የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ በፋሲል ከነማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተደርጎ በአፄዎቹ የ2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ፋሲል ከነማ በጨዋታው የተጠቀመው የመጀመሪያ ምርጥ አስራ አንድ ይህን ይመስላል ። ሳማኪ ሚካኤል ፣ አለምብርሀን ግዛው ፣ መናፍ አወል ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ አምሳሉ ጥላሁን ፣ ይሁን እንደሻው ፣ ሽመክት ጉግሳ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ናቸው ።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በጨዋታው የነበረው ምርጥ አስራ አንድም ይህን ይመስላል ። ዘሪሁን ታደለ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ ፣ ተስፋዬ በቀለ ፣ ያረዴ የማነ ፣ አብነት ደምሴ ፣ ስንታየሁ ወለጬ ፣ ሙሴ ከበላ ፣ ናትናኤል መስፍን ኢብራሂም ከድር እና ልደቱ ለማ ናቸው ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሙሉ የአጋማሹ ክፍለ ጊዜም ያን ያህል በግብ ሙከራዎች የታጀበ አልነበረም ።
በፋሲል ከነማ በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ቢያደርጉም የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ይህንን የፈቀዱ አልነበረም ።
በጨዋታው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በቀላሉ ይዞታል ።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ጊዜን በአጋማሹ በማሳለፍ በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን ኳሶች ወደ ፋሲል ከነማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገዋል ።
በጨዋታው በቀጣይ የነበረው የግብ ሙከራ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም በ34ኛው ደቂቃ ላይ አለምብርሀን ይገዛው ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ሲሆኑ ሁለቱም በግብ ጠባቂው ተይዘዋል ።
በ37ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሽመክት ጉግሳ በተከታታይ የደረሱትን ኳሶች ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ በሁለተም በኩል ተመጣጣኝ ሊባል በሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረ ነበር ። ነገር ግን አፄዎቹ በአንፃራዊነት ከተጋጣሚያቸው የተሻለ በተቃራኒ የግብ ክልል ላይ ከኳስ ጋር ሲገኙ ተስተውሏል ።
ፋሲል ከነማዎች የኢትዮ ኤሌክትሪክን የግብ ክልል ደጋግመው ማንኳኳት ቢችሉም በአጋማሹ ቀዳሚ 23 ደቂቃዎች ዘሪሁንን የፈተነ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል ።
በ69ኛው ደቂቃ ላይ ግን የመጀመሪያ ግብ በ2013 የሊጉ ሻምፕየኖች በኩል ተቆጥሯል ። በመልሶ ማጥቃት ይዘው የሄዱትን ኳስ አምሳሉ ጥላሁን ከታፈሰ ሰለሞን ተቀብሎ ሳይጠበቅ በቀኝ እግሩ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሯል ።
የመጀመሪያው ግብ ከተቆጠረ በሰከንዶች ልዩነት በጨዋታው ከዚህ ቀደም ባልታዩ መልኩ የፊት አጥቂ ሚናን ይዞ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ኳስ እና መረብን በማገናኘት የአፄዎቹን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አድርጓል ።
78ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያግዛቸውን አስቆጥረዋል ። ከቆመ ኳስ በረጅን የተሻገረውን አብነት ደምሴ በግንባር ሲገጨው ከግቡ ለቆ የወጣው የግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል አስተዋጽኦም ታክሎበት ግቡ ተቆጥሯል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የጨዋታውን ውጤት ወደ አቻ ለመቀየር ጥረቶችን ቢያደርጉም ይበልጥ የመከላከል ሚና ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይሮ ያስገባውን የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው ቡድን ላይ ሌላ ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል ።
በመጨረሻም ፋሲል ከነማ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ከጨዋታው ሶስት ነጥቦችን ይዞ መውጣት ችሏል ።
በጨዋታው የነበሩ ቁጥራዊ መረጃዎች
ፋሲል ከነማ 2 – 1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
15 የግብ ሙከራ 7
6 ኢላማቸውን የጠበቁ 3
13 ጥፋት 25
1 ቢጫ ካርድ 1
0 ቀይ ካርድ 0
4 የማዕዝን ምት 2
54% የኳስ ቁጥጥር 46%
ቀጣይ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ቅዳሜ የካቲት 18 (ቀን 10:00)
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና
ቅዳሜ የካቲት 18 (ምሽት 1:00)
ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