በሀያኛው ሳምት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ የአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ቡድን ባህርዳር ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲ 3ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ዘንድሮ ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሁኖ የቀረበዉ ባህርዳር ከተማ በሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጦ እና በተቃራኒው በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጦ ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘዉ የአሰልጣኝ ዘማርያም ቡድን ለገጣፎ ለገዳዲ ባደረጉት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ባህርዳር ከተማ የጨዋታው የበላይ ሁኖ ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በተለይ በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት እና አልፎ አልፎ በሚገኙ ቅፅበቶችም በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ የነበሩት ለገጣፎች በማጥቃቱ ረገድ ያን ያህል ባይሳካላቸውም በመከላከሉ ግን በተለይ የመጀመሪያቹን 30 ያህል ደቂቃዎች የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በ33ተኛዉ ደቂቃ ላይ ፍራኦል መንግስቱ የጣና ሞገዶቹን ቀዳሚ ሊያደርግ የሚችል ድንቅ ሙከራን ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም በግብ ዘቡ ሚኪያስ መክኖበታል። ከዚች ለግብ የቀረበች ሙከራ በኋላ ተጭነዉ መጫወት የቻሉት ባህርዳሮች በ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በ41ነኛዉ ደቂቃ ላይ ፉአድ ፈረጃ ከመዓዘን ያሻገረዉን ኳስ ፋሲል አስማማዉ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት በመጠኑም ቢሆን በማጥቃት ሂደቱ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ለገጣፎዎች በተቃራኒው በ68ተኛዉ እና 71ኛዉ ደቂቃ ተከታታይ ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል።
በዚህም በመጀመሪያ በዕለቱ ድንቅ ከነበረዉ ፉአድ ፈረጃ የተሻገረለትን ኳስ አለልኝ አዘነ ወደ ግብነት ሲቀይር በተመሳሳይ አማካዩ የአብስራ ተስፋየ ደግሞ ድንቅ የቅጣት ምት በማስቆጠር የክለቡን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ላይም ባህርዳር ከተማ ጨዋታውን አቀዝቆዞ በመጫወት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥር በተቃራኒው ለገጣፎ በጨዋታዉ መገባደጃ ወቅት የማስተዛዘኛ ግብ በገብርኤል አህመድ አማካኝነት አስቆጥሮ ጨዋታው በባህርዳር 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ዉጤቱን ተከትሎም የጣና ሞገዶቹ በ42 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲመቀመጡ በጨዋታው ሽንፈት የገጠመዉ ለገጣፎ ለገዳዲ ደግሞ በ10 ነጥቦች እና 35 የገብ ዕዳ የሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።