እሁድ የካቲት 05 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚካሄደው የ2015 ሶፊ ማልት ሀዋሳ ግማሽ ማራቶን አትሌቶች ውድድር አጠቃላይ ከ400,000 ብር በላይ ሽልማት እንደሚሆን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች አሳወቁ።
ሽልማቱ ውድድሩን (ግማሽ ማራቶኑን) ከ60 ደቂቃ በታች ለሚጨርሱ ማንኛውም ወንድ አትሌቶች እና ከ70 ደቂቃ በታች ለሚጨርሱ ሴት አትሌቶች በየዘርፋቸው የሚከፋፈሉት የ100,000 ብር ሽልማትን ያካትታል። ይህንን የሰዓት ግብ የሚያስመዘግበው አንድ አትሌት ብቻ ከሆነ አትሌቱ ሙሉውን 100,000 ብር ሽልማት የሚወስድ ይሆናል። ግቡን የሚያስመዘግቡት ከአንድ በላይ አትሌቶች ከሆኑ፤ ሽልማቱ በአትሌቶቹ መካከል ይከፋፈላል።በሃዋሳው ግማሽ ማራቶን ውድድር በ10 አመታት ውስጥ የተመዘገበው ፈጣን ሰዓት 61፡53 ደቂቃ በወንዶች እና 72፡12 ደቂቃ በሴቶች መሆኑ ይታወሳል። ውጤቶቹ የተመዘገቡት በየካቲት 2014 አ.ም በባዘዘው አስማረ እና ጥሩዬ መስፍን ነው።ከላይ ከተጠቀሰው የጉርሻ ሽልማት በተጨማሪም ከአንድ እስከ ሶስት ለሚገቡት ወንድ እና ሴት አትሌቶች ሽልማቱ ካለፈው አመት በእጥፍ የሚጨምር ሲሆን አንደኛ ለሚገባ አትሌት 50,000 ብር፣ ሁለተኛ 15,000 እና ሶስተኛ 10,000 ብር ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል። እስከ አስረኛ የሚገቡ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ያገኛሉ።
ከዚህ ቀደም የማራቶን የአለም ሻምፒዮን የሆነው ታምራት ቶላ (2013 እ.ኤ.አ) እና ኬንያዊው ዊልሰን ቼቤት (2010እ.ኤ.አ) የዚህ ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸፊዎች እንደሆኑ የሚታወስ ሲሆን የዚህ አመት የውድድር ሽልማት መጠን መጨመሩ ከዚህ ቀደሙም በበለጠ ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ወደ ውድድሩ ለመሳብ የሚያግዝ ይሆናል ሲሉ የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል።