ዋሊያዎቹ ነገ ወደ ሞሮኮ ያቀናሉ
የዋሊያዎቹ የግብ አዳኝ ጌታነህ ከበደ በቃኝ በማለቱ አቡበከር ናስርና ሽመልስ በቀለ በጉዳት ከዋሊያዎቹ ስብስብ ውጪ መሆናቸውን አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ተናገሩ።
አሰልጣኙ ዛሬ ከቀትር በኋላ በሰጡት መግለጫ ውጫዊና ቴክኒካዊ ዲሲፕሊን ዙሪያ ከቡድኑ አባላት መነጋገራቸውን ገልጸዋል። አሰልጣኙ ሰባት ጊዜ ልምምድ እንደሰሩና በይበልጥ በአጨወወት ስታይልና ቴክኒካዊ ሂደት ላይ አተኩረው እንደሰሩ አስረድተዋል። ከሱዳኑ አልሂላል ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ከሞላ ጎደል ጥሩ እንደነበሩና የጎደሉ ጉዳዮች ላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስረድተዋል። ከሶስቱ ተጨዋቾች ውጪ ይዘው ከነበሩት 27 ተጨዋቾች አራቱን ቀንሰው 23 ተጨዋቾችን መያዛቸውን ገልጸዋል።
ስለተቀነሱት ተጨዋቾች ዙሪያ የተጠየቁት አሰልጣኙ አለልኝ አዘነ የሚወዳደረው በቦታው ሲሆን በዚህም ከጋቶችና ናትናኤል ጋር ተፎካክሮ ሁለቱን የተሻለ ሆነው እንዳገኟቸው አስረድተዋል። አሰልጣኙ ከአለልኝ አዘነ ውጪ ብርሃኑ በቀለ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱና ተገኑ ተሾመን መቀነሳቸው ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
“ተጨዋቾቼ የምፈልገውን ለማድረግ ይጥራሉ ይሄ በጣም አስደስቶኛል ወደምፈልገው እንዲመጡ የተሻለ ሰርተን የምንፈልገው ደረጃ እንደርሳለን ለዚህ ልምምዳችንን አጠናክረን እንገፋበታለን ከአጨዋወት አንጻር በጥሩ ሁኔታ ተቀብለው እየሰሩ መሆኑና የሁልጊዜ አጨዋወት ለማድረግ ግን ተደጋጋሚ ስራ ይጠይቃል ” ያሉት
አሰልጣኙ 30 ተጨዋቾችን መርጠው እንደነበርና ጌታነህ ከበደ ይብቃኝ በማለቱ አቡበከር ናስርና ሽመልስ በቀለ በጉዳት ከዋሊያዎቹ ስብስብ ውጪ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሀገር ጥሪ ደርሷቸው ቡድኑን መቀላቀል ስላልቻሉት ሶስቱ ተጨዋቾች ሲያስረዱ “ጌታነህ ናዝሬት ድረስ መጥቶ አናግሮኝ ሃሳቡን አለመቀየሩን ገልጾልኝ መተማመን ላይ በመድረሳችን ቡድኔን አልተቀላቀለም
አስቀድሞም በመወሰኑ አቋሙን መቀየር እንደሚከብደው በመግለጹ ውሳኔውን አክብሬ ተለያይተናል ሽመልስም በጉዳት መሆኑን አስረድቶኝ ተግባብተናል የአቡበከር ግን በኢሜይል ተጠይቆ በኢሜይል የመለሰው ነው ሶስቱም ላለመቀላቀላቸው በሚገባ ተከባብረን የተስማማነው ነው” በማለት መልሰዋል።
የአሰልጣኝ ገ/መድህን ሃይሌው ስብስብ ከሴራሊዮንና ቡርኪናፋሶ ጋር ላለባቸው የዓለም አለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ነገ ከቀትር በኋላ ወደ ሞሮኮ ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።