በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 የ28ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተደረጉ ሲሆን 6 ጎሎች በ5 ተጫዋቾች ተመዝግበዋል። በሁለቱ ጨዋታዎች 8 ቢጫ ካርድ እና አንድ ቀይ ካርድ(በሁለተኛ ቢጫ) ለተጫዋቾች ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰኞ ሰኔ 19 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ግጥሚያ(ዎችን) ጨምሮ ሌሎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ውጤት በማፅደቅ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።
በተጫዋቾች በኩል አለልኝ አዘነ(ባህርዳር ከተማ) ክለቡ ከ ሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው የ28ኛ ሳምንት እግርኳስ ጨዋታ በ 63 ኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድ ተወስኗል።
ሐሙስ ሰኔ 22 2015 የሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች በእኩል ሰዓት እንዲደረጉ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ወስኗል። በዚህም በፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ ክፍል አምስት አንቀፅ 26 ቁጥር 6 መሰረት አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬደዋ ከተማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከ ወልቂጤ ከተማ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታድየም ከቀኑ በ09:00 ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል።