በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሀያ ስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ዕለት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሀምበሪቾ ዱራሜን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል።
ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ መሪነት በጀመረዉ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ይዘዉት የመጡትን የጨዋታ መንገድ ለመተግበር እና እንቅስቃሴያቸውን ለማስቀጠል ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን በእንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ በጀመረዉ ጨዋታም ኳስ ተቆጣጥረዉ ለመጫወት ይሞክሩ የነበሩት ቡናማዎቹ በ16ተኛዉ ደቂቃ ላይ ጨዋታዉን መምራት ጀምረዋል። በዚህም የሀምበሪቾዉ ተከላካይ ሙና በቀለ ኳስ በዕጅ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ቅጣት ምት አማኑኤል ዮሐንስ ወደ ግብነት መቀየር ሲችል ፤ ተጫዋቹም በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
ተጫዋች ገና በጊዜ በቀይ ካርድ ከወጣባቸዉ በኋላ በጎዶሎ ለመቀጠል የተገደዱት ሀምበሪቾዎች በአብዝሀኛዉ የመጀመሪያው አጋማሽ ያን ያህል ጫና ፈጥረዉ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ በተቃራኒው በ32ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም አማኑኤል አድማሱ ከመሐመድ ኑር ናስር የተሻገረለትን ኳስ በተከላካዮች አለመግባባት አግኝቷት ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በሁለተኛዉ አጋማሽም ቡናማዎቹ ይበልጥኑ ጫና ፈጥረዉ ሲጫወቱ በ52ተኛዉ ደቂቃ ላይም መሪነታቸዉን ወደ ሶስት ከፍ አድርገዋል። በዚህም ከመሐመድ ኑር ናስር የተቀበለዉን ኳስ አንተነህ ተፈራ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከዚች ግብ መቆጠር ከሀያ ደቂቃዎች በኋላም ቡናማዎቹ አራተኛ ግብ አግኝተዋል። በዚህም ሳጥን ዉስጥ አማኑኤል የመታትን ኳስ የግብ ዘቡ ሲመልሳት በቅርብ ርቀት ያገኛት መሐመድ ኑር ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
ቡናማዎቹ አራተኛ ግብ ካስቆጠሩ ከሁለት ደቂቃዎች በኀሏ ደግሞ በአጠቃላይ በሙሉ ደቂቃዉ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ሀምበሪቾዎች በአላዛር አድማሱ አማካኝነት ግብ ማግኘት ችለዉ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ፤ በ88ተኛዉ ደቂቃ ላይ ጫላ ተሽታ ከርቀት ድንቅ ግብ በማስቆጠር የቡናማዎቹን የግብ መጠን ወደ አምስት ከፍ ሲያደርግ በ90ናኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ መሐመድ ኑር ናስር ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ መርሐግብሩን ኢትዮጵያ ቡናዎች 6ለ1 እንዲያሸንፉ አስችሏል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በሜዳዉ እና በደጋፊዉ ፊት ሀድያ ሆሳዕናን 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ አመሻሽ 12:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ ላይም ገና በጊዜ በአስረኛዉ ደቂቃ ሀይቆቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማግኘት ችለዋል። በዚህም በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ የመስመር ተጫዋቹ እዮብ አለማዩ ይዞ ገብቶ ለአጥቂዉ እስራኤል እሸቱ አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በቶሎ መልስ ለመስጠት የሞከሩት ሀድያዎች በዳዋ ሁቴሳ አማካኝነት በ13ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጠሩ ተብሎ ሲታሰብ ያመከኑት እድል አስቆጪ ነበር ፤ በተመጣጣኝ የሚባል የመሐል ሜዳ ፉክክር በቀጠለዉ ጨዋታም በ22ተኛዉ ደቂቃ ላይ አሊ ሱለይማን ጥሩ የግብ ዕድል አግኝቶ ኳሷን ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የግብ ዘቡ ያሬድ ኳሷን እንደምንም ይዟል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ተጨማሪ ሙከራዎችን ሳንመለከት አጋማሹ ሲጠናቀቅ ፤ ከዕረፍት መልስ ግን ተሻሽለዉ የገቡት ሀድያዎች በ51ኛዉ ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል ። በዚህም ከሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ ወደ ግራ መስመር በኩል የተሰጠዉን የቅጣት ምት ኳስ ዳዋ ሁቴሳ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
በዚህ ሂደት በተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በቀጠለዉ ጨዋታ በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ በሜዳዉ የቀኝ መስመር በኩል አሊ ሱለይማን ወደ ዉስጥ ሲቀንሰዉ ኳስ በሀድያዉ ተከላካይ ከድር ኩልባሊ አማካኝነት በዕጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አሊ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡ ሀዋሳ ከተማ ጨዋታዉን 2ለ1 እንዲያሸንፉ አስችሏል።