በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ ወላይታ ዲቻን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል ።
ተመጣጣኝ የሚባል የሚባል የጨዋታ ፉክክር ባስመለከተዉ እና በተቃራኒው በሙከራ ረገድ ግን ደካማ በነበረዉ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ባህርዳር ከተማዎች በይበልጥ በኳስ ቁጥጥር ተሽለዉ በመቅረብ አልፎ አልፎ የሚያገኟቸዉን ዕድሎች ወደ ግብነት ለመቀየር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ በተቃራኒው ወላይታ ዲቻዎች ከኋላ መስመር የሚነሱ ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል የጨዋታዉን የበላይነት ለመያዝ የሞከሩ ቢሆንም ነገር ግን ያን ያህል ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ላይ እምብዛም ሆነዉ ተስተዉሏል ፤ በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ዲቻዎች አብነት ደምሴ ባቀበለዉ ኳስ ቢኒያም ፍቅሬ ድንቅ ሙከራ አድርጎ ኳሷ ለጥቂት ወጥታለች።
በጨዋታዉ ረገድ የተሻሉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በ31ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከማዕዘን ምት የተሻገረዉን ኳስ የፊት መስመር ተጫዋቹ ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዕረፍት መልስ ወላይታ ዲቻዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለዉ በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመጠጋት ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ፤ በተቃራኒው ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ ያስቆጠሩትን ግብ አስጠብቀዉ ለመዉጣት ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርባቸዉ 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ መቻል ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል ።
በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክር መከናወን በጀመረዉ የሁለት ክለቦች የአመሻሽ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ጨዋታ ገና በመባቻዉ ግብ ተስተናግዶበታል ። በዚህም በ14ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ያሻገረዉን ኳስ የሻሸመኔ ከተማ ተከላካዮች ሲመልሱት በቅርብ ርቀት ላይ የነበረዉ ከንዓን ማርክነህ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል ።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች ዳግም ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ግብ አስቆጥረዉ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጭ ተብሎ ተሽሮባቸዋል። አሁንም በተደጋጋሚ ማጥቃታቸዉን የቀጠሉት መቻሎች ዳግም በ35ተኛዉ ደቂቃ ላይ በቺጂኦኬ አማካኝነት ድንቅ የግብ ሙከራ አድርገዉ የነበረ ቢሆንም የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል ።
በተቃራኒው ያን ያህል የግብ ሙከራ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ሻሸመኔ ከተማዎች በአንፃሩ በሂደት ወደ ጨዋታዉ መግባት ቢችሉም ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ። ከዕረፍት መልስ አንደ መጀመሪያዉ አጋማሽ ሁሉ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ግብ ጠባቂዉን አልፎ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ተከላካዩ የአብስራ አውጥቶበታል።
የጨዋታዉ ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ይበልጥኑ እንቅስቃሴዉን እየተቆጣጠሩ የሄዱት መቻሎች በ69ነኛዉ ደቂቃ ላይ በግቡ ባለቤት ከንዓን ማርክነህ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ኳሷ ለጥቂት ወጥታባቸዋለች። ያን ያህል በሙከራዉ ረገድ ደካማ የነበሩት ሻሸመኔዎችም ተጨማሪ አደጋዎችን መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታዉ በመቻል 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።