በስምንት ምድብ ተከፍሎ በሰላሳ አንድ ክለቦች መሀከል ሲደረግ የቆየዉ የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በጎንደር አራዳ አሸናፊነት በዛሬዉ እለት ተጠናቋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከሰኔ 15 ጀምሮ በ8 ምድቦች ተከፍሎ በ31 ክለቦች መካከል ሲደረግ የቆየዉ የ2015 አ/ም የወንዶች የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው እለት በተደረጉ ሁለት መርሀ ግብሮች ፍፃሜዉን አግኝቷል።
በማስቀደም 7:00 ሰአት ሲል ለደረጃ ጨዋታ የሲዳማ ክልሉ መታፈሪያ ክፍሌ እና የኦሮሚያ ክልሉ ሱሉልታ ቢ ተገናኝተዉ መደበኛዉ የጨዋታ ክፍለ ግዜ 0-0 በሆነ ዉጤት ተጠናቆ በተሰጠዉ የመለያ ምት ሱሉልታ ቢ 4-2 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ዉድድሩን በሶስተኝነት በማጠናቀቅ የነሀስ ሜዳልያ ተሸላሚ መሆኑን አረጋግጧል።
- ማሰታውቂያ -
በማስከተል 9:00 ሰአት ጀምሮ በፍፃሜዉ የዋንጫ ጨዋታ በሁለቱም በአማራ ክልል ተወካዮች በጎንደር አራዳ እና በደምበጫ ከተማ መሀከል የተደረገ ሲሆን ጨዋታዉን ጎንደር አራዳ 2-1 በሆነ ዉጤት አሸንፎ ሻምፒዮን መሆን ችሏል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳኛቸው ንግሩ ፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸረፋ ደሌቾ እንዲሁም የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በክብር እንግድነት በመገኘት ለአሸናፊዎች የሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት እንዲሁም ለተለያዩ አካላት የምስጋና የምስክር ሰርተፊኬት አበርክተዉላቸዋል።
ዉድድሩን ለመሩ ዳኞች እና ኮሚሺነሮችም ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በዚህም መሰረት ኮሚሽነር ጌቱ ተጫነ ፣ ዋና ፌ/ዳኛ ወንድማገኝ መለሰ ፣ 1ኛ ረዳት ፌ/ዳኛ ዘሪሁን ጊደታ ፣ 2ኛ ረዳት ፌ/ዳኛ ሰለሞን አጥናፉ እና 4ኛ ዳኛ ፌ/ዳኛ ሙሉነህ ጥላሁን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።
ይሄ ዉድድር ላይ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም የምስጋና ሰርተፊኬት እና የዋንጫ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ዉድድሩን በሶስተኝነት ያጠናቀቀዉ ሱሉልታ ቢ የነሀስ ሜዳልያ ሲሸለም ዉድድሩን በሁለተኛነት ያጠናቀቀዉ ደምበጫ ከተማ የብር ሜዳልያ ሲሸለም አሸናፊዉ ጎንደር አራዳ ደግሞ የወርቅ ሜዳልያ ተሸልሟል።
የዉድድሩ አዘጋጅ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዋንጫ ተሸላሚ የሆነ ሲሆን የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ል ፕሬዝዳንት አቶ ማርቆስ ኤልያስ የተዘጋጀዉን ዋንጫ ተቀብለዋል።
በስተመጨረሻም የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ በመሆን ጎንደር አራዳ የተዘጋጀዉን ዋንጫ ተቀብሏል።
በዘንድሮው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በወንዶች ጎንደር አራዳ ፣ ደንበጫ ከተማ ፣ መታፈርያ ክፍሌ እና ሱሉልታ ከተማ ቢ ወደ አንደኛ ሊግ ያደጉ ክለቦች ሲሆኑ በሴቶች አምቦ ጎል ፕሮጀክት እና ደብረማርቆስ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ያደጉ ክለቦች ሆነዋል።