የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መጋቢት 23 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አራት በመሸናነፍ ቀሪ ሶስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 17 ጎሎች ተቆጥረዋል። አንድ ጨዋታ(የባህር ዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ) በተጫዋች አለልኝ አዘነ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። 19 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ የተመዘገበ ቀይ ካርድ የለም።
በሳምንቱ በስድስት ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። በረከት ግዛው(ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)፣ ብሩክ ሙሉጌታ(ኢትዮጵያ መድን)፣ በረከት ሳሙኤል (ሃዋሳ ከተማ)፣ ቢንያም አይተን(አዳማ ከተማ) እና አማኑኤል ኤረቦ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) በሳምንቱ ጨዋታ አምስተኛ የጨዋታ ቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ሲወሰን ማይክል ኔልሰን /ሻሸመኔ ከተማ – ተጫዋች/ ክለቡ ከ ሲዳማ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ከዳኛውና ከረዳት ዳኞች እይታ ዉጪ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን ገፍትሮ ከጣለው በኋላ እግሩን ረግጦት የሄደ መሆኑን ሪፖርት በመደረጉ በፈጸመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት 4/አራት ጨዋታ እንዲታገድና ብር /3000/ ሶስት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።