የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ነገም 6ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ከነዚህ 6ጨዋታዎች መካከል ደግሞ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
የዘንድሮው አዳማ ከተማ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው እና እንደ ቀድሞ አመታት ለትልልቅ ቡድኖች ፈተና መሆን ከብዶት ይስተዋላል። ከዚህ ባሻገርም እንደ ቀደሙት ጊዜያት ለዋንጫ መፎካከር ከብዶት ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እየዳከረ ይገኛል። የካሳዬ አራጌው ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ሲሆን በተለይ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት እንደሚቸገር ውጤቱ ያሳያል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተለይ ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ከፍተኛ ግብ የማስቆጠር ችግር የሚስተዋልበት ሲሆን ለዚህ ደግሞ የድንቁ አጥቂው አቡበከር ናስር መጎዳት እንደዋነኛ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። የሱን መጎዳት ተከትሎ ወደ ሜዳ እየገቡ የሚገኙት እንዳለ ደባልቄ እና ሀብታሙ ታደሰ ጥሩ ጥምረት ሊፈጥሩ ሲሞክሩ ይታያል ግን ብዙም ፍሬአማ ሊሆን አልቻለም።
- ማሰታውቂያ -
በ11ኛው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን ወደ ባህርዳር የተጓዘው አዳማ ከተማ በባህር ዳር ከነማ የ2-1 ሽንፈት አስተናግዶ ተመልሷል። ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ በሸገር ደርቢ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል። ስለሆነም ሁለቱም ቡድኖች በነገው ጨዋታ ከሽንፈት ለማገገም የሚያደርጉት በመሆኑ በጉጉት ይጠበቃል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ ከተማ በሜዳው ምንም አይነት ሽንፈት አላስተናገደም። ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 6ቱን በሜዳው ያከናወነ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 2ቱን አሸንፎ በ4ቱ ደግሞ አቻ መለያየት ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ደግሞ ከ11 ጨዋታዎች በ2ቱ አሸንፎ በ6ቱ ደግሞ አቻ ተለያይቶ በ3ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፎ 12 ነጥቦችን ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው በ1ግብ ክፍያ ብቻ ከፍ ብሎ 13ኛ ደረጃ ተቀምጧል። ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በሊጉ እስካሁን ከሜዳው ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለ ሲሆን ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 6ጨዋታዎች 3ቱን አቻ ተለያይቶ በ3ቱ ደግሞ ሽንፈት አጋጥሞት ተመልሷል። በአጠቃላይ በሊጉ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 3ቱን ድል አድርጎ 4አቻ ተለያይቶ በ4ቱ ደግሞ ተሸንፎ ከተጋጣሚው አዳማ ከተማ በ1ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ በ13ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ነገ 9:00 ሲል በሚጀምረው እና ፌደራል አርቢቢ ቢኒያም ወ/አገኘው በሚመሩት ጨዋታ በአዳማ ከተማ በኩል ከጉዳት መልስ ልምምድ የጀመሩት ብሩክ ቃልቦሬ እና ሚካኤል ጆርጅ የመግባታቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ከነዓን ማርክነህ የመግባቱ እድል ሰፊ ነው። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከፋሲል ከነማ ጋር ሲጫወቱ የተጎዳው አጥቂው አቡበከር ናስር አሁንም በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ሲሆን አቤል ከበደ ደግሞ ከቅጣት የሚመለስ ተጫዋች ይሆናል።