የትግራይ ክልል ስፖርትን ለማነቃቃት እና ህዝቡ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት የስነልቦና ቀዉስ በቶሎ ማገገም እንዲችል እና በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለፕሪሚየር ሊጉ ድሞቀት እና መነቃቃት ፈጥረዉ የነበሩት ሶስቱ ክለቦች ፈርሰዉ እንዳይበተኑ ለማድረግ የታለመዉን አለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በተመለከተ ዛሬ ረፋድ መግለጫ ተሰጥቷል።
ለትግራይ ክልል ክለቦች ለመቀሌ 70 እንደርታ ፤ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ስሁል ሽረ እግር ኳስ ክለቦች በሁለት ወር ውስጥ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰበሰብ መታሰቡን በዛሬዉ ዕለት ረፋድ ላይ በሸራተን አዲስ በተሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል።
የገቢ አሰባሳቢዉ EY ፕሮዳክሽን እና የሦስቱ ክለብ ዋና ተወካዮች በጋራ በሰጡት መግለጫም ከጦርነት ማግስት ያለውን ማኅበራዊ ትስስር እና ግኑኝነት ወደ በጎ ለመቀየር በዘርፉ ላይ ስፖርት ከፍ ያለ ሚና እንዳለዉ ሲገለፅ ፤ የትግራይ ክልልን ስፖርት ለማነቃቃትም ” ክለቦቻችን እንታደግ ” በሚል መሪ ቃል በሀገር ቤትና በውጪ ሀገር በስፖርታዊ መሰረታዊ ሕጎች በመመራት ዘመቻው አዲስ አበባ ተጀምሮ መቀሌ እንደሚጠናቀቅም ተነግሯል።
- ማሰታውቂያ -
የመክፈቻ ስነ ስርአቱ በወዳጅነት አደባባይ የለገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተጀምሮ በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ ከተማ የማጠቃለያ ፕሮግራም በ60ኛው ቀን ላይ እንደሚደረግም በመግለጫዉ ላይ ተነግሯል።
ገቢ ማሰባሰቢያው ቃል ከሚገቡ ግለሰቦች ድርጅቶች ፤ ባጭር የጽሑፍ መልክት ፤ የዲያስፖራ ጎፈንድሚ አካውንት ተከፍቶ ዘመቻው እንደሚጀምር እና የትግራይ ክልል ባለሀብቶችን ጨምሮ ደጋፊ አካላት የሚካተቱበት ዘመቻ መሆኑን ሲገለፅ ፤ የ2011 አመተ ምህረት የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ መቀሌ 70 እንደርታ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ይርጋ ገ/እግዚያብሔር ጦርነቱ የፈጠረባቸውን ውድመትም በዝርዝር በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ስሁል ሽሬ እግርኳስ ክለብ ፕሬዝዳንቶችም ክለቦቻቸዉን መልሶ ለማቋቋም ከኢዋይ ጋር የተደረገው ስምምነት ቁልፍ መሆኑን ሲናገሩ ፤ ከክለባቸዉ ፈቃድ ውጪ ግን የሚደረግ ሌላ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሕጋዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል።