ለአይቮሪ ኮስት 2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ምሽት ላይ የኢትዮጵያ አቻውን የሚገጥመው የጊኒ ዝሆኖች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ካባ ዲያዋራ ዕቅዳቸውን አለመቀየራቸውን እና የምድቡን ሶስተኛና አራተኛ ጨዋታዎች እንደሚያሸንፉ ትናንት ምሽት በሰጡት የቅድመ ጨዋታ መግለጫ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ምንም እንኳን ሁለት ወይም ሶስት ተጫዋቾችን በጉዳት ላያሰልፍ የሚችልበት ዕድል ቢገጥመውም በዕቅዳቸው ላይ እክል እንደሌለው አሰልጣኙ ተናግረዋል።
ሀሙስ ምሽት ለጋዜጠኞች በሰጡት የቅድመ-ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ አሰልጣኝ ካባ፤ ከስብስባቸው መሃል ሴሩ ጊራሲ፣ አንቷን ኮንቴ እና ሞርጋን ጊላቮጊ ላይሰለፉ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል።
«በአጠቃላይ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፤ ምናልባት ኮንቴና ሴሩ አነስተኛ ጉዳት አለባቸው። ሞርጋንም ትናንት ልምምድ ላይ አነስተኛ ጉዳት ገጥሞታል፤ የጉዳቶቻቸውን መጠን ከህክምና ውጤት እናያለን ነገር ግን ከመጫወት የሚከለክላቸው አይመስለኝም፤ ነገር ግን ደግሞ ልጆቹን አደጋ ላይ መጣል አንፈልግም። ብለዋል
- ማሰታውቂያ -
“ወደሞሮኮ የመጣንበት ዓላማ ግልጽ ነው፤ ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ ስድስት ነጥብ መውሰድ፤ ለማለፍ ማድረግ ያለብን ይሄን ብቻ ነው፡፡ ግብ የማግባት ችግራችን ላይ እየሰራን ነው ሁለቱንም ጨዋታዎች ለማሸነፍ እንጫወታለን።” ብለዋል
አሰልጣኙ አክለውም “ቡድናችን ግብ የመፍጠር ችግር እንደሌለብን በተደጋጋሚ አይተናል ነገርግን ዕድሎችን ወደግብ የመቀየር ውጤታማነታችንን ማሻሻል ግን ይጠበቅብናል። ውጤታማነታችንን ማሻሻል ግድ ይለናል በተለይ እንደዚህ ዓይነት ቀለል ያሉ ተጋጣሚዎች ላይ። ልጆቼ በየክለቦቻቸው ግብ የማግባት ችግር የለባቸውም፤ ወደብሔራዊ ቡድን ሲመጡም ያን የማድረግ ግዴታ አለባቸው። በልምምድ ወቅት ብዙ ነገር አይተናል በሜዳ ላይ እንደግመዋለን የሚል እምነት አለኝ።
የሁለቱ ሃገራት የደርሶ መልስ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት ከምሽቱ 5:30 በካዛብላንካ ከተማ በመሃመድ አምስተኛ ስታዲየም ይደረጋል።