በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሀያ ዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ወላይታ ዲቻ እና ወልቂጤ ከተማ መርሐግብራቸዉን ያለ ግብ በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
በዉጤት ደረጃ ለሁለቱም ክለቦች እጅግ አስፈላጊ በነበረዉ የዕለቱ ተጠባቂ መርሐግብር ሁለቱም ክለቦች ጥንቃቄ ላይ መሰረት ያደረገን የጨዋታ መንገድ ለመከተል ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን በተለይ ወላይታ ዲቻ በርከት ያሉ ተጫዋቾቹን በጉዳት ምክንያት እንደማጣቱ ምክንያት በሜዳ ላይ የነበረዉ እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር ብሎ ማንሳት ይቻላል።
በዚህ ሂደት በጀመረዉ ጨዋታም ክትፎዎቹ ገና በጨዋታው መባቻ በ6ተኛዉ ደቂቃ ላይ ጥሩ የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዉ ነበር በዚህም ፤ ሳሙኤል አስፈሪ ከቀኝ መስመር ያሻማዉን ኳስ የኋላሸት ሰለሞን በሚገርም ሁኔታ በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሷን አውጥቷታል።
- ማሰታውቂያ -
ከዚች ሙከራ በኋላ አሁንም በጀመሩበት መንገድ ጨዋታቸዉን የቀጠሉት ወልቂጤዎች በ25ተኛዉ ደቂቃ ላይ በድጋሚ ድንቅ የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል ፤ በዚህም አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ ከግራ በኩል ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ብዙአየሁ ሰይፈ በጭንቅላቱ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራ ረገድ በመጠኑም ቢሆን በወልቂጤዎች ብልጫ የተወሰደባቸዉ ዲቻዎች በአጋማሹ በቃልኪዳን ዘላለም እና ያሬድ ከበደ አማካኝነት ያደረጓቸዉ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ ማለት ይቻላል ። የተለየ አቀራረብ ወደ ሜዳ ይዘዉ የገቡት እና ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት ክትፎዎቹ በአጋማሹ መጠናቀቂያ 45ኛ ደቂቃ ላይ በአጥቂያቸዉ ጌታነህ ከበደ አማካኝነት ጥሩ የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን በማጥቃት እንቅስቃሴያቸዉ ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት ዲቻዎች በፊት መስመር ተጫዋቾቻቸዉ ቃልኪዳን ዘላለም እና ያሬድ ዳዊት አማካኝነት በድጋሚ ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ዕድሉን ግን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ላይ በ74ተኛዉ ደቂቃ ከወልቂጤ የቀኝ ማጥቃት በኩል ከአቡበከር ሳኒ የተሻማዉን ኳስ አቤል በሚገጭበት ወቅት ያሬድ ታደሰ የተጫዋቹን መለያ በመጎተቱ ምክንያት የተሰጠዉን የፍፁም ቅጣት ምት አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ከፍፁም ቅጣት ምቱ መሳት በኋላ የተረበሹ የሚመስሉት እና ግብ ለማስቆጠር ወደ ጥድፊያ የገቡት ክትፎዎቹ ረጃጅም ኳሶች ከየአቅጣጫው ፊት መስመር ላይ ለሚገኙት ተጫዋቾች በመጣል አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ነገር ግን ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በመጨረሻም በ90ኛዉ ደቂቃ ላይም ከቀኝ መስመር በኩል አቡበከር ሳኒ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ዉጭ ወጥታለች። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የዕለቱ ተጠባቂ መርሐግብርም ምንም አይነት ግብ ሳይስተናገድበት 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል ፤ ዉጤቱን ተከትሎም ወላይታ ዲቻ በሊጉ መሰንበቱን ሲያረጋግጥ በተቃራኒው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በሊጉ ለመቆየት የ30ኛ ሳምንት መርሐግብሩን እንዲጠብቅ ሁኗል።