*….. ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተፈጸመው የስያሜ
መብት ስምምነቱ ይፋ አልተደረገም….
*….. የሽልማቱ ገንዘብም መቀራረብ አነጋጋሪ ሆኗል…
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የአመቱ የሊፕሪሚየር ሊጉን የመዝጊያና የሽልማት ስነስርዓት በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በደማቅ ስነስርዓት አካሂዷል።
- ማሰታውቂያ -
በርካታ ታዳሚ በተገኘበት በትላንት ምሽቱ መርሃ ግብር በአመቱ በሊግ ውድድር የተካፈሉ 16 ክለቦች የሽልማት ክፍፍል ያደረጉ ሲሆን የገንዘቡ ሽልማት ተቀራራቢነት ግን ጥያቄ የፈጠረ ሆኗል። በአመቱ የዋንጫ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሁለተኛ በሆነው ባህርዳር ከተማ መሃል ያለው ልዩነት ከ300 ሺህ ብር አለመብለጡ የተገኘውን ብር የማዳረስ ስራ የተሰራ አስመስሎታል የሚሉ ቅሬታዎች ተደምጠዋል።
በሊጉ ውሳኔ መሰረት አሸናፊዎቹ ፈረሰኞቹ 12 ሚሊዮን 983 ሺህ ሁለተኛው ባህርዳር ከተማ 12 ሚሊዮን 724 ሺህ ለሶስተኛው ኢትዮጵያ መድን 12 ሚሊዮን 464 ሺህ ብር ተሰጥቷቸዋል። አራተኛ ለሆነው ኢትዮጵያ ቡና 12 ሚሊዮን 204 ሺህ ብር፣ ለአምስተኛው ፋሲል ከነማ 11 ሚሊዮን 945፣ ለስድስተኛው ሀድያ ሆሳዕና 11 ሚሊዮን 685 ሺህ፣ ለሰባተኛው ለሀዋሳ ከተማ 11 ሚሊዮን 425 ሺህ ፣ ለስምንተኛው አዳማ ከተማ 11 ሚሊዮን 166 ሺህ ተሰጥቷል። ለዘጠነኛው መቻል 10 ሚሊዮን 906 ሺህ ብር፣ ለአስረኛው ድሬዳዋ ከተማ 10 ሚሊዮን 646 ሺህ ብር፣ ለአስራ አንደኛው ሲዳማ ቡና 10 ሚሊዮን 387 ሺህ ብር ፣ ለአስራ ሁለተኛው ወላይታ ድቻ 10 ሚሊዮን 127 ሺህ ብር ፣ ለአስራ ሶስተኛው ወልቂጤ ከተማ 9 ሚሊዮን 867 ሺህ ብር እንዲሰጥ ተደርጓል።
ወራጅ ክለቦች ለሆኑት ሶስቱ ክለቦችም የድርሻቸውን ያገኙ ሲሆን አስራ አራተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከተማ 9 ሚሊዮን 608 ሺህ ብር፣ አስራ አምስተኛው ለገጣፎ ለገዳዲ 9 ሚሊዮን 348 ሺህ ብር የመጨረሻው አስራ ስድስተኛው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 9 ሚሊዮን 088 ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል። ሊግ ኩባንያው በዚህ የክለቦቹ ክፍፍል 176 ሚሊዮን 581 ሺህ ከ125 ብር ወጪ ማድረጉ ታውቋል።
በሀያት ሪጀንሲው ፕሮግራም የአመቱ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው የቅ/ጊዮርጊሱ ቢኒያም በላይ 210 ሺህ ብርና ዋንጫ ተሸልሟል። በሽልማቱም መድረክ ላይ
” በተገኘው ድል የክለቡን ቦርድ ደጋፊዎችና አሰልጣኞች እንኳን ደስ አላችሁ በዚህ አመት ከባድ ጊዘዜ አሳልፈናል በአንድነታችን የተገኘ ድል ነው 16ኛ ዋንጫ ስላገኘን እንኳንም ደስ አላችሁ ኮከብ በመባሌም ደስ ብሎኛል ያለናንተ አይሳካም ነበር ኮከብ እንድባል ድምጽ የሰጣችሁኝ የኛ ደጋፊዎችና የተጋጣሚ ቡድኖች ደጋፊዎችን አመሰግናለሁ” ብሏል። የተጨዋቹ ባለቤትም ” አንተ ለኔ ሁሌም ኮከብ ነህ ” ብላ አሞግሳዋለች።
