ላለፉት ሶስት አመታት ቤትኪንግ ከተሰኘዉ አቋማሪ ድርጅት ጋር በጋራ አብሮ ሲሰራ የነበረዉ እና ከወራት በፊት ደግሞ በጋራ ስምምነት ዉሉን ያፈረሰዉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አሁን ደግሞ ከሁሉ ስፖርት አቋማሪ ድርጅት ጋር አዲስ የአጋርነት ስምምነት ፈፅሟል።
በዚህም በሁለቱ አካላት መካከል ከተደረሱት ስምምነቶች መሀል ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት በዉድድሩ ላይ ክለቦች ጨዋታቸውን የሚያደርጉት በሁሉ ስፖርት በተዘጋጀችዉ ኳስ ሲሆን በተጨማሪም በጨዋታ ዕለት ለሚኖሩ የውድድር አመራሮች ፣ ኳስ አቀባዮች ፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና መሰል አካላቶች የሚጠቀሟቸዉ ግብአቶች ማለትም ትጥቆች ከሁሉ ስፖርት የተዘጋጁ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁሉ ስፖርት በገንዘብ አምስት ሚሊየን ብር እንዲሁም በአይነት ስድስት ሚሊየን ብር በድምር አስራ አንድ ሚሊየን ብር ለሁለት አመታት ለአክሲዮን ማህበሩ እንደሚከፍል ቦሌ አካባቢ በሚገኘዉ ራማዳ ሆቴል በተከናወነዉ ስምምነት ላይ ተገልጿል።