የቀድሞው የፋሲል ከነማ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው በይፋ የአሜሪካው ክለብ ሎደን ዩናይትድ ተጫዋች በመሆን ፊርማውን ማኖሩን ክለቡ ይፋ አድርጓል። ክለቡ ይፋ እንዳደረገው መረጃ ከሆነም ሱራፌል የሁለት አመት እንዲሁም እንደ የሚያሳያው ብቃት ለተጨማሪ አንድ አመት የሚራዘም ውል ላይ ፊርማውን አኑሯል። የተጫዋቹን ፊርማ የሊጉ አስተዳደር እንዳፀደቀውም በክለቡ ጨዋታዎችን ማድረግ ይጀምራል። የቡድኑ አሰልጣኝ ርያን ማርቲን ሱራፌልን በጣም ጥሩ የአጥቂ አማካይ ነው ያሉ ሲሆን ተጫዋቹ ቡድናቸውን በመቀላቀሉ መደሰታቸውን ገልፀዋል። ሎደን ዩናይትድ በአሜሪካ የሊግ እርከን በሁለተኛው ሊግ ላይ በምስራቅ ኮንፈረንስ የሚጫወት ሲሆን በ13 ጨዋታዎች 17 ነጥቦች በመሰብሰብ ከ12 ክለቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።