የአመቱ ኮከብ አሰልጣኝነት ክብር አግኝቶ ዋንጫና 200 ሺህ ብር የተሸለመው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ “ብዙ ውጣ ውረድ አልፈን 16ኛውን ዋንጫ ስላገኘን እንኳን ደስ አላችሁ 16 ቱም አሰልጣኞች ለማሸነፍ አቅደን የተሳካልኝ ለኔ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ቤተሰቦቼ ልጆቼና ባለቤቴ ደጋፊዎቼ የቦርድ አመራሮችን እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት ተናግሯል።
የአመቱ ተስፈኛ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠውና 150 ሺህ ብር የተሸለመው የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ታረቀኝ
“በእናንተ ፊት እንድሸለም ያደረገኝ ፈጣሪን አመሰግናለሁ
እናትና አባቴ ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞቼና አፈወርቅና ይታገሱ በአመራር ደረጃ የነበሩት አቶ አንበስ በሙሉ አመሰግናለሁ
ከሰሞኑ አሜሪካ ሀገር ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ብሄድም በፈጸምኩት አሳዛኝ ድርጊት እንድመለስ በመደረጉ ላዘናችሁብኝ ኢትዮጵያዊያን ይቅርታ እጠይቃለሁ በቀጣይ ተስተካክዬ አገሬን እንደምረዳ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለት በደማቅ ጭብጨባ የታጀበ ንግግር አድርጓል። የአመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ የተመረጠውና 150 ሺህ ብር የተበረከተለት የኢትዮጵያ መድኑ አቡበከር ኑራ በበኩሉ “ይሄ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው የረዱኝን ሁሉ አመሰግናለሁ አሰልጣኜ ገብረ መድህን ኃይሌንም አመሰግናለሁ እሱ ለኔ አሰልጣኝ ብቻ አይደለም እናቴም ሁሌ ከጎኔ ነች እሷንም አመሰግናለሁ” ሲል ተናግሯል።
ከዘጠኝ አመት በኋላ የአመቱ ኮከብ የተባለውና 105 ሺህ ብር ከዋንጫ ጋር የተበረከተለት ፌዴራል ዳኛ ቢኒያም ወ/አገኘሁ በበኩሉ “ለኔ ከባድ አመት ነበር ጥሩ ውድድር መርቻለሁ እግዚአብሄር ፈቅዶ በማሸነፌ ደስ ብሎኛል ባለቤቴን አባቴ ቤተሰቦቼን የሙያ ጓደኞቼን አመሰግናለሁ” ሲል ለሁለተኛ ተከታታይ አመታት ኮከብ ተብሎ ተመርጦ 105 ሺህ ብር የተበረከተለት ኢንተርናሽናል ረዳት አርቢትር ትግል ግዛው በበኩሉ
” ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጩ በማሸነፌ ደስ ብሎኛል ለዚህ ድል በመብቃቴ ቤተሰቤን፣ ፌዴሬሽኑን፣ የብሄራዊ የዳኞች ኮሚቴን፣ አብረውኝ የለፉትን ጓደኞቼን በሙሉ አመሰግናለሁ” በማለት ተናግሯል።
የሊግ ኩባንያው አመራሮች ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ መሰረት በምሽቱ ሲጠበቅ የነበረው የሊጉ የስያሜ መብት የሚሸጥበት ስምምነት ግን ሳይካሄድ መቅረቱ መነጋገሪያ ሆኗል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት የስያሜ መብቱን በ300 ሚሊዮን ብር መግዛቱ የተነገረ ሲሆን የወረቀት ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቃቸው ስምምነቱ በምሽቱ ይፋ አለመደረጉ ታውቋል።
በምሽቱ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ እና ሚኒስትር ደኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነትና ሴሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።