በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሀያ ዘጠነኛ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀድያ ሆሳዕናን በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆን የቻለበትን ዉጤት አስመዝግቧል።
የውድድር አመቱን በሻምፒዮንነት ለማገባደድ ከጨዋታዉ አንድ ነጥብ ብቻ ይፈልግ የነበረዉ የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ላይ ብልጫ ወስዶ በጀመረበት የቀን ዘጠኝ ሰዓቱ መርሐግብር ላይ ፈረሰኞቹ የተሻለ ብልጫ ወስደዉ ሲንቀሳቀሱ ሲስተዋል ፤ በተቃራኒው ነብሮቹ ሀድያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ባመዘነ የጨዋታ መንገድ አልፎ አልፎ በሚገኙ ረጃጅም ኳሶች በጨዋታዉ አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታም በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዉ ተጠቃሽ ሙከራ ተደርጎበታል ፤ በዚህም ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመሐል ክፍል ወደ ፊት የተሻገረዉን ኳስ የሀድያ ተከላካዮች ወደ ዉጭ ካወጡት በኋላ ሄኖክ አዱኛ ያሻማዉን የመዓዘን ኳስ ናትናኤል ዘለቀ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
12ተኛዉ ደቂቃ ደግሞ ተከላካዩ ምኞት ደበበ በቀጥታ በረጅሙ ለኢስማኤል ኦሮ አጎሮ የጣለዉን ኳስ አጥቂዉ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ እንደምንም ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ፔፔ ሰይዶ በፍጥነት ወጥቶ ኳሷን አውጥቷታል።
በጨዋታዉ 20ኛ ደቂቃ ላይ ግን ፈረሰኞቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም አማካዩ ናትናኤል ዘለቀ ለመስመር ተጫዋቹ ቸርነት ጉግሳ ያቀበለዉን ኳስ ተጫዋቹ ከሳጥኑ ጠርዝ በቀጥታ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በ24 ተኛዉ ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ ሳጥን ዉስጥ ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ አጎሮ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ የግብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ ኳሷን ወደ ዉጭ አዉጥቷታል።
በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩ የሚመስሉት ሀድያዎች በግልፅ በተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት መስመር በመጣል በአጥቂዎቹ ፀጋየ ብርሐኑ እና ባየ ገዛኸኝ አማካኝነት አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በአጋማሹ ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብም ሆነ አደገኛ ተጠቃሽ ሙከራ ሳያደርጉ ሁለቱም ክለቦች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ይበልጥኑ ተሻሽለዉ የተመለሱት ጊዮርጊሶች ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በ49ነኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ ማጥቃት በኩል ሄኖክ አዱኛ ያሻማዉን የቅጣት ምት ኳስ ረመዳን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ሳጥን ሲያሻማ ልማደኛዉ አጥቂ ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
በ59ነኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በአብዝሀኛዉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አደጋ ለመፍጠር የቸቸገሩት ነብሮቹ ሙከራ ማዶረግ ችለዋል ፤ በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ተመስገን ብርሀኑ ከአጥቂዉ ባየ ገዛኸኝ የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር ጫናቸዉን አበርትተዉ የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በአጥቂዉ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ፣ አቤል ያለዉ እና ቸርነት ጉግሳን በመሳሰሉ ተጫዋች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ እና ግብም ሳይስተናገድባቸዉ ጨዋታዉን 2ለ0 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ አንድ ጨዋታ እየቀራቸዉ የ2015 አመት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን መሆን የቻሉበትን ዉጤት ማስመዝገብ ችለዋል።