ቀን 10:00 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ፊሽካ በጀመረዉ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ገና በጨዋታዉ መባቻ በ12ተኛዉ ደቂቃ ላይ የፊት መስመር ተጫዋቹ ሱራፌል ከቀኝ በኩል ከያሬድ የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም አምበሉ በረከት ተንሸራቶ ኳሷን አምክኗታል ።
የመሐል ሜዳ ብልጫ የነበራቸዉ ሀዋሳ ከተማዎች አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን በቀጥታ በተከላካዮች መሐል ለአሊ ሱለይማን ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ በቀኝ ዕግሩ ወደ ግብነት ቀይሮ ተጫዋቹ ገና በ20ኛዉ ደቂቃ ላይ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ግብ አስቆጣሪዉ አሊ ሱለይማን ዳግም ከታፈሰ ሰለሞን ድንቅ ኳስ ተቀብሎ ግብ ለማስቆጠር ቢሞክርም የመስመር ዳኛዉ ከጨዋታ ዉጭ ብለዉ ሽረዉታል።
በተመሳሳይ በዕለቱ በመሐል ሜዳዉ ላይ ድንቅ የነበረዉ ታፈሰ ሰለሞን ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በሀዋሳ የቀኝ ማጥቃት መስመር በኩል ቆሞ ለነበረዉ አሊ ሱለይማን ድንቅ ሰንጣቂ ኳስ አሻግሮለት አሊም ኳሷን በሚገባ ገፍቶ ሳጥን ዉስጥ ከገባ በኋላ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ አድርጓል።
- ማሰታውቂያ -
በሙከራ ረግድ ደካማ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ38ተኛዉ ደቂቃ ላይ ቻርልስ ሙሰጌ ከያሬድ የተሻገረለትን ኳስ በርከት ባሉ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች መሐል በጭንቅላቱ ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂዉ ፅዮን መርዕድ ኳሷን አዉጥቷታል።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች የእንቅስቃሴ ለውጦችን በማድረግ በተለይ ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ነገር ግን የኋላዉ ክፍል የነበረዉ አደረጃጀት ደካማ መሆኑ በብዙ ዋጋ ሲያስከፍላቸዉ ተመልክተናል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ በ65ተኛዉ ደቂቃ ላይ አሊ ሱለይማን ግልፅ የግብ ዕድል ቢያገኝም ነገር ግን ተጫዋቹ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በድጋሚ በ77ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባዉ እስራኤል እሸቱ ከኋላ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ግብ ለማስቆጠር ቢሞክርም ነገር ግን ግብ ጠባቂዉ እዮብ ካሳየ ኳሷን ግብ ከመሆን አክሽፏታል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታም በ ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች ሶስተኛ ግብ አስቆጥረዋል ፤ በዚህም ተቀይሮ የገባዉ እስራኤል እሸቱ ያቀበለዉን ኳስ አሊ ሱለይማን ወደ ግብ ሲሞክረዉ ግብጠባቂዉ ዳግም ሲመልሰዉ ራሱ አሊ በድጋሚ ወደ ግብነት ቀይሮ ሀዋሳ ከተማዎች የዕለቱን ጨዋታ 3ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል።
* በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ መቻል ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ማሸነፍ ችሏል ።
በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች መርሐግብራቸዉን ገና ከመጀመራቸው በ4ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተጥሯል ። በዚህም ከቀኝ በኩል ከንዓን ለበሀይሉ ያቀበለዉን ኳስ ተጫዋቹ በቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር ሷሷን ያገኛት ምንይሉ ወንድሙ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መቻልን ገና በአራተኛው ደቂቃ መሪ ማድረግ ችሏል።
በይበልጥኑ በቀኝ መስመር በኩል ብልጫ የነበራቸዉ እና ከነበራቸዉ ብልጫ አንፃር ዳግም በፈጣን ሽግግር ሳጥን ውስጥ የደረሱት መቻሎች ያገኙትን ኳስ በዮሐንስ አማካኝነት በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂዉ ፍሬዉ ሲመልሳት ኳሷን በቅርብ ያገኛት አቤል ነጋሽ ወደ ግብነት ቀይሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 2ለ0 ከፍ ማድረግ ችሏል።
በተመሳሳይ ብልጫ በወሰዱበት የቀኝ መስመር በኩል ከነዓን ማርክነህ ከኤፍሬም ነጋሽ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ከገቡ በኋላ ከነዓን በቀጥታ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ ግብ ጠባቂዉ አመከናት እንጅ መቻሎች መሪነታቸውን ወደ ሶስት ከፍ ለማድረግ ተቃርበው ነበር ። በአጠቃላይ በመጀመሪያዉ አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸዉ ባንኮች አጋማሹ ለገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩ በቢኒያም ጌታቸዉ አማካኝነት ከግራ በኩል ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም የግብ ዘቡ አሊዮንዚ መልሶባቸዋል።
በሁለተኛዉ አጋማሽ በመመራት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረዉ መጫወት ሲቀጥሉ በአንፃሩ መቻሎች መሪነታቸዉን አስጠብቀዉ ተጨማሪ ጎሎችን ደግሞ ለማግኘት በተለይ በባንክ የግራ መከላከል በኩል የነበራቸዉን ብልጫ አጠንክረዉ ሲቀጥሉ ተስተውሏል።
በ58ተኛዉ ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቆመ ኳስ በፉዓድ ፈረጃ አማካኝነት ድንቅ ሙከራ አድርገዉ ግብ ጠባቂዉ ሲያወጣ ፤ በተቃራኒው በ76ተኛዉ ደቂቃ ላይ በመቻል በኩል ምንይሉ ወንድሙ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም የግብ ዘቡ ፍሬዉ ኳሷን እንደምንም አምክኗት ጨዋታዉ በመቻል 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።