የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት የዕለተ ቅዳሜ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ(ቅዳሜ) አንስቶ እስከ ሰኞ ድረስ በሚደረጉ 6 ጨዋታዎች የሚቀጥሉ ይሆናል። በብቸኛ የቅዳሜ ጨዋታ ዛሬ መቐለ ላይ መቐለ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን በግዙፉ መቐለ ስታድየም የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች ከተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ በመጣል ከነበሩበት የውጤት ቀውስ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰው የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በመላው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ እንዲጠበቅ አድርጎታል። በሌላ በኩል ሁለቱም ቡድኖች ወደ 8 ከሚጠጉ ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ሊለያዩ ችለዋል። በመቐለ ከተማ በኩል 5ተጫዋቾች (ዱላ ሙላቱ(ከሀዲያ ሆሳዕና የፈረመ)፣ ዮሱፍ ደንገቶ (ከወላይታ ድቻ የፈረመ)፣ ሙሉጌታ ረጋሳ (ከወልዲያ የፈረመ)፣ ዮሴፍ ሀይሉ (ነባር )፣ ተመስገን አዳሙ (ነባር)) እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ 3ተጫዋቾች(ማናዬ ፋንቱ፣ አብዱሰላም እና በረከት ይስሀቅ) የተለያዩ መሆኑ ዛሬ ተሰምቷል።
በመቐለ ከተማ በኩል ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ጋይስ አፖንግ ላይ ጥገኛ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ሁለቱ ተጫዋቾች በጨዋታ ላይ ግብ የማያስቆጥሩ ከሆነ ቡድኑ ከሌላ ተጫዋቾች የግብ እድል መፍጠር ሲሳነው ተስተውሏል። ከ12 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ(በደደቢት) የተሸነፈው መቐለ ከተማ 5ግቦች ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ እጅግ በጣም የሚወደስ ነው። በተለይ በአርባምንጭ ከተማ በአጥቂነት የምናውቀው ዓመለ ሚልክያስ እጅግ በተለየ ሚና በተከላካይ አማካኝነት በየጨዋታው የመቐለ ከተማ ተከላካዮችን ሽፋን በመስጠት እና በማገዝ ድንቅ ብቃቱን ማስመስከር ችሏል። ለረጅም ጊዜ ከግብ ማግባት ርቆ የነበረው የመቐለ ከተማ አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ14ኛው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የራስ መተማመኑን መመለስ የሚችልበት አጋጣሚ የፈጠረ ሲሆን ይህም ጥቃቅን ስህተት ለሚሰራው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር እንደስጋት የሚታይ ነው። በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡና በኩልም የክሪዝስቶም ንታምቢ ወደ ቡድኑ መመለስ በመሀል ሜዳው ክፍል ላይ ኢትዮጵያ ቡና በተጋጣሚዎቹ ላይ ብልጫ እንዲወስድ እና ለቡድን አጋሮቹ በተለይም ለሳምሶን ጥላሁን እና ለኤልያስ ማሞ የሜዳ ላይ ነፃነት እንዲያገኙ አስችሏል። ይህ ደግሞ አጥቂው ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ ግብ ማግባቱ እንዲመለስ አስችሎታል። ከነዚህ ሁሉ ተጫዋቾች በተጨማሪ ለሰሞኑ የኢትዮጵያ ቡና መነቃቃት እና ውጤት መስመር ስሙ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ተጫዋች ቢኖር እሱም አማኑኤል ዮሀንስ ነው።
በ14ኛው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታቸውን ያከናወኑት አ/አ ስታዲየም ላይ ሲሆን መቐለ ከተማ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሁለት ግቦች ታግዞ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን 2-1 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በሳሙኤል ሳኑሚ፣ ኤልያስ ማሞ እና አቡበከር ነስሩ 3ግቦች ታግዞ ፋሲል ከተማን ማሸነፍ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማድረግ ከነበረበት 13ጨዋታዎች 12ቱን ያደረገው መቐለ ከተማ በ6ቱ አሸንፎ በተመሳሳይ በ6ቱ ጨዋታዎች አቻ ወጥቶ በ1ጨዋታብቻ ተሸንፎ ከመሪው ደደቢት በ1 ነጥብ ርቆ በ24 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ካደረጋቸው 13ጨዋታዎች 5ቱንአሸንፎ 3ቱን አቻ ወጥቶ እንዲሁም በ5 ጨዋታዎች ተሸንፎ በ18ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ (ቅዳሜ) የካቲት 03/2010 9:00 ሲል በግዙፉ መቐለ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።