በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ7ተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታቸውን ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት አጠናቀዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ምንም እንኳን በሁሉም ረገድ የቅዱስ ጊዮርጊስን የበላይነት የተመለከትን ቢሆነም ቀዳሚዋን ሙከራ በማድረግ ግን የገብረ ክርስቶስ ቢራራዉ ቡድን ቀዳሚ ነበር ፤ በዚህም በ12ኛዉ ደቂቃ ላይ ከመሐል ክፍል የተሻገረለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በጥሩ ዕይታ ለኋላሸት ሰለሞን አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ኳሷን አምክኗታል።
በ34ኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም ያቀበለዉን ኳስ የፊት መስመር አጥቂዉ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥኑ ሲያሻግር ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረዉ የመስመር ተጫዋቹ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። በድጋሚ በ37ኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ከሄንክ አዱኛ የተቀበለውን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግራ ዕግሩ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ለጥቂት ወደ ዉጬ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
በአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ ክትፎዎች ድንቅ ግብ የማግባት አጋጣሚ አግኝተዉ ነበር በዚህም ከመሐል ክፍል የተሻገረለትን ኳስ አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ በጭንቅላት ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ ቻርልስ በሚመልስበት ሰዓት በአቅራቢያው ይገኝ የነበረዉ አቡበከር ሳኒ በድጋሚ ሲሞክር የፈረሰኞቹ ተከላካዮች እንደምንም ኳሱን አዉጥተዉታል።
ከዕረፍት መልስ ፈረሰኞቹ የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠናክረዉ ወደ ሜዳ ቢገቡም በ55ኛዉ ደቂቃ ላይ በክትፎዎች በኩል ለግብ የቀረበ ሙከራ ተመልክተንበታል። በዚህም ጌታነህ ከበደ ያሻማውን ኳስ የኋላሸት ሰለሞን በጭንቅላቱ ግጭቶ ቢሞክርም ግብ ጠባቂዉ ሲመልስ ተጨራርፋ የተገኘችዉን ኳስ አቡበከር ሳኒ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች እንደምንም አዉጥተዉታል።
በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ ክትፎዎቹ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ ማግኘት ችለዋል። በዚህም በዕለቱ ኳስን በዕግሩ በመጫወት ረገድ ደካማ የነበረዉ ግብ ጠባቂዉ ቻርልስ ሉክዋጎ በትክክል ያላራቃትን ሷስ አቡበከር ሳኒ አግኝቶ ግብ በማስቆጠር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አጥቂው ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በጭንቅላቱ በመግጨት ለራሱም ለክለቡም ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት ፈረሰኞቹ በ90+2 ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም መሰረት የመስመር ተከላካዩ ሱለይማን አህመድ ያሻማውን ኳስ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። በዚህም የ6ተኛዉ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ 2አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።