በእስካሁኑ የውድድር አመት ሁለቱም ጠንካራና ደካማ ጉዞ እያደረጉ ቢሆኑም የሁለቱ ቡድኖች አቋም ምንም ይሁን የደርቢ ፍልሚያ እንደመሆኑ ተጨዋቾቹ ለራሳቸው ድል ለክለባቸው የበላይነትና ለደጋፊዎቻቸው ደስታ የሚያደርጉት ፍልሚያ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት የተቸረው ሆኗል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በእስካሁኑ 7 ጨዋታ 5 ጊዜ ረትተው አንድ ጊዜ ተሸንፈው አንድ ጊዜ አቻ ወጥተው በ16 ነጥብና 10 ግብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ነገ ካሸነፉ በቀጥታ ሁለተኛ ደረጃን የሚይዙ በመሆኑ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል ። በእስካሁኑ 7 ጨዋታ 2 ጊዜ ረትተው 3 ጊዜ ተሸንፈው 2 ጊዜ አቻ በመውጣት በ8 ነጥብና 2 የግብ ዕዳ 13 ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን ማሸነፍ በቀጥታ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ፍልሚያው አጓጊ ሆኗል።
የነገውን ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ በመሃል ዳኝነት ሲመራው ሁለቱ ኢንተርናሽናል ረዳቶች ሙስጠፋ መኪና ፋሲካ የኋላሸት በረዳትነት ተመድበዋል። አራተኛ ዳኝነቱን ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ ኮሚሽነርነቱን ተስፋዬ ኦሜጋ መያዛቸውን የደረሰን መረጃ ያስረዳል።
በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ከእርስ በርስ ፍልሚያ በመቀጠል ባሉ በቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መቻል፣ ሃዲያ ሆሳዕናና ፋሲል ከነማን ሲገጥሙ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሀዋሳ ከተማ ፣ሻሸመኔ ከተማና ሀድያ ሆሳዕናን የሚፋለሙ ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለቱ ክለቦች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ 45 ጊዜ እርስበርስ ተፋልመዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 22 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል
ኢትዮጵያ ቡና 8 ጊዜ ሲረታ 15 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።በ45ቱ ጨዋታ 89 ኳሶች ሲቆጠሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ 61 ጎሎችን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 28 ጎሎችን ከመረብ አሳርፈዋል…. ነገ 9 ሰዓት ላይ ለ46ኛ ጊዜ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ሆኗል።