የፋሲካ /የትንሳኤ/ በዓልን እንዴት እንዳሳለፈ
“የፋሲካ በዓልን ያሳለፍኩት ትናንት ማክሰኞ ናዝሬት ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር የቅድሚያ ጨዋታ ስለነበረን በልምምድ ላይ እና በአመጋገቡም
በኩል ጥንቃቄ በማድረግ እረፍት በማድረግ ነበርና ዓመት በዓሉን ከጓደኞቼ ጋር በመልካም ሁኔታ ላሳልፍ ችያለው”፡፡
የፋሲካ በዓልን በማስመልከት እንኳን አደረሳችሁ ማለት ስለሚፈልጋቸው ሰዎች
- ማሰታውቂያ -
“የፋሲካ በዓልን አስመልክቼ እንኳን አደረሳችሁ የምላቸው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ ለቤተሰቦቼ፣ ለጓደኞቼ፣ ለኢትዮጵያ ቡና
ተጨዋቾች፣ አመራሮች እና አሰልጣኞች እንደዚሁም ደግሞ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር ለሚገኙት ደጋፊዎቻችን መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ
በማለት መልህክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ”፡፡
የባህር ዳር ከተማን በሰፊ ግብ ስለረቱበት ጨዋታ
“የባህር ዳር ከተማ ጋር የነበረን ጨዋታ ተጋጣሚያችን መቐለ 70 እንደርታን አሸንፎ ከመምጣቱ እና ጥሩ ቡድን ከመሆኑም አንፃር እኛ የግድ ወደ
አሸናፊነት ለመምጣት ያደረግነው ስለነበር ከእነሱ በተሻለ መልኩ ተጫውተን የድል ውጤቱን ልናሳካ ችለናል፤ ጨዋታውን በማሸነፋችንም በጣም
ተደስተናል”፡፡
የባህር ዳር ከተማ ላይ ያስቆጠረው ጎል ከረጅም ጊዜ በኋላ ስለመሆኑ እና በጎሏ ስለተሰማው ስሜት
“የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች ሆኜ የመጨረሻ ግቤን ያስቆጠርኩት ዓምና መቐለ 70 እንደርታን በተፋለምንበት እና ድል ባደረግንበት ግጥሚያ ስለ ነበር ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ባህር ዳር ላይ አቡበከር በጥሩ ሁኔታ ያቀበለኝን ግብ ሳገባ የተሰማኝ የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነበር፤ በእዚሁ አጋጣሚ ኳሷን ያቀበለኝን አቡበከርን ለማመስገን እፈልጋለው”፡፡
ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ስላላቸው የሸገር ደርቢ ጨዋታ እና ማን የግጥሚያው አሸናፊ እንደሚሆን
“የቅ/ጊዮርጊስ ክለብን የምንፋለምበት የእሁዱ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ለሁለታችንም ጠንካራና ከበድ የሚልብን ቢሆንም በእኛ በኩል
ለግጥሚያው ለሌሎች ቡድኖች እንደምንዘጋጀው ሁሉ በሚገባ ተዘጋጅተንበታል፤ በሸገር ደርቢው ጨዋታም አሸናፊ የምንሆነው እኛ ኢትዮጵያ ቡናዎች
ነን”፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ስለማንሳት እድላቸው
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን የማንሳት እድላችን አሁን ላይ ውድድሮቹ ወደ መጠናቀቁ ደረጃ ከማምራታቸው እና ከመሪው ክለብ ጋር
ያለንም የነጥብ ልዩነት ራቅ ያለ ከመሆኑ አንፃር በጣም ጠባብ ነው፤ ስለዚህም ከእዚህ በኋላ የሚኖሩንን ግጥሚያዎች እያሸነፍን በመጓዝ
የሚመጣውን ማናቸውንም ውጤት እንቀበላለን፤ ከእዛ ውጪም ለጥሎ ማለፉ ዋንጫ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እና ውጤታማም ሆነን ደጋፊዎቻችንን
በእዚሁ ለመካስ ጥረቶችን እናደርጋለን”፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ አቋም እና ስለ ቡድኑ መንፈስ
“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ በአሁን ሰዓት ክለባችን ያለው ወቅታዊ አቋም ጥሩ ነው፤ ጥሩ መነቃቃት እና
ጨዋታዎችን የማሸነፍ ከፍተኛ ፍላጎትም በቡድኑ ውስጥ ይታያል፤ እኛ ጋር ስላለው የቡድን መንፈስም ማለት የምፈልገው እያንዳንዳችን ጥሩ ግንኙነት
ነው ያለን፤ ለእዚህ ደጋፊም አንድ ነገርን ሰርተን ማለፍ እንዳለብን እያሰብንም ነው”፡፡
ከቅ/ጊዮርጊስ በሚኖራችሁ የሸገር ደርቢ ጨዋታ አቡበከር ናስርን በቅጣት የምታጡ ከሆነ ትጎዳላችሁ? ስለ አቡበከር ብቃትስ ምን ትላለህ?
“የኢትዮጵያ ቡና እያደረጋቸው ባሉት የሊጉ ጨዋታዎች በምርጥ አቋሙ እና ብቃቱ ላይ በመገኘት የአሁን ሰዓት ላይ ለክለቡ ጥሩ እየተጫወተ
ስለሚገኘው አቡበከር ናስር ቅጣት እስካሁን የተወሰነ ነገር ባይኖርም የእሁዱ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ የእሱ መኖር እንደ ቡድን ተጨማሪ ነገር
የሚፈጥርልን ስለሆነ በጣም ያስፈልገናል፤ አቡኪን የምናጣ ከሆነ አጥቂው ክፍል ላይ መሳሳት ይፈጠራልና አሁን ላይ ውሳኔውን በመጠባበቅ ላይ ነው
የምንገኘው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር ችሎታ እና ወቅታዊ ብቃትም ከወዲሁ ማለት የምፈልገው አቡኪ ሁሌም ራሱን ለመለወጥ
ዝግጁ የሆነና ጥሩም የኳስ ችሎታ ያለው እና ጎል በማስቆጠር ብቃቱም የሚደነቅ ተጨዋች ነው፤ ገና ከወጣትነት እድሜው አኳያም በጎል አዳኝነቱ
ጨራሽ እና ሁነኛም አጥቂ ስለሆነ ሊበረታታ የሚገባው ተጨዋች ነው”፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ የነበረውን አቋም እየመለሰ ስለመምጣቱ እና ከጨዋታ ወደ ጨዋታም መሻሻልን ስለማሳየቱ
“የኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ቆይታዬ ላይ ከእዚህ በፊት ወደነበርኩበት እና ጥሩም ወደሆንኩበት የቀድሞ አቋሜ እና ብቃቴ የአሁን ሰዓት ላይ
በመመለስ ላይ የምገኘው ባለፈው ክረምት አጋጥሞኝ እና ወደ ሜዳም በፍጥነት ለመመለስ አስቸግሮኝ ከነበረው ከፍተኛ ጉዳቴ በክለባችን
ፊዚዬቴራፒስት ይስሃቅ ሽፈራው ባደረገልኝ ጥሩ የሆነና ተከታታይ ህክምና ልድን በመቻሌ ነው፤ ፈጣሪ ይመስገን አሁን በጥሩ ጤንነት እና በጥሩ አቋም
ላይም ስላለው ክለቤን ከእዚህ በተሻለም ለማገልገል ራሴን የበለጠ አዘጋጃለው”፡፡