አቶ አወል ወደ ዋናው ቡድን ትገባለክ ብሎኝ ነበር ።
በዛን ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ጨዋታ ነበረው ። ከዛ የቡና ቡድን መሪ እወስድሀለሁ ተዘጋጅ አንተ ብሎኝ ሄደ ። ከዛን ክረምት ላይ ስልክ ደወለልኝ እና ሙከራ ማየት አለብን አሉኝ ። ከዛ በሙከራው ወደ 200 አካባቢ ሰው ነበረ ከነዛ ውስጥ 50 ሰው ሲቀር መካተት ቻልኩ ። በመቀጠል መስከረም አካባቢ MRI ከታየሁ በኋላ አስፈረሙኝ ።
ከዛም በኢትዮጵያ ቡና ከ20 አመት በታች ቡድን በ2011 እና በ2012 ኮቪድ መጥቶ እግርኳሱ እስኪቆም ድረስ ስጫወት ቆይቻለሁ ።
ሀትሪክ : ከዛስ ?
ፋሲል : ከዛም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር መልቀቂያ ወስጄ ተለያየሁ እና ወደ ደባርቅ ከተማ አመርቼ 2013ን በዛው አሳለፍኩ ። ክረምት ላይ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ አሰልጣኝ ተስፋዬ አርባምንጭ መጥቶ ነበር እና ካየኝ በኋላ ወሰደኝ 2014ን በከፍተኛ ሊግ በፌዴራል ፖሊስ ላሳልፍ ችያለሁ ።
ሀትሪክ – እስካሁን የአራት ክለቦችን ማልያ ለብሰካል ። ጥሩ ጊዜ አሳልፌበታለሁ የምትለው ክለብ የትኛው ነው ?
ፋሲል – በደደቢት ከ2007 እስከ 2010 ያሳለፍኩት በጣም አሪፍ ጊዜ ነበር ። ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ እሱን ጊዜ ጥሩ የሆነ ፍቅር ነበረን ከልጆች ጋር ደሞም ጎበዝ ጎበዝ ልጆች ነበሩ ። ስብስብ ውስጥ ከነበሩት ጋር አብሬ በመጫወቴ አብሬ በመስራቴ በጣም ነበር ትልቅ ደስታ የሚሰማኝ ከዛ በኋላ ነው እግርኳስ ተጫዋች መሆንም የተመኘውት እና ጥሩ ጊዜ ለኔ ደደቢት ፕሮጀክት የሰራሁበት ነው ።
ሀትሪክ – ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለምን ተለያየክ ?
ፋሲል – MRI ለሁለት አመት ነበር የመጣልኝ ። ከዛ 2012 ግማሽ ላይ ኮቪድ መጣ ። በዛው መልቀቂያ ወስጄ ወጣሁ ። ግን የተወሰነ መቆየት ብችል ኖሮ በካሳዬ አራጌ ቡድን ውስጥ የመጀመሪያ ሰው እሆናለሁ ነበር ብዬ አስባለሁ ። አንድ ተጫዋች የራሱን ብቃት እና አቅም ማወቅ አለበት አይደል ? ኳስን መስርቶ ለሚጫወት ቡድን ደግሞ የሚሆን የሜዳ ላይ ብቃት አለኝ ብዬ አስባለሁ ።
ሀትሪክ – ለኔ ጥሩ እና በደንብ ብቃቴን አውጥቼ እጫወትበታለሁ የምትለው ቦታ ?
ፋሲል – የተከላካይ አማካይ ቦታ ነበር የምጫወተው ። ከኢትዮጵያ ቡና በኋላ ደግሞ ወደ መሀል ተከላካይ እየተመለስኩም እጫወት ነበር ። ግን በይበልጥ የተከላካይ አማካይ ቦታ በጣም የምወደው ቦታ ነው ። በፌዴራል ፖሊስ ዘንድሮ ብዙ የተጫወትኩት በተከላካይ አማካይ ቦታ ነው ግን አንዳንዴ የመሀል ተከላካይ ተጫዋቾች በተለያዩ ምክንያቶች በማይኖሩበት ጊዜ አሰልጣኙ ወደ ኋላ መልሶ ያጫውተኝ ነበር ።
ሀትሪክ – ቤተሰቦች በእግርኳስ እንድትቀጥልበት ድጋፍ ወይስ ተቃውሞ ነበራቸው ?
ፋሲል – ይደግፉኝ ነበር ። እናቴም አባቴም ኳስ ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር እና አልተጫኑኝም ኳሱን እንድጫወት ይገፋፉኝ ነበር እንደውም ። ቤት እንኳን ስቀመጥ ዛሬ ለምን አልሄድክም ልምምድ እያሉ ይጠይቁኝ ነበር ። በቃ እንጀራዬን እንድሰራ እንጂ እንዲ አታድርግ እንዲ አድርግ እያሉ አይጫኑኝም ።
ሀትሪክ – ከኢትዮጵያ ተጫዋቾች እንደ አርአያክ ወይም ሲጫወት ስታየው እንደሱ መሆን እፈልጋለሁ የምትለው ማነው ?
ፋሲል – ጋቶች ፓኖም ነው በጣም ነው የምወደው እና ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና የነበረው አሁን ለድሬዳዋ ከተማ የሚጫወተው ዳንኤል ደምሴ በጣም የማደንቀው ተጫዋች ነው ።
ሀትሪክ – ከውጪስ ?
ፋሲል – የባርሴሎናው ቡስኬት
ሀትሪክ – በእግር ኳስ እቅድክ ምንድነው ?
