በ25ኛዉ ሳምንት በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ12:00 ሰአት ጀምሮ ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና እና በለገጣፎ ለገዳዲ መሀከል የተደረገዉ ጨዋታ በአንድ አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ቡና አስራ አንደኛዉ የአቻ ዉጤት ሆኖ ሲመዘገብ ለለገጣፎ ለገዳዲ በበኩሉ የፕሪሚየር ሊግ ቆይታዉ የተቋጨበት ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል።
የመጀመሪያዉ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተስተዋለበት የነበረ ቢሆንም በአንፃሩ ለገጣፎ ለገዳዲዎች የጎል እድል ለመፍጠር ባደረጉት እንቅስቃሴ የተሻሉ ነበር።
ለአብነትም በጨዋታዉ ክፍለ ግዜ መጀመሪያ አከባቢ እና መሀከል ላይ በአማኑኤል አረቦ እና በጋብሬል አህመድ አማካኝነት የጎል እድል ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ሳይሳካላቸዉ ቀርቶ የመጀመሪያዉ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ ያለ ግብ ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛዉ አጋማሽ ከመጀመሪያዉ የተሻለ የነበረ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል አረቦ ባስቆጠረዉ ጎል ለገጣፎዎች ጨዋታውን 1-0 በሆነ ዉጤት መምራት ጀምረዋል።
ጨዋታዉ እስከ 79ኛ ደቂቃ ድረስ በለገጣፎ ለገዳዲ መሪነት የቀጠለ ቢሆንም በ79ኛ ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የተገኘዉን የቅጣት ምት ኳስ ኃይለሚካኤል አደፍርስ በግራ መስመር በኩል ያሻማዉን ኳስ መሀመድኑር ናስር በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት የቀየረ ሲሆን ጨዋታዉ 1-1 ሆኗል።
ጨዋታዉ ወደ አቻ ዉጤት ካመራ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል በመስፍን ታፈሰ በኩል ማግኘት ችለዉ የነበረ ቢሆንም የለገጣፎ ለገዳዲዉ ግብ ጠባቂ ኮፊ ሜንሳህ አምክኖበታል።
በመጨረሻዎቹ በጨዋታዉ ክፍለ ግዜ ሁለቱም ክለቦች ተጭነዉ ተጫዉተዉ አንዳቸዉ ወደ አንዳቸዉ የግብ ክልል ቢደርሱም ነገር ግን ያገኟቸዉን የግብ እድሎች ሳይጠቀሙ ቀርተዉ ጨዋታዉ 1-1 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎም ለገጣፎ ለገዳዲ በሊጉ ዉስጥ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች እያሉት በ12 ነጥብ እና በ40 የጎል እዳ በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።