አሰልጣኛቸውን ከህመም መልስ ያገኙት ወልቂጤዎች ከመመራት ተነስተው ጣፋጭ ሥስት ነጥቦችን አሳክተዋል።
የለገጣፎ ለገዳዲዎች መልሶ ማጥቃት ፣ የወልቂጤዎች በሙከራ ያልታጀቡ ቅብብሎች በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ሁለት ግቦች ተቆጥረውበታል።
በኢብሳ ፍቃዱ እና በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ሙከራዎችን በማድረግ የወልቂጤን ግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩት በዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመሩት ለገዳዲዎች ጨዋታው ላይ መሪ ያደረጋቸውን ግብ ጀማል ጣሰው በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል።ኢብሳ በፍቃዱ ከቀኝ መስመር ሱራፋኤል አወል ያሻማለትን ኳስ በመቀስ ምት መትቶት የግቡ ቀዋሚ ገጭቶ ሲመለስ ጀማል ጣሰው በራሱ ግብ ላይ ሊያስቆጥረው ችሏል።የወልቂጤ የመሀል ክፍል ላይ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ከመጀመርያው ግብ መቆጠር 8 ደቂቃዎች በኃላ አስራት መገርሳ መቆጣጠር ያልቻለውን ኳስ አማኑኤል አርቦ ከኢብሳ በፍቃዱ ተቀብሎ በጥሩ አጨራረስ የለገጣፎ ለገዳዲን መሪነት ወደ ሁለት ግብ ከፍ አድርጎታል።
በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ለገዳዲዎች የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ የታዩት የገብረክርስቶስ ቢራራ ልጆች በአቤል ነጋሽ ፣ በብዙአየሁ ሰይፋ አማክኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።በተለይ በጨዋታው 30ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ ከተመስገን በጅሮንድ የተቀበለውን ቆንጆ ኳስ ከበረኛው አናት ለማሳለፍ ቢሞክርም ከግቡ አናት ለትንሽ ወጥቶበታል።
- ማሰታውቂያ -
ሁለተኛው አጋማሽ አንደተጀመረ ወልቂጤዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።የዚህም ከርቀት ተመትቶ በሽር ደሊል የተፋው ኳስ በፍፁም ቅጣት ሳጥን በግራ በኩል የነበረው ጌታነህ ከበደ ወደ ውስጥ አሻምቶት አስራት መገርሳ በቀላሉ አስቆጥሮታል።
ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ወልቂጤዎች በጌታነህ ከበደ እና በአቤል ነጋሽ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በበሽር ደሊል አማካኝነት መከራቸው ሳይሳኩ ቀርተዋል ።
ሆኖም የበሽር ደሊል ጥረቶች ከንቱ ያስቀረ ግብ በ72 ኛው ደቂቃ በኃላሸት ሰለሞን አማካኝነት ሊቆጠር ችሏል። ጌታነህ ከበደ ያሻማውን የማእዘን ምት የኃላሸት ሰለሞን በግምባሩ በመግጨት ወልቂጤዎቹን አቻ አድርጓል።
የሁለት ግብ ልዩነት መሪነታቸውን ያጡት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በ78ኛው ደቂቃ ላይ በኢብሳ በፍቃዱና በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ወደ መሪነት ሚመልሳቸው ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
የዕለቱ ዳኛ በሰጡት 3 የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ሰራተኞቹ ወልቂጤ ከተማዎች ከማእዘን ምት ጌታነህ ከበደ አሻምቶት ተጨርፎ የወጣውን ኳስ አዲስአለም ተስፋዬ በቀላሉ አስቆጥሮ ወልቂጤዎችን ከሁለት ግብ ልዩነት መመራት ወደ አሸናፊነት መልሷቸዋል ።
በድራማዊ ክስተቶች የታጀበው ጨዋታም በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።