ፋሲል – ከፈጣሪ ጋር በአውሮፓ ውስጥ የመጫወት ትልቅ ህልም አለኝ ።
ሀትሪክ – ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ኮንትራት አለክ አሁን ?
ፋሲል – ለአንድ አመት ብቻ ነው የፈረምኩት ። ከፍተኛ ሊግ ላይ በብዛት እንደዛ ነው ። አሁን ላይ በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሙከራ ዕድል ለማግኘት እየጣርኩ ነው ።
ሀትሪክ – ስለዚህ ቀጣይ አመት ፋሲልን በፕሪሚየር ሊግ እንመለከተዋለን ?
ፋሲል – አዎ ከ70% እና 80% አካባቢ እንደዛ ነው ያሰብኩት ።
ሀትሪክ – ቀርበው ያናገሩክ ክለቦች አሉ ?
ፋሲል – አዎ በሙከራ ደረጃ እንደሚያዩኝ የነገሩኝ አሉ እና ተዘጋጅና ጠብቀን ብለውኝ እኔም በአሁን ሰአት በተገቢው ተዘጋጅቼ እየጠበኩ ነው ።
ሀትሪክ – ላንተ እግርኳስ ምንድነው ?
ፋሲል – ለኔ እግርኳስ መዝናኛዬም ነው እንጀራዬም ነው ።
ሀትሪክ – አርባምንጭ ላይ ያለው ተተኪ ታዳጊዎች የማፍራት ስራ ምን ያህል ነው ?
ፋሲል – አርባምንጭ ላይ ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ ። ከተማው ላይ በጣም ጎበዝ ጎበዝ ልጆች አሉ በፊት በፊት አሰልጣኞች መተው ያዩ ነበር ። አሁን ግን ብዙም ትኩረት አይሰጥም ወደዚህ ። እኔ አዲስ አበባ ሄጄ ስመለስ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር በጣም ጥሩ አቅም ያላቸው ልጆች አሉ ግን ዕድል ባለማግኘታቸው ሰፈር ውሰጥ ተቀምጠው ነው የሚውሉት ። ያ ነገር ያናደኛል ወደፊት ፈጣሪ ቢልልኝ ፕሮጀክት እከፍታለሉ የሚል ሀሳብ አለኝ ።
ሀትሪክ – በእግርኳስ የተከፋህበት ቀን አለ ?
ፋሲል – አዎ አለ ። የከፋኝ ቀን ደደቢት ፕሮጀክት ገና በተጀመረበት ሰዓት ሰውነቴ ግዙፍ ነው እና ትልቅ ነክ ተብዬ ከ13 እና 15 አመት በታች ቡድን መካተት ሳልችል ቀርቻለሁ ።
ሀትሪክ – ትልቅ ነህ ተብለክ ነው ሳትካተት የቀረኸው ?
ፋሲል – አው ልጅ አይደለሀም ትልቅ ነክ ብለው ሙከራ ማድረግ አትችልም አሉኝ ።
ሀትሪክ – በጣም የተደሰትክበት አጋጣሚስ ?
ፋሲል – የተደሰትኩበት ደግሞ በዛው የደደቢት ፕሮጀከት መቀላቀል የቻልኩበት እና ለትዮጵያ ቡና የፈረምኩበትን ጊዜ በጣም ነበር የተደሰትኩት ።
ሀትሪክ – በቀጣይ የእግርኳስ ዘመንክ ማልያውን ለብሼ ብጫወት የምትለው የኢትዮጵያ ክለብ አለ ?
ፋሲል – በኢትዮጵያ ውሰጥ ማልያውን ለብሼ መጫወት የምፈልገው በተስፋ ቡድን ተጫውቼ ያሳለፍኩበትን የኢትዮጵያ ቡና ዋና ቡድንን ማልያ ለብሼ ብጫወት ደስ ይለኛል ።
ሀትሪክ – ከአግርኳስ ውጪ ያለህን ጊዜ በምን ታሳልፋለክ ?
ፋሲል – ብዙ ጊዜ በቤተክርስቲያን ነው የማሳልፈው ። ወደ መንፈሳዊ ህይወት በጣም አተኩራለሁ ። ከዛም ባለፈ በፍቅር ፋሲል የሚባል ልጅ አለኝ ከሱጋር ብዙ ጊዜዬን አሳልፋለሁ ። ፈጣሪንም እሱን ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ ።
ሀትሪክ – ፋሲል በክረምቱ የዝውውር መስኮት ላይ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እየሰማን እንገኛለን ። የሚጠራው ገንዘብ ተገቢ ነው ትላለክ ?
ፋሲል – አዎ እኔ ተገቢ ነው እላለሁ ። ለምን ብትል አንድ ተጫዋች ቢጎዳ የሆነ ነገር ቢሆን የመጀመሪያው አላማው ብሎ የወጣበት ነገር ነው ከእንደገና ሌላ ነገር ውስጥ ለመግባት ብዙ ጊዜ ይፈልጋል ። ስለዚህ ተገቢ ነው እላለሁ ።
ሀትሪክ – በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልገው አካል ካለ ዕድሉን ሰጠሁክ ።
ፋሲል – ማመስገን የምፈልገው አሁን በፌዴራል ፖሊስ ያሰለጥነኝ የነበረው አሰልጣኝ ተስፋዬ ፤ በኢትዮጵያ ቡና ያሰለጥነኝ የነበረው ዮሴፍ ፤ በደደቢት ያሰለጥነኝ የነበረው አሁን በጋሞ ጬንቻ ምክትል አሰልጣኝ የሆነው መላኩን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ ።