ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም ክለቦች በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ አደጋዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተመልክተናል ። በዚህም በመባቻዉ በ5ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደዊት ተፈራ ከአማካዩ ናትናኤል የተቀበለዉን ኳስ ወደ ግብ በመሞክርም የግብ ዘቡ ኬኒ ሲመልስበት ፤ በተመሳሳይ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሞሰስ ኦዶ ከቀኝ መስመር በኩል ከሄኖክ የተቀበለዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች ።
በአንፃሩም በይበልጥ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በአብዝሀኛዉ የጨዋታዉ ክፍለ ጊዜ በመከላከል ስራ ላይ ያሳለፉት ሻሸመኔ ከተማዎች በአጋማሽ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ ቢቸገሩም ፤ ነገር ግን በተደጋጋሚ ይጥሏቸዉ በነበሩ ረዣዥም ኳሶች አንዳች ነገርን ለመፍጠር ሲጥሉ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የቀኑ ጨዋታ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ፈረሰኞቹ በአጥቂ ሞሰስ ኦዶ አማካኝነት ግልፅ የግብ እድል አግኝተዉ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ኳሷን ሳይጠቀምባት ቀርቶ አጋማሹ ያለ ግቅ ተጠናቋል ። ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክር የተመለከትን ሲሆን በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በርከት ያሉ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ግብ ለማስቆጠር ግን አሁንም ሲቸገሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በአንፃሩ አሁንም ረዣዥም ኳሶችን ለአጥቂዉ ስንታየሁ በማድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር ይጥሩ የነበሩት ሻሸመኔዎች በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል ። በዚህም ከግራ በኩል ከረመዳን የተሻገረዉን ኳስ ታምራት በጭንቅላቱ ሲጨርፋት ያገኛት አማኑኤል ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። የመሪነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ጫናቸዉን አጠንክረዉ ያቃጠሉት ፈረሰኞቹ በ86ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግባቸዉን አግኝተዋል ፤ በዚህም ቢኒያም በላይ በግራ በኩል እየገፋ ሳጥን ዉስጥ ገብቶ ያቀበለዉን ኳስ አማኑኤል ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡ ሁለት ለዜሮ እንዲያሸንፍ አድርጓል።
* ቀዝቃዛ ፉክክር በተስተዋለበት የምሽቱ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታቸውን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል ።
ምሸት አንድ ሰዓት ሲል በጀመረዉ እና በጨዋታ እንዲሁም በሙከራ ረገድ ቀዝቃዛ በነበረዉ የዕለቱ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ከተፈጠሩት ዕድሎች መካከል ጋዲሳ መብራቴ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሳጥን ዉስጥ ከገባ በኋላ ለተመስገን አቀብሎት ተጫዋቹ ኳሷን ሳይጠቀምባት ቀርቷል።
በተቃራኒው ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዉ የተስተዋሉት ሀድያዎች በአብዝሀኛዉ የጨዋታዉ ክፍለ ጊዜ በይበልጥ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመከላከል ላይ እንቅስቃሴ ላይ አሳልፈዋል።
ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በርከት ባሉ የኳስ መቆራረጦች በቀጠለዉ እና ማራኪ እንቅስቃሴ ባላስመለከተዉ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች ምንም እንኳን ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ ግን የተሻሉ ሁነዉ ተስተውሏል ።
በተቃራኒው በሁለተኛው አጋማሽ አንድ ሁለት እድሎችን መፍጠር የቻሉት ሀድያዎች ዳዋ ሆቴሳ ከተመስገን በተቀበላት ኳስ ድንቅ ሙከራ አድርገዉ ግብ ጠባቂዉ ፋረመስ ሲመልስ ፤ በተመሳሳይ በየነ ባንጃዉ ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ዉጥናቸዉ ሰምሮ ሁለቱም ክለቦች ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታዉ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።