የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት የመጨረሻ አንድ ጨዋታ ነገ ይደረጋል።
የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት 7ጨዋታዎች ዛሬ (ቅዳሜ) የተደረጉ ሲሆን የመጨረሻ አንድ ጨዋታ ደግሞ ነገ (እሁድ) የሚደረግ ይሆናል።
ሁለት በተለያየ አቋም ላይ በሚገኙት ቡድኖች መካከል የሚደረገው ይህ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናን እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊጉ ጥሩ ግስጋሴ ማድረግ ያልቻለው እና እስካሁን በሊጉ ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና በኢ/ር ካሳዬ አራጌ እየተመራ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማስመዝገብ እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እንዲሁም በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ያለመሸነፍ ሪከርዱን ለማስጠበቅ እና ከመሪዎቹ ተርታ ላለመራቅ የሚያደርጉት ጨዋታ ስለሆነ ከባድ ፉክክር ይስተዋልበታል ተብሎ ይጠበቃል።
- ማሰታውቂያ -
በ3ኛው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ወደ መቐለ ተጉዞ ከመቐለ ከተማ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መመለስ ሲችል ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በብሩክ በየነ ብቸኛ ግብ ባህርዳር ከተማን በማሸነፍ የሊጉን መሪ ወልዋሎን በቅርብ ርቀት መከተል ጀምሯል። ውጤቶቹም ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ2ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በ7 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። የነገውን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ኃ/ስላሴ የሚመሩት ይሆናል።