”ሲዳማ ቡናን ከመዉረድ ስጋት እንዲላቀቅ ማድረጌ እጅግ በጣም ደስታን ፈጥሮልኛል”
”የተስፋዉ u20 ቡድናችን መጠናከር ይገባዋል”
”ከክለቡ ጋር አብሬ እቀጥላለሁ”
ስዩም ከበደ /የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ/
- ማሰታውቂያ -
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ባደረገዉ ስብሰባ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከክለቡ ጋር እንዲቀጥል ወስኗል።
አሰልጣኙም ከክለቡ ጋር እስከ 2016 ዓ.ም የውድድር ዘመን መጨረሻ ድረስ የሚያቆይ ኮንትራት እንዳለዉ ገልፆልናል።
እኛም ከሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጋር ስለ ክለቡ ቆይታ እና ቀጣይ ጉዞዉ አጭር ቆይታ አድርገናል።
ሀትሪክ :- ሲዳማ ቡናን ከያዝክ በኋላ የ2015 ቆይታህ ምን ይመስል ነበር ?
ስዩም :- ያዉ እንደሚታወቀዉ ወደ ቡድኑ የተቀላቀልኩት ዉድድሩ ተጀምሮ አራት ጨዋታዎች ተደርገዉ ቡድኑ 1 ነጥብ ብቻ ይዞ እያለ ነበር። ይህ ደግሞ ስራዬን ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎታል ምክንያቱም በቅድመ ዝግጅትና በተጫዋቾች ምልመላ ወቅት ከክለቡ ጋር አብሮ አለመሆኔ ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎት በብዙ ዉጣ ዉረዶችና ፈተናዎች የዉድድር ዘመኑን እንዳጠናቅቅ አስገድዶኛል።
ነገር ግን የ2015 ዓ/ም የዉድድር ዘመኑን ሳጠናቅቅ ክለቡን ከመዉረድ ስጋት እንዲላቀቅ ማድረጌ ግን እጅግ በጣም ደስታን ፈጥሮልኛል።
ሀትሪክ :- በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ዉጤት ስለማጣታችሁ ምን ትለናለህ ?
ስዩም :- በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ዉጤት አለማግኘታችን 4ኛ ሆነን የማጠናቀቅ ዕድላችን አበላሽቶብናል። ነገር ግን እንደ አሰልጣኝ ለወጣቶቻችን እና ላልተጫወቱት ዕድል መስጠት ስለነበረብኝ በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ አዳዲስ ልጆችን ወደ ሜዳ አስገብቼ ያየሁበት ነበር ያ ደግሞ የራሱ ጠቀሜታ አለዉ።
በጥቅሉ ጠንካራዉ ክለባችን ከዘመኑ ዉድድር ብዙ የተማረባቸዉ ነገሮች ስለሚበዙ ለቀጣዩ በተሻለ ቁመና እንደምንቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ።
ሀትሪክ :- ከእላይ እንደገለፅክልን በተጠናቀቀዉ የዉድድር አመት ከታች ላደጉ ልጆች እድል እንደተሰጠ እና ይሄም ጠቀሜታ እንዳለዉ ገልፀህልናልና በቀጣይ ለታዳጊ ልጆች እድል በመስጠቱ ላይ ከተስፋዉ ቡድን ጋር ተቀራርቦ በመስራቱ ላይ እና ከአሰልጣኞቹ ጋር ተጣምሮ በመስራቱ ላይ ምን ታስባለህ ?
ስዩም :- በሚኖረን pre-season preparation ከተስፋ ቡድን አሰልጣኞች ጋር በመነጋገርና በመመካከር እጅግ ተስፋ ላላቸዉ ታዳጊዎች በዝግጅት ፕሮግራማችን እንዲካፈሉ ዕድል እንሰጣለን። አሁን ካሉን ጋር አወዳድረን የተሻሉትን ለማሳደግ ጥረት እናደርጋለን።
ለወደፊት ይበልጥ ለታዳጊዎቹ የተስፋ ዕድሉን ለመስጠት መጀመሪያ የወጣቶች ምልመላ ላይ በእጅጉ ትኩረት ተደርጎበት ሊሰራ ይገባል። ዋናዉ ቡድን ላይ ጠንካራ ታዳጊ ልጆች እንዲኖሩን የተስፋ u20 ቡድናችን መጠናከር ይገባዋል ለዚህም ከአሰልጣኞቹ ጋር በቅርበት በመነጋገር እንሰራለን።
ሀትሪክ :- በቀጣይ በሲዳማ ቡና ቤት በሚኖርህ ቆይታ ምን እንጠብቅ ?
ስዩም :- ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ዘንድሮም 4ኛ ሆነን ለመጨረስ ዕድሉ ነበረን። በቀጣይ ለሻምፒዮን ፍልሚያዉ በሚያስችል ቁመና ለመገኘት ከወዲሁ ቅድመ ሥራዎች ተጀምረዉ በመስራት ላይ እንገኛለንና ጠንካራዉን ሲዳማ ቡናን በመስራት ጥሩ የዉድድር ዓመት እናሳልፋለን ብዬ አስባለሁ።
ሀትሪክ :- በመጨረሻም ማመስገን የምትፈልጋቸዉ አካላት ካሉ እድሉን እንስጥህ።
ስዩም :- ከሁሉ አስቀድሜ ፈጣሪን ማመስገን የምፈልግ ሲሆን ከእሱ በመቀጠል ወደ ክለቡ አንድ ብዬ በመጣሁበት ወቅት ለሲዳማ ቡና ይመጥናል ብለዉ አምነዉኝ ወደ ክለቡ እንድመጣ ላደረጉኝ ለክለቡ ለቦርድ አመራሮች ምስጋናዬን ማስተላለፍ የምፈልግ ሲሆን እንዲሁም ክለቡ ባሳለፋቸዉ አስቸጋሪ መንገዶች ሁሉ አብረዉን ለነበሩ ለክለቡ ለቦርድ አመራሮች ፣ ለስራ አስኪያጁ ፣ ለደጋፊ ማህበሩ እና ለክለባችን የጀርባ አጥንት ለሆኑት ለደጋፊዎቻችን በሙሉ በእኔ በኮቺንግ ስታፌ እና በተጫዋቾቼ ስም ምስጋናዬ ይድረሳቸዉ።
ሀትሪክ :- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
ስዩም :- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ አመሰግናለሁ።