ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 29ኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎቹ !
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 29ኛ ሳምንት በአዳማ ከተማ በተደረጉ ጨዋታዎች ሰባት ጨዋታዎች በመሸናነፍ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 18 ጎሎች ተቆጥረዋል።በሳምንቱ 19 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ ሁለት ተጫዋቾች ቀይ ካርድ ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰኞ ሰኔ 26 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ግጥሚያ(ዎችን) ጨምሮ ሌሎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ ውጤት በማፅደቅ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።
- ማሰታውቂያ -
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች 6 ተጫዋቾችና ላይ ቅጣት ተላልፏል። ሱሌማን ትራዎሬ(ለገጣፎ ለገዳዲ) የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድ ና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ፥ በረከት ሳሙኤል (ሃዋሳ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድ፥ እንየው ካሳሁን(ድሬደዋ ከተማ)፣ እያሱ ለገሰ(ድሬደዋ ከተማ)፣ ተባረክ ሔፋሞ (ሃዋሳ ከተማ) እና ዓለምብርሀን ይግዛው(ፋሲል ከነማ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም በሁለት ክለቦች የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። አርባ ምንጭ ከተማ በነበረው የ29ኛ ሳምንት እግርኳስ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የጨዋታ አመራሮችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበ የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት ደጋፊዎቹ ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 75000/ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ፥ ሲዳማ ቡና ለነበረው የ29ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ ቅድመ ስብሰባ ላይ የቡድን መሪው ስላለመገኘቱ ሪፖርት ቀርቦበት በፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ክለቡ ብር 5000/አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ወስኗል።