በአስራ አምስት ነጥቦች እና ሰባት ደረጃዎች ተበላልጠው አንደኛ እና ሰባተኛ ደረጃ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ባደረጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ፈረሰኞቹ አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል።
በርከት ባሉ ተጓዥ ደጋፊዎች ሞቅ ያለ ድባብ ታጅቦ በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች በንፅፅር ፈረሰኞቹ የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸውን በመጠቀም ወደ አፄዎቹ ሳጥን ለመግባት ሲሞክሩ በተቃራኒው አፄዎቹ በሜዳዉ የመሐል ክፍል እና በግራ በኩል ባዘነበለ የማጥቃት መስመራቸው በጨዋታው ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተመልክተናል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም ገና በጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመሐል ተከላካይ ምኞት ደበበ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት በሄኖክ አዱኛ ተቀይሮ ወጥቷል። በ20ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ሱለይማን ሀሚድ ያሻማውን የማዕዘን ኳስ አቤል በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ሚኬኤል ሳማኬ እንደምንም ኳሷን ግብ ከመሆን ታድጓታል።
በ29ነኛዉ ደቂቃ ላይም ከመሐል ሜዳዉ ጨረቃ አካባቢ የተገኘዉን ቅጣት ምት መናፍ አወል ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቃዉ ቻርልስ በቀላሉ ኳሷን ተቆጣጥሯታል። በአጋማሹ እምብዛም ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ወይም ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩት አፄዎቹ በአጋማሹ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከሞከራት ሙከራ ውጭ ተጨማሪ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠናክረዉ የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ ጊዜ ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል መድረስ ችለዉ የነበረ ቢሆንም በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ወሳኝ ተጫዋቻቸዉ የሆነዉን አማካዩ ጋቶች ፓኖም በሽመክት ጉግሳ ጥፋት ተሰርቶበት ተጎድቶ ከሜዳ ወጥቷል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ71ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል። በዚህም ከሱለይማን ሀሚድ የተቀበለውን ኳስ አቤል ያለዉ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ለእስማኤል ኦሮ አጎሮ አቀብሎት አጥቂዉ በፍጥነት ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም አፄዎቹ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ተጭነዉ በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ሲያደርጉት የነበረዉ ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ በወሳኙ ጨዋታ በቅ/ጊዮርጊስ 1ለ0 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።