በሊጉ የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ሀዋሳ ከተማን አሸንፏል ።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በ19ኛው ሳምንት በባህርዳር ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አምስት ለውጦችን አድርገው ገብተዋል ። አሳንቴ ጎድፍሬድ ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ አቤል አሰበ እና ሄኖክ ሀሰን ምትክ
መሳይ ጳውሎስ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ጋዲሳ መብራቴ በመጀመሪያው አሰላለፍ ተካተዋል ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ ወልቂጤ ከተማን ከረቱበት ጨዋታ ሶስት ለውጦችን በማድረግ በመድኃኔ ብርሀኔ ፣ አዲሱ አቱላ እና ሙጂብ ቃሲም ምትክ አብዱልባሲጥ ከማል ፣ ዳንኤል ደርቤ እና እዮብ አለማየሁ በምርጥ 11 አካተዋል ።
ቀዝቀዝ ባለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ በአንፃራዊነት ሀዋሳ ከተማዎች የተሻሉ ሆነው የታዩበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
ድሬዳዋ ከተማዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ፊት ለመድረስ ጥረት ከማድረጋቸው ውጪ ይህ ነው ሊባል የሚችል ዕድል አልፈጠሩም ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁነኛ የፊት አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም አለመኖር በተወሰኑ መልኩ በማጥቃት ላይ ክፍተት እንደፈጠረባቸው ማሳያዎች ነበሩ ።
በጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራ በ17ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን አሊ ሱሌማን የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮችን አልፎ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ያደረገው ጥረት ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።
ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ኤርትራዊው አጥቂ አሊ ሱሌማን ከበቃሉ ገነነ የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽን ግብ ሳይቆጠርበት 0 – 0 ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው የታዩት ደግሞ ድሬዳዋ ከተማዎች ነበሩ ። ብርቱካናማዎቹ የተሻለ ጫና ፈጥረው በጀመሩት አጋማሽ የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ መስመር ለመፈተን ጥረቶች አድርገዋል ።
በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይም ጋዲሳ መብራቴ እና ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ በቀላሉ ተይዘዋል ።
የጨዋታው ደቂቃ 71 ላይ በደረሰበት ወቅት በጨዋታው እጅግ ለቀረበው የግብ ሙከራ የታየበት ነበር ። በአጋጣሚው ቻርለስ ሙሴጌ ለዳዊት እስጢፋኖስ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ።
በአጋማሹ ተቀዛቅዘው የታዩት ሀይቆቹ በአዲሱ አቱላ እና አሊ ሱሌማን ካደረጓቸው ኢላሚቸውን ካልጠበቁ ኳሶች በቀር ጠንካራ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ።
በ78ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎችን ጥረት ፍሬ አፍርቷል ። ኤልያስ አህመድ በሀዋሳ ከተማ የግራ መስመር አቅጣጫ በሚገኘው የሳጥኑ ክፍል ይዞ የገባውን ኳስ ከበረኛው ላይ ከፍ አድርጎ በማሳለፍ ለአቤል ከበደ የደረሰው ኳስ ድሬደዋ ከተማን መሪ አድርጓል ።
በቀጣዮቹ የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የነበሩት ጥረቶች ደካማ መሆንም ሙሉ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ 1 – 0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል ።
ውጤቱንም ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ነጥቡን 27 በማድረስ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በ31 ነጥብ በነበረበት የአራተኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ረቡዕ ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከተማን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ በዕለተ አርብ ከቀን 9:00 ጀምሮ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥም ይሆናል ።