በአምስት ነጥቦች እና አምስት ደረጃዎች ተበላልጠው አስራ ሁለተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዉ የ20ኛዉን የመጀመሪያ ጨዋታ የከወኑት አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታቸውን አንድ አቻ በሆነ ዉጤት አገባደዋል።
በአስራ ስምንተኛዉ የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ በሀድያ ሆሳዕና ተሸንፎ በተመሳሳይ ደግሞ የመዲናዉ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን ከሲዳማ ቡና ጋር ያለ ግብ በአቻ ዉጤት አጠናቆ እንደመምጣቱ ሁለቱም ቡድኖች መርሐግብሩን በሶስት ነጥብ ለመደምደም በሚመስል መልኩ ብርቱ የሜዳ ላይ ፉክክር ሲያደርጉ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በተለይ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋየ ቡድን ኢትዮጵያ ቡና የሜዳውን የመሐል ክፍል እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና አልፎ አልፎም የመስመር ተጫዋቾቹን በመጠቀም ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ በጨዋታው ቀዳሚ የሚያደርገውን ግብ ለማግኘት ሲጥር ፤ በተቃራኒው ከጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃ እንስቶ በይበልጥ በመከላከሉ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የነበረዉ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ከኋላ ለፊት መስመር ተጫዋቾቹ ኤሪክ ካፓይቶ እና ተመስገን ደረሰ በሚጥሏቸዉ ረጃጅም ኳሶች ግብ ለማስቆጠር የነበራቸዉ ጥረት ፍሬ አፍርቶ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅት በተመስገን ደረሰ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በቶሎ የአቻነት ግብ ለማግኘት ያላቸውን ሀይል በሙሉ አሟጠዉ ሲጫወቱ የነበሩት ቡናማዎቹ በተቃራኒው ያገቡትን ግብ አስጠብቀዉ ለመዉጣት መከላከሉ ላይ የተጠመዱት አርባምንጮች ከተማዎች ላይ ጫናቸዉን በይበልጥ አስቀጥለዉ በ59ኛዉ ደቂቃ ላይም አማኑኤል ዮሐንስ ከመሐል ያቀበለውን ኳስ መሐመድ ኑር ናስር ግብ ጠባቂዉን በማለፍ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
በተለይ ቡናማዎቹ በቶሎ የአቻነት ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በሂደት ሀይልን የቀላቀል የአጨዋወት መንገድ መከተል የጀመሩት አዞዎቹ በ75ኛዉ ደቂቃ ላይ በአንዳልካቸዉ መስፍን አማካኝነት ከሳጥኑ ዉጭ ለግብ የቀረበ ድንቅ ሙከራን ቢያደርጉም ኳሷን ሕዝቄል ሞራኬ አውጥቷታል። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